ዋዜማ- ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረት በተፈጠረበት ትግራይ ክልል፤ ጥሬ ብር እሰከ 25 በመቶ በሚደርስ ኮሚሽን እየተሸጠ መሆኑን ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች።

በሕወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ፤ የትግራይ ክልል የድጎማ በጀት አለመለቀቁ ፤ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን የክልሉ ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ይኸው የጥሬ ገንዘብ እጥረት በእለት ተእለት የነዋሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ችግር ከመፍጠሩ ባሻገር፤ በየጊዜው አዳዲስ ህጋዊነት የሌላቸው የጥሬ ገንዘብ ማግኛ መንገዶች እንዲተገበሩ በር ከፍቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ጥሬ ብርን በኮሚሽን መሸጥ በስፋት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህም የነዋሪዎችን እንቅስቃሴ በ2013ቱ ጦርነት ወቅት ወደነበረው ሁኔታ መልሶታል፡፡

የጥሬ ብር እጥረት እና የኮሚሽን ሽያጭ

ከጥቅምት ወር፤ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ከፌደራል መንግሥት የሚላከው የድጎማ በጀት መቋረጥ እንዲሁም በክልሉ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች መካከል የተፈጠረው ውስጣዊ ክፍፍል እና የግጭት ድባብ ተዳምሮ፤ ባንኮች ለጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ብዙዎች ‹‹በ2013ቱ ጦርነት ወቅት ያጋጠመው አይነት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል›› በሚል ስጋት በባንኮች ያስቀመጡትን ገንዘብ በብዛት አውጥተዋል፡፡ በተለይም ባለፉት ሦስት ወራት ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሬ ገንዘብ ከባንኮች ወጪ መደረጉን በክልሉ ከሚገኙ ባንኮች ተረድተናል።

በክልሉ የሚገኙ ባንኮች ደንበኞቻቸው የሚፈልጉትን ያህል ገንዘብ መስጠት ባለመቻላቸው፣ ነዋሪዎች ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚሆን ጥሬ ገንዘብ ለማግኘት ተጨማሪ ክፍያዎችን ለመክፈል ተገደዋል። 

በክልሉ የሚገኙ ባንኮች ለአንድ ደንበኛ በቀን የሚሰጡትን የጥሬ ገንዘብ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ገድበዋል። የጥሬ ገንዘብ እጥረቱ በተባባሰባቸው እንደ መቀለ፣ አዲግራት፣ አክሱም እና አድዋ ያሉ ከተሞች የሚገኙ ባንኮች በአብዛኛው ‹‹ጥሬ ብር የለንም›› በማለት ደንበኞቻቸውን እስከመመለስ መድረሳቸውን ከነዋሪዎች ሰምተናል።።

በአንጻራዊነት እንደ ሽረ እና ማይጨው ባሉ ከተሞች የሚገኙ ባንኮች በቀን ለአንድ ደንበኛ 1 ሺህ ብር እየሰጡ መሆኑን ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት ተረድታለች። ይህም ሁልጊዜ የሚገኝ አለመሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ ባንኮች ‹‹ገንዘብ የለንም›› ብለው የሚመልሱበት ሁኔታም ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አላማጣ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ባንኮች፤ ለደንበኞቻቸው በቀን እስከ 1 ሺህ ብር ድረስ ወጪ ማድረግን እንደሚፈቅዱ ነግረውናል፡፡

ጥሬ ገንዘብ በአፋር እና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች ወደ ትግራይ ክልል ገብቶ በኮሚሽን እየተሸጠ ሲሆን፤ የኮሚሽን ሽያጩ እንደ ጥሬ ብሩ መጠን፤ ከ5 በመቶ እስከ 25 በመቶ ድረስ እንደሚሸጥ ባደረግነው ማጣራት ተረድተናል።

የኮሚሽን ሽያጩ የሚከናወነው በጥሬ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች በኩል ሲሆን፤ ጥሬ ብር የሚፈልጉ አካላት በባንክ ሂሳብ ወይም በሞባይል ባንኪንግ ከ5እስከ 25 በመቶ የሚደርስ የኮሚሽን ክፍያ ጨምረው በመላክ ጥሬ ገንዘብ ይረከባሉ።

የጥሬ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች የሚጠይቁት የኮሚሽን መጠን እንደየ አካባቢው እና እንደሚፈለገው የብር መጠን ልዩነት ያለው ሲሆን፤ የተፈለገው የገንዘብ መጠን አነስተኛ ከሆነ፤ የኮሚሽኑ መጠን ከአምስት እስከ 10 በመቶ ይደርሳል።

በመቶ ሺዎች እና በሚሊዮኖች መጠን ያለው ከፍተኛ ጥሬ ብር በሚፈለግበት ጊዜ፤የኮሚሽን ክፍያው እስከ 25 በመቶ ድረስ ከፍ ይላል።

​በተለይም በወርቅ ማውጣት እና ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት የዕለት ተዕለት ግብይታቸው በጥሬ ገንዘብ የሚፈጸም በመሆኑ፣ እስከ 25 በመቶ የሚደርስ ተጨማሪ ኮሚሽን በመክፈል ጥሬ ብር እንደሚሰበስቡ ምንጮች ጠቁመዋል።

የእርዳታ ድርጅቶች እና የተረጂዎች ፈተና

​በክልሉ የተፈጠረው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ለተፈናቃዮች እና እርዳታ ለሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያቀርቡት ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ፈታኝ እንደሆነባቸው ምንጮች ነግረውናል።

በአይነት እና በገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ የረድኤት ድርጅቶች፤ በቀጥታ የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረግ አለመቻላቸውን የረድኤት ተቋማት ሠራተኞች ለዋዜማ ተናግረዋል። ድርጅቶቹ ከዚህ ቀደም የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉት በጥሬ ገንዘብ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ግን በተረጂዎች የባንክ ሂሳብ ለማስተላለፍ መገደዳቸውን ነግረውናል።

በዚህም አንዳንድ የባንክ ሒሳብ ቁጥር የሌላቸው ተረጂዎች የገንዘብ ድጋፍ የማያገኙበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑ ተገልጿል። የገንዘብ ዕርዳታውን በባንክ ሂሳብ ቁጥራቸው መቀበል የቻሉ ተረጂዎችም በቀላሉ ከባንክ አውጥተው ለመጠቀም እየተቸገሩ ነው። 

ተረጂዎች ጥሬ ብር ለማግኘት ባንኮች ወደ አሉባቸው ከተሞች ደርሰው ለመመለስ ለከፍተኛ የትራንስፖርት ውጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን የሚገልጹት የረድኤት ድርጅቶች ሠራተኞች፤ አብዛኞቹ ተረጂዎች በገጠራማ አካባቢዎች እና በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ በመሆናቸው፤ እምብዛም የዲጂታል ገንዘብ ዝውውር አማራጮችን እንደማይጠቀሙ ነግረውናል፡፡ 

ምንም እንኳን፤ ችግሩ እየከፋ ሲመጣ የዲጂታል ክፍያ አማራጮች እየተለመዱ ቢመጡም፤ በተረጂዎች ዘንድ ግን ውስንነቶች አሉ ብለዋል፡፡ 

አጠቃላይ በክልሉ የተከሰተው የጥሬ ገንዘብ እጥረት በከተሞች አካባቢ ያለውን የግብይት ስርዓት በከፍተኛ ደረጃ ወደ ዲጂታል አማራጮች አዙሮታል። በከተሞች ከትንሽ እስከ ከፍተኛ ግብይቶች ወደ ዲጂታል የገንዘብ ዝውውር የተሸጋገሩ ቢሆኑም፤ በገጠራማ አካባቢዎች ግን ይህ አይነቱ አማራጭ እምብዛም እንደሌለ ተጠቁሟል፡፡ 

በክልሉ የተፈጠረው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ከሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች ጋር ተዳምሮ፤ በክልሉ ያለውን የኑሮ ውድነት ይበልጥ እያባባሰው እንደሚገኝ ተገልጧል።

ለበርካታ ህገ-ወጥ መንገዶች በር የከፈተው የጥሬ ገንዘብ እጥረት፤ የኤርትራ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ‹‹ናቅፋ›› እስከ አዲግራት እና አድዋ ከተሞች ድረስ እንዲሰራጭ ምክንያት መሆኑን የአካባቢውን ነዋሪዎች ዋቢ በማድረግ ዋዜማ ከወራት በፊት ዘግባ ነበር፡፡   [ዋዜማ]