ዋዜማ- የተቀሠቀሰው ጦርነት በዓለም ዙሪያ የነዳጅ እና ጋዝ ቀውስ አስከትሏል። በቀጠናው የነዳጅ ላኪ የኾኑት ኳታር፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኩዌት፣ ኢራን እና ኢራቅ በተለይ ኢራን ሆርሙዝ ሠርጥን ከዘጋች ወዲህ፣ አብዛኛውን የነዳጅ ምርታቸውን ለዓለማቀፍ ገበያ ማቅረብ አልቻሉም። ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በዓለማቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል በ50 በመቶ ጨምሯል። የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና የአቅርቦት ሠንሠለቱ መስተጓጎሉ፣ በተለይ የምግብ ሸቀጦች እና የማዳበሪያ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጓል።

የአፍሪካ ልማት ባንክና አጋሮቹ ባወጡት ሪፖርት ሀያ ዘጠኝ ያህል የአፍሪቃ ሀገራት በነዳጅ ቀውሱ ሳቢያ የመገበያያ ገንዘባቸው ማሽቆልቆል ገጥሞታል። ሴኔጋል ፣ሱዳንና ጋምቢያ የሀገራቸውን የውጪ ምንዛሪ ተቀማጭ አቅም እያሟጠጡ ነው።

ዓለማቀፍ የነዳጅ ቀውስ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የተጣራ ነዳጅ ከውጭ የሚያስገቡ የአፍሪካ አገራትን ምን ያህል ለነዳጅ ዋጋ እና እጥረት ተጋላጭ እንደሆኑ በገሃድ አሳይቷል።

ሀገራት የነዳጅ ጉዳይን የሚከታተሉ ሚንስትሮቻቸውንና ሌሎች ባለስልጣናት በሙስናና በአቅም ችግር ሳቢያ ከማባረር እስከ እስር የደረሰ እርምጃ ወስደዋል።

40 ያህል የአፍሪካ አገራት ከውጭ በሚያስገቡት ነዳጅ ላይ ጥገኛ ናቸው። የምስራቅ አፍሪካ አገራት በዋናነት በባሕረ ሠላጤው አገራት ነዳጅ እና ጋዝ ላይ ጥገኛ መሆናቸው፣ የነዳጅ ስትራቴጂክ መጠባበቂያቸው አነስተኛነት እና የቁጥጥር ሥርዓታቸው መላላት፣ የዓለማቀፍ የነዳጅ ገበያ ሲናጋ ጫናው ወዲያውኑ ያርፍባቸዋል። ዓለማቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ ነዳጅ ከውጭ የሚያስገቡ አገራት በትንሹ የ90 ቀናት የፔትሮሊየም ስትራቴጂክ መጠባበቂያ መያዝ እንዳለባቸው ይመክራል።

በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነቱ ከተቀሠቀሠና በተለይ 20 በመቶው የዓለም ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ሠርጥ ከተዘጋ በኋላ፣ በርካታ የአፍሪካና እስያ አገራት የነዳጅ እጥረትን ለማስቀረት እና የነዳጅ ዋጋ እንዳያሻቅብ ለመከላከልል የሚያስችሉ የተለያዩ አስተዳደራዊ፣ ሕጋዊና ኢኮኖሚያዊ ርምጃዎችን ወስደዋል።

ኢትዮጵያ

ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት የከፋ የነዳጅ እጥረትንና የዋጋ ጭማሪን ለማስቀረት ጠበቅ ያሉ አስተዳደራዊ ርምጃዎች የወሠደችው ኢትዮጵያ ናት። የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ እጥረትን ለመቅረፍ ነዳጅ ቅድሚያ የሚሠጣቸውን ተቋማት እና ዘርፎች ይፋ አድርጓል። ለነዳጅ ቅድሚያ ከተሠጣቸው መካከል፣ ቁልፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች፣ የመሠረታዊ ፍጆታ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ላኪዎች እና አስመጪዎች፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሠጪዎች፣ የጸጥታ እና የጤና ተቋማት እና የሰብዓዊ አገልግሎቶች ይገኙበታል። ሕዝቡም የእግር ጉዞ እንዲለምድ መንግሥት መክሯል።

