ዋዜማ- በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ዘጠነኛ ቀን ውሎ ለተመካካሪዎች ሙያዊ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ስምንቱ “የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች” በሚመካከሩባቸው አጀንዳዎች ዙሪያ ጥናቶችን ባከናወኑ “ምሁራን” ማብራሪያ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ይህ ማብራሪያ “ተመካካሪዎች” የምክክር አጀንዳዎችን “በአግባቡ” እንዲረዱ የሚያደርግ መሆኑን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።
ተመካካሪዎች ከሐምሌ 17 ቀን፤ 2018 ዓ.ም ጀምሮ 50 አባላት ባሉት “ንዑስ” ቡድን ደረጃ በአጀንዳዎች ዙሪያ “ምክረ ሀሳቦችን” እንደሚያደራጁ ይጠበቃል። ይህ ሂደት ሲጠናቀቅ 250 አባላትን በሚይዙ “ስልታዊ” ቡድኖች ደረጃ ምክረ ሀሳብ የሚደራጅ ሲሆን፤ 500 አባላት ያሉት የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን የሁለቱን “ስልታዊ” ቡድኖች ምክረ ሀሳቦች ወደ አንድ በማምጣት ምክረ ሀሳቡን ያደራጃል ተብሎ ይጠበቃል።
የኮሚሽኑ ማስጠንቀቂያ
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ የሳምንቱን የምክክር ሂደት አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሰጡት መግለጫ፤ “በማህበራዊ ሚዲያዊ የሚሰራጩ መረጃዎች ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ” አሳስበዋል። የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ለተመካካሪዎች ባደረጉት ገለጻ ደግሞ፣ በምክክር ሂደቱ የሚሰነዘሩ ሀሳቦች “ለማህበራዊ ሚዲያ ፍጆታ” መዋል እንደሌለባቸው ማሳሰባቸውን ምንጮች ገልጸዋል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ ሆነው በሚገኙ ተመካካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ኮሚሽነሮቹ መግለጻቸውንም ሰምተናል።
የጦር መሳሪያ መሰብሰብን በተመለከተ
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከሚመካከርባቸው አጀንዳዎች መካከል የ”ሰላም ግንባታ” አጀንዳ አንዱ ሲሆን፤ “ግጭቶችን እና መሳሪያ ያነሱ አካላትን የሚመለከቱ ጉዳዮች” በሚል “ንዑስ” አጀንዳ ውስጥ፤ “ሕገ ወጥ” የጦር መሳሪያን መሰብሰብ የሚቻልበት ሁኔታ በተመካካሪዎች አማራጭ እንዲቀርብበት ተጠይቋል። በዚሁ ንዑስ አጀንዳ ውስጥ ከተካተቱ መሪ ጥያቄዎች መካከል፤ “በሲቪል ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ሕገ ወጥ መሳሪያ መሰብሰብ የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚል ጥያቄ ይገኝበታል። ጥያቄው የመልስ አማራጮችን ያልያዘ ሲሆን፤ ተመካካሪዎች በጥያቄው ዙሪያ አማራጮችን እንዲያቀርቡ የሚጋብዝ ነው።
ፖሊሲ ተዘጋጅቶለት የነበረው የሽግግር ፍትህ ለምክክር ቀርቧል
የሚንስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 9 ቀን፤ 2016 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ “የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን” ማጽደቁን ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ የፍትህ ሚኒስቴርም ፖሊሲውን ለማስተግበር የሚያስችለውን ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቆ ነበር። የፖሊሲው ማስተግበሪያ አዋጆችን ማዘጋጀትን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉለት መሆኑ ሲነገርለት የነበረው ፖሊሲ ግን ተግባራዊ ሳይደረግ ከሁለት ዓመት የዘለለ ጊዜ አስቆጥሯል።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በ”ሰላም ግንባታ” አጀንዳ ውስጥ ካካተታቸው ንዑስ አጀንዳዎች መካከል “የሽግግር ፍትህ” አንዱ መሆኑን ዋዜማ የተመለከተችው ሰነድ ይጠቁማል። ይህ ሰነድ ከሁለት ዓመት በፊት ጽድቆ የትግበራ ምዕራፍ ውስጥ ለመግባት ተዘጋጅቶ የነበረው ፖሊሲ ከተግባራዊነት ተገትቶ፤ የሽግግር ፍትህ እንደ አዲስ ምክክር የሚደረግበት መሆኑን ያረጋገጠ ነው።
ፍትህ ሚኒስቴር ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ ሲያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች በድንገት እንዲቆሙ ተደርገው መቆየታቸውንም ሰምተናል። ለምክክሩ በቀረበው ንዑስ አጀንዳ ውስጥም፤ “በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ከየት ይጀምር?” የሚል ጥያቄን ጀምሮ ጉዳዩ በአዲስ መልክ እንዲታይ የሚያደርጉ መሪ ጥያቄዎች ተዘጋጅተውለታል።
የጣምራ ዜግነት ጉዳይ
ኢትዮጵያ ጥምር ዜግነትን ከማይፈቅዱ የዓለም ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን፤ “የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት ሰብዓዊ መብቶች” አጀንዳ ይህንን ጉዳይ ለምምክር አቅርቦታል። በአጀንዳው ከተካተቱ “ንዑስ” አጀንዳዎች መካከል፤ “የዲያስፖራ ጉዳይ” አንዱ ነው። ለንዑስ አጀንዳው ከተዘጋጁ ጥያቄዎች መካከልም “የጣምራ ዜግነት መብት እውቅና ጉዳይ ምን መሆን አለበት?” የሚለው ይጠቀሳል።
የዲያስፖራው ማህበረሰብ የፖለቲካ መብቶች ጉዳይም በንዑስ አጀንዳው የተካተተ ሲሆን፤ “የዲያስፖራው የመምረጥ እና መመረጥ መብት ምን መሆን አለበት?” የሚል መሪ ጥያቄ መቅረቡን ዋዜማ ለተመካካሪዎች ከቀረበ ሰነድ ተመልክታለች።[ዋዜማ]
