ዋዜማ- ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስምንተኛ ቀን ውሎው በአጀንዳዎች ዙሪያ ”በጥቃቅን” ቡድን ደረጃ ሲካሄድ የቆይውን “ምክክር” አስቀጥሏል። በአጀንዳዎች ዙሪያ የሚካሄድና የመጀሪያ ምዕራፍ “ምክክር” የሆነው ይህ ሂደት የሦስት ቀናት የግዜ ዕቅድ የተያዘለት ቢሆንም፤ እባዛኞቹ ቡድኖች “ምክክራቸውን” አለማጠናቀቃቸውን ምንጮች ነግረውናል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ይህ የምክክር ሂደት ለአንድ ቀን “ባለበት” እንዲቆይና ለተመካካሪዎች በምክክር አጀንዳዎች ዙሪያ የአንድ ቀን ገለጻ እንዲሰጣቸው መወሰኑንም ዋዜማ ሰምታለች። 

ኮሚሽኑ ለተመካካሪዎች ባስተላለፈው መልዕክት ሐምሌ 16 ቀን፣ 2018 ዓ.ም  በአንድ አጀንዳ ዙሪያ ለሚመካከሩና “የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን” በሚል ስያሜ በተደራጁ ቡድኖች ደረጃ፤ የምክክር አጀንዳዎችን የተመለከተ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ጠቁሟል። ማብራሪያውን ኮሚሽኑ ያደራጀው የምሁራን ፓናል (panel of experts) አባላት እንደሚሰጡ የታወቀ ሲሆን፤ ማብራሪያው ለመገናኛ ብዙኃን ዝግ በሆኑ አዳራሾች እንደሚሰጥ ተነግሯል።

የሥርዓተ መንግስት አማራጮች

ለምክክር ከቀረቡና ትኩረት ከሳቡ አጀንዳዎች መካከል አንዱ በሆነው “የመንግስት አደረጃጀት፣ ቅርጽ፣ የፖለቲካ ስርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ስርዓት” አጀንዳ ውስጥ የተካተተው “የመንግስት አደረጃጀት፣ አስተዳደር ስርዓት ዓይነት” ንዑስ አጀንዳ፤ ለኢትዮጵያ ቀጣይ የመንግስት ስርዓት ሦስት አማራጮችን አስቀምጧል። “አሃዳዊ (unitary)፣ “ፌደራላዊ” እና “ኮንፌደራላዊ” የሚሉት አማራጮች ለተመካካሪዎች በቀረበው “የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎች – የውይይት መሪ ጥያቄዎች” ሰነድ ላይ የተቀመጡ ሲሆን፤ ተመካካሪዎች ለኢትዮጵያ ይበጃል የሚሉት ሌላ ስርዓት ካለም እንዲያቀርቡ ሰነዱ ይጠይቃል። 

ተመካካሪዎች የፌደራል ስርዓትን ምርጫቸው የሚያደርጉ ከሆነ፤ “አሁን ያለው የፌደራል ስርዓት ያለምንምማሻሻያ ይቀጥል”፣ “አሁን ያለው የፌደራል ስርዓት ድክመቶቹ ተገምግመው ማሻሻያ ይደረግበት”፣ “ከብሔር ፌደራሊዝም ወጥተን ወደ ጂኦግራፊያዊ ፌደራሊዝም ወይም ይበልጥ ማዕከላዊ ወደሆነ ሥርዓት እንሸጋገር” በሚሉ አማራጮች ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡ መጠየቃቸውን ዋዜማ ተገንዝባለች። 

ሦስት የመንግስት አስተዳደር ስርዓቶችም እንደ አማራጭ ቀርበዋል። “ፓርላሜንታዊ”፣ “ፕሬዝዳንታዊ” እና “የሁለቱ ሥርዓቶች ቅይጥ”  በአማራጭነት የቀረቡ ሥርዓቶች መሆናቸውን ዋዜማ የተመለከተችው ሰነድ ያሳያል። “የፌደራል መንግስት እና የክልል መንግስታት መሪዎች የስልጣን ዘመንን በግዜ መገደብ” የሚለውም በአጀንዳው ስር “ምክክር” የሚደረግበት “ንዑስ” አጀንዳ ሆኖ ተቀምጧል። 