አንዳንድ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው በርቀት ሥራ እንዲሠሩ፣ ተሽከርካሪዎችን በጋራ እንዲጠቀሙ፣ ለቁልፍ ተልዕኮዎች ካልሆነ ተሽከርካሪዎችን እንዳያንቀሳቅሱ ያደረጉ ሲሆን፣ እጅግ አስፈላጊ ላልሆኑ ሠራተኞቻቸውም በግዳጅ የዓመት እረፍት እስከመስጠት ደርሠዋል።

መንግሥት የነዳጅ ሥርጭትን የሚቆጣጠር እና ለነዳጅ ቅድሚያ ለተሠጣቸው ተቋማት እና አገልግሎቶች ነዳጅ በትክክል በመመሪያው መሠረት መድረሱን የሚከታተል ልዩ ክፍልም አቋቁሟል።

ከነዳጅ ሕገወጥ ንግድና ነዳጅ ያላግባብ ከማከማቸት ጋር በተያያዘ የመንግሥት ሃላፊዎችን ጨምሮ ከ600 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል። የነዳጅና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር፣ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር ወይም ያላግባብ ተከማችቶ የነበረ በብዙ መቶ ሺህ ሊትር የሚገመት ነዳጅ መውረሱንም ተናግሯል።

የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማስከተሉን በመጥቀስ፣ መንግሥት በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ላይ ጭማሪ አድርጓል። ከጦርነቱ ጀምሮ መንግሥት በወር ከ15 እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ ድጎማ እያዋለ እንደሚገኝ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ኬንያ

ኬንያ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ አብዛኛውን የነዳጅ ፍላጎቷን የምታሟላው ከመካከለኛው ምስራቅ በተለይም ከባሕረ ሠላጤው አገራት ነው። ለሦስት ሳምንት ብቻ የሚበቃትን መጠባበቂያ ነዳጅ የምታጠራቅመው ኬንያ፣ ጦርነት ተከትሎ ከአጠቃላይ ነዳጅ ማደያዎቿ 20 በመቶ ያህሉ የነዳጅ እጥረት እንደገጠማቸው ተነግሯል።

ሆኖም የአገሪቱ መንግሥት ጦርነቱ የደቀነውን ስጋት ለመመከት ይህ ነው የሚባል ጥብቅ ርምጃ እስካሁን አልወሠደችም። መንግሥት ሆርሙዝ ሠርጥ ቢዘጋም ነዳጅ አቅራቢዎች ከአውሮፓ እና ሕንድ ጭምር ነዳጅ እያጓጓዙ መሆኑን በመግለጽ፣ ምንም እንኳ ነዳጅ ያላግባብ የሚያከማቹ ነጋዴዎች ቢኖሩም የነዳጅ እጥረት ግን አልተፈጠረም ብሏል። ባለስልጣናቱ፣ የአገሪቱ የነዳጅ አቅርቦት የተረጋጋ ሆኖ እንደሚቀጥልና የሚያሠጋ ነገር እንደሌለም በመግለጽ ላይ ናቸው። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ረቡዕ መጋቢት 30 ድረስም፣ በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ አልተደረገም።

መንግሥት የነዳጅ እጥረት ስጋት የተፈጠረ የመሰለው ዋጋው እስኪጨምር ለመጠበቅ ያላግባብ ነዳጅ ያከማቹ አካላት በመኖራቸው ነው ብሏል። ያላግባብ ያከማቹትን ነዳጁን ወደ ገበያ ባስቸኳይ የማያወጡ አካላት ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም ባለስልጣናቱ አስጠንቅቀዋል። ይህንኑ ተከትሎ፣ መንግሥት በኢነርጂው ዘርፍ በተደራጀ ሕገወጥ መረቦች ላይ የተጠናከረ ዘመቻ ከፍቷል። በጦርነቱ እጥረት የተፈጠረ በማስመሰል ከደረጃ በታች የሆነ ነዳጅ ለገበያ አቅርበዋል የተባሉ ሦስት የአገሪቱ ብሄራዊ የፔትሮሊየም ኩባንያ እና የሌሎች ኩባንያዎች ሃላፊዎች የታሠሩ ሲሆን፣ ሌሎች ሁለት ኃላፊዎችም ምርመራ ተጀምሮባቸዋል ተብሏል።

ኡጋንዳ

ኡጋንዳ እስከተያዘው ሚያዝያ ወር መገባደጃ በቂ መጠባበቂያ ነዳጅ እንዳላት የገለጠች ሲሆን፣ ኡጋንዳዊያን በነዳጅ ረገድ ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ በመግለጽ ባለስልጣናቷ ሕዝቡን በማረጋጋት ላይ ናቸው። መንግሥት፣ ነዳጅ አከፋፋዮች በነዳጅ ምርቶች ላይ ዋጋ እንዳይጨምሩ ከማስጠንቀቅ ያለፈ ከነዳጅ ቁጠባ ጋር በተያያዘ እስካሁን የወሠደው ጠበቅ ያለ ርምጃ የለም።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት፣ በኬንያዋ ሞምባሳ እና በታንዛኒያ ወደቦች በቅርቡ የሚገባ ተጨማሪ ነዳጅ እንደሚኖርና ይህም የአገሪቱን ስትራቴጂ የነዳጅ መጠባበቂያ ይበልጥ አስተማማኝ እንደሚያደርገው ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ደቡብ ሱዳን

ደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የድፍድፍ ነዳጅ አምራች ብትሆንም፣ ድፍድፉን ግን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተጣራ ነዳጅ የምታስገባ አገር ናት። ከፍተኛ የድፍድፍ ነዳጅ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ደቡብ ሱዳን፣ 96 በመቶውን የኤሌክትሪክ ኃይሏን የምታመርተው ከነዳጅ ነው። የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ፣ አገሪቱ የገጠማትን የነዳጅ እጥረት ለመቋቋምና ነዳጅ ለመቆጠብ፣ መንግሥት በዋና ከተማዋ ጁባ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በመቀነስ በፈረቃ እንዲዳረስ ማድረግ ጀምሯል።

ታንዛኒያ

የነዳጅ አቅርቦቱን ለመጨመር ከስትራቴጂክ መጠባበቂያዋ ነዳጅ ለገበያ እንዲውል አድርጋለች። ታንዛኒያ የሆርሙዝ ሠርጥ መዘጋት የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል እንደፈጠረ በመግለጽ፣ ከሳምንት በፊት በነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ የተባለ ጭማሪ አድርጋለች።

የአገሪቱ የነዳጅ ዋጋ ተቆጣጣሪ ተቋም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ባደረገ ማግስት፣ የተቋሙ ሃላፊ ከሥልጣን ተባረዋል። ተቋሙ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ያደረገው፣ የመንግሥት ባለስልጣናት አገሪቱ እስከ ግንቦት የመጀመሪያ ሳምንት የሚበቃ መጠባበቂያ ነዳጅ አላት ካሉ በኋላ ነበር።

ከመጋቢት 30 ጀምሮ ደሞ ከፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ጋር ለሥራ የሚንቀሳቀስ ባለስልጣናት በሙሉ ባንድ አውቶብስ እንዲጓዙ ታዘዋል። ፕሬዝዳንት ሳሚያ፤ ባለስልጣኖቻቸው አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዞዎችን እንዲሠርዙና ነዳጅ በቁጠባ እንዲቀሙ መመሪያ ሠጥተዋል።

መንግሥት ለነዳጅ ድጎማ ፈንድ እንዲያቋቋም ጭምር ለፓርላማው ሃሳብ ቀርቧል።

ሞሪሺዬስ

የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት ከውጭ ነዳጅ የምታስገባው ሞሪሺዬስ፣ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል በሚጠቀሙ አካባቢዎች ላይ የኃይል ብክነት እንዳይኖር ገደብ ጥላለች።

የደቡባዊ እስያ አገራትም፣ የነዳጅ እጥረቱን ለመፍታትና የነዳጅ ዋጋን ለመቆጣጠር ጠበቅ ያሉ ርምጃዎችን በመውሠድ ላይ ናቸው። እንደ ቬትናም፣ ታይላንድ፣ ፊሊፒንስ እና ኢንዶኔዥያ ያሉ የቀጠናው አገራት 57 በመቶውን የነዳጅ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት ከመካከለኛው ምሥራቅ ነው።

ማዳጋስካር ለሶስት ሳምንት የሚቆይና ሊራዘም የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጋለች። የሀገሪቱ መንግስት ነዳጅን ከመንግስት የዋጋ ተመን በላይ የሚሸጡ የበረታ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ብሏል።

ዛምቢያ በበኩሏ የነዳጅ ችግር እስኪፈታ በነዳጅ ላይ ተጥሎ የነበረውን ታክስ አንስታለች።

ቬትናም

ቬትናም 80 በመቶውን ድፍድፍ የምትገዛው ከኩዌት ነው። የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የነዳጅ እጥረት ባስከተለ በኋላ፣ መንግሥት ነዳጅ ለመቆጠብ ሲል የመንግሥት ሠራተኞች ከቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ መመሪያ አውጥቷል። የቬትናም አየር መንገድ ደሞ 23 የአገር ውስጥ በረራዎችን በቅርቡ ሠርዟል።

ቬትናም አማራጭ የኢነርጂ ምንጭ ፍለጋ ፊቷን ወደ ድንጋይ ክሰል እንደገና ለመመለስ የተገደደች ሲሆን፣ ነዳጅን መልሶ ለውጭ ገበያ ማቅረብን ለማቆም ማሰቧንም ከቀናት በፊት ገልጣ ነበር።

ፊሊፒንስ

አነስተኛ ስትራቴጂክ የነዳጅ መጠባበቂያ ያላት ፊሊፒንስ፣ ፊሊፒንስ 95 በመቶውን ነዳጅ የምታስገባው በዋናነት ከሳዑዲ ዓረቢያ ነው። ፊሊፒንስ፣ በቀጠናው የነዳጅ እጥረቱ ክፉኛ ተጽዕኖ ካሳደረባቸው አገራት መካከል በቀዳሚነት የምትተጠቀስ ሆናለች። የአገሪቱ መንግሥት ጦርነቱን ተከትሎ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ ደርሷል። ነዳጅ ለመቆጠብ ሲባል፣ የመንግሥት የስራ ቀናትም አራት ቀናት ብቻ እንዲሆኑ ተወስኗል። ፊሊፒንስ አማራጭ የኢነርጂ ምንጭ ፍለጋ ፊቷን ወደ ድንጋይ ከሰል እንደገና መመለስ መጀመሯም ተገልጧል።

ኢንዶኔዥያ

ኢንዶኔዥያ የነዳጅ እጥረትን ለመቋቋም ከወሠደቻቸው ጠበቅ ያሉ ርምጃዎች መካከል አንዱ፣ የግል ተሽከርካሪዎች የሚገዙት ነዳጅ በቀን ከ50 ሊትር እንዳይበልጥ ማድረጓ ተጠቃሽ ነው። የአገሪቱ መንግሥት የነዳጅ ዋጋን ለማረጋጋት በቢሊዮኖች ዶላር ድጎማ በማድረግ ላይ ነው።

ኢንዶኔዥያ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት እንዳይገጥማት፣ የነዳጅ ምንጮቿን በማስፋት ከአፍሪካና አሜሪካ ተጨማሪ ነዳጅ ማስገባትን እንደ መፍትሄ ወስደዋለች።

የአገሪቱ መንግሥት አየር መንገዶች ለአገር ውስጥ በረራዎች ከ9 እስከ 13 በመቶ ዋጋ እንዲጨምሩ የፈቀደ ሲሆን፣ ከውጭ በሚገቡ የአውሮፕላን መለዋወጫዎች ላይ የሚጥለውን ቀረጥ ደሞ ሙሉ በሙሉ አንስቷል። ይህም የተደረገው፣ አየር መንገዶች በነዳጅ እጥረት የሚደርስባቸውን ጫና ማካካስ እንዲችሉ ነው። [ዋዜማ]