ዋዜማ- በትግራይ “ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል” የሚል ስጋት ያደረባቸው በርካታ ወጣቶች ወደ አዲስ አበባና ጎረቤት ሀገራት መሸሻቸውንና ይህን ሽሽት ለመቀልበስ በትግራይ የጉዞ እገዳ እየተደረገባቸው መሆኑን ለዋዜማ ተናግረዋል።

በሕወሓት እና ፌደራል መንግሥት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ፣ የዳግም ግጭት መቀስቀስ ስጋት የገባቸው ወጣቶች ከትግራይ ክልል እንዳይወጡ መንገድ ላይ ተይዞ እስከመመለስ የደረሰ እገዳ እየደረሰባቸው መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች።

የትግራይ ወጣቶች በተከታታይ ወደ መሀል ሀገር መሸሽ በመቀጠላቸው፣ “ሕገ ወጥ ስደተኞች” ናቸው በሚል የእንቅስቃሴ ገደብ እያጋጠማቸው ነው ተብሏል። በየቀኑ ከክልሉ የሚወጡ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑ ያሳሰባቸው፣ የትግራይ ኃይሎች በተለያዩ ስልቶች ሽሽቱን ለመቀልበስ ጫና እየፈጠሩ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት አካላቸው ምንጮች ያሰባሰብነው መረጃ አመላክቷል።

በትግራይ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአመዛኙ ወጣቶች የሚበዙባቸው የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችን እንዳይንቀሳቀሱ እስከመከልከል የደረሰ ገደብ እያጋጠመ ነው ። በተለይ የጉዞ መስመራቸውን ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በኩል የሆኑ ተሽከርካሪዎች፣ ወጣቶችን በብዛት ጭነው የትግራይ ኃይሎች ኬላዎችን አልፈው መሄድ እንደማይፈቀድላቸው በድብቅ ተጉዘው አዲስ አበባ ከደረሱና ከዚህ ቀደም ከመንገድ ተይዘው ከተመለሱ ወጣቶች ሰምተናል።

ከተሳፋሪዎች መካከል በርከት ያሉ ወጣቶችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች የኬላ ፍተሻ ጣቢያዎች ላይ ለሚገኙ የትግራይ ኃይሎች ገንዘብ ተከፍሎ ካልሆነ ማለፍ ፈታኝ መሆኑን ወጣቶች ነግረውናል። በዚህም  ከተለመደ የትራንስፖርት አገልግሎት በተለየ ሁኔታ፣ ወጣቶችን በድብቅ በእግር የፍተሻ ጣቢዎችን ለማሳለፍ እንደሚገደዱ አንድ ዋዜማ ያነጋገረችው አሽከርካሪ ጠቁሟል። 

ቀደም ሲል ወጣቶች ከትግራይ እንዳይወጡ የኬላ ቁጥጥር የነበረው በአማራ እና አፋር አዋሳኝ አካባቢዎች እንደነበር ምንጮች ገልጠዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከመሀል ትግራይ ከተሞች ጭምር በብዛት ወጣቶችን ያሳፈሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አማራ እና አፋር ክሎሎች መስመር እንዳይንቀሳቀሱ እየተከለከሉ ነው ።

በጭነት ተሽከርካሪዎች ጭምር በሌሊት ከትግራይ ለመውጣት የሞከሩ ወጣቶች፣ በፖሊስ ተይዘው በማቆያ ካምፕ እንደሚገኙ ሰምተናል።

ከአስር ቀናት በፊት የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በአንድ ሳምንት ገደማ ብቻ በድብቅ ከትግራይ ለመውጣት የሞከሩ ከ150 በላይ ወጣቶች በፖሊስ ተይዘው መመለሳቸውን ተረድተናል። ከሳምንት በፊት በቀናነት ልዩነት በተከታታይ፣ “ሕገ ወጥ ስደተኞች” እና “ኮብላዮች” ብሎ ያጋለጣቸውን 171 ወጣቶችን መያዙን የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን በፌስቡክ ገጹ ያሰራጨው መረጃ ያመላክታል።

ወጣቶች ወደ መሀል ሀገር እንዲሸሹ ያስገደዳቸው የዳግም ግጭት ውጥረት ያስከተለው፣ የግዳጅ ውትድርና አገልግሎት መሆኑን ይናገራሉ ። የትግራይ ኃይሎች በየአካባቢው በተለያየ ስልት ወጣቶችን ለውትድርና በግዳጅ እየመለመሉ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል።

በሕወሓት እና ፌደራል መንግሥት የፕሪቶሪያ ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት መሠረት፣ በትጥቅ ማስፈታት፣ ከኅብረተሰቡ ጋር በማቀላቀልና መልሶ በማቋቋም የተሰናበቱ ተዋጊዎች ጭምር በግዳጅ ተይዘው ወደ ትግራይ ኃይሎች ካምፕ እየገቡ መሆኑን ምንጮች ገልጠዋል።

በትጥቅ ማስፈታት ሂደት ያለፉ ተዋጊዎች እና በራሳቸው ፈቃድ ወደ ሰላማዊ ህይወት የተመለሱ ወጣቶች በየአድራሻቸው በትግራይ ኃይሎች ተፈገው እየተወሰዱ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል። በተለይ በጦርነቱ ወቀት ተማሪዎች የነበሩ ተዋጊዎች በራሳቸው ፈቃድ በተናጠል ራሳቸውን ከትግራይ ኃይሎች ያገለሉ ቢሆንም፣ የዳግም ግዳጅ ውትድርናውን ሽሽት ከትግራይ ለመውጣት መገደዳቸውን ይናገራሉ።።

የሕወሓት ሊቀመንበርነት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መጋቢት 20፣ 2018 ዓ፣ም በመቀሌ ከተማ በተካሄደ ሰልፍ ላይ ወጣቶችን ወደ አዲስ አበባ እንዳይሸሹ ማስፈራራታቸው ይታወሳል። ደብረጽዮን በወቅቱ ባደረጉት ንግግር “የጦርነት አደጋ አንዣቧል በማለት ወደ አዲስ አበባ በመሄድ የግፍና የእስር ሰለባ እየሆንክ ያለህ የትግራይ ወጣት ስደት መፍትሄ እንዳልሆነ ልትረዳ ይገባል። በአዲስ አበባ ያለህ ወጣት ከብልፅግና ካራ እንደማታመልጥ ተረድተህ ከሰራዊትህና ከህዝብህ ጋር ልትወግን ይገባል” በማለት ወጣቶችን መክረዋል።

በአዲስ አበባ እስርና ማስፈራራት ገጠመን ያሉ የተወሰኑ የትግራይ ወጣቶች አሉ። በተለይ በቡድን ተከራይተው በሚኖሩበት አካባቢ “ኤርትራውያን ናችሁ” ተብለው ለቀናት በእስር ያሳለፉ አራት ወጣቶችን አግኝተናል። 

አዲስ አበባ የደረሱ ወጣቶች የደህንነት ዋስትና፣ የስራ ዕድልና የተረጋጋ የመኖሪያ