ሦስት አማራጮች የቀረቡለት የምርጫ ሥርዓት

ሀገሪቱ የምትመራበት የምርጫ ሥርዓት “የአብላጫ ድምጽ”፣ “ተመጣጣኝ የውክልና ሥርዓት” እና “ቅይጥ የውክልና ሥርዓት” የሚሉ አማራጮች ቀርበውለታል። የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት ጉዳይም ለምክክር የቀረበ ንዑስ አጀንዳ ሲሆን፤ “ብሔርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀት ቀርቶ ወደ ዜጋ ተኮር የፖለቲካ ሥርዓት ሽግግር እንዲደረግ” በሚጠይቁና “የአሁኑ የፖለቲካ አደረጃጀት የብሔር ብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ማረጋገጫ ስለሆነ ሊነካ አይገባም” በሚሉ ወገኖች መካከል ያለው ልዩነት በምክክር እንዲፈታ በንዑስ አጀንዳው ተጠይቋል።

የሥራ ዋስትና ስጋት የገጠማቸው “ቃለ- ጉባኤ ያዦች”

ኮሚሽኑ 50 አባላት ባሉት “ንዑስ” ቡድን ደረጃ ከሚደረጉ የምክክር ሂደቶች ጀምሮ የጉባኤውን አጠቃላይ ሂደት በቃለ ጉባኤ ለመሰነድ 256 “ቃለ ጉባኤ ያዦችን” አሰልጥኖ ማሰማራቱን ማስታወቁ ይታወሳል። እነዚህ ቃለ ጉባኤ ያዦች ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች ተቋማት የተውጣጡ ሲሆኑ፤ “አንዳንድ” ተቋማት እነዚህ “ቃለ ጉባኤ ያዦች” ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ መጠየቃቸውን ዋዜማ ሰምታለች። ከተቋማቸው መሰሉ ጥሪ የደረሳቸው “ቃለ ጉባኤ ያዦች” ጉዳዩን ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸውን የሰማን ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ተቋማቱን እንደሚያነጋግር መግለጡን አውቀናል። ጉዳዩ የሥራ ዋስትና ስጋት ያለበት መሆኑንም ምንጮች ነግረውናል።

ለተመካካሪዎች አበል የከፈሉ ክልሎች

በምክክሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ “ተመካካሪዎች” የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ሲሆኑ፤ አንዳንድ ክልሎች ለተመካካሪዎች ከፍተኛ አበል መክፈላቸውን ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች። ለተመካካሪዎች “አበል” ከከፈሉ ክልሎች መካከል ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ሲዳማ እና አፋር ክልሎች የሚጠቀሱ ሲሆን፤ “ለትራንስፖርት” በሚል የተከፈለው አበል ከ5 ሺሕ እስከ 80 ሺሕ ብር የሚደርስ መሆኑን ያሰባሰብነው መረጃ ያመላክታል። ለአብዛኛው የሶማሌ ክልል ተሳታፊዎች የ80 ሺሕ ብር የአበል ክፍያ እንደተፈጸመላቸው የገለጡልን ምንጫችን፤ ክፍያው የተፈጸመው ኮሚሽኑ ሁሉንም የተሳታፊዎች ወጭ እንደሚሸፍን ባሳወቀበት ሁኔታ ውስጥ ነው ብለዋል። ለሲዳማ ክልል “ተመካካሪዎች” 5 ሺሕ፣ ከኦሮሚያ ክልል “አንዳንድ” አካባቢዎች ለተወከሉ “ተመካካሪዎች” 9 ሺሕ፣ ለአፋር ክልል “ተመካካሪዎች” ደግሞ እስከ 10 ሺሕ ብር የሚደርስ ክፍያ መፈጸሙንም ምንጮች ነግረውናል።

የምክክር ጉባኤውን ለማካሄድ ከፍተኛ በጀት መመደቡን የገለጡት ምንጫን፤ ተመካካሪዎች ላረፉባቸው “ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ”፣ “ኢትዮ ቻይና ኮሌጅ” እና ለሌሎች ሆቴሎች ከፍተኛ መጠን ያለው ክፍያ እየተፈጸመ ስለመሆኑ ሰምተናል። [ዋዜማ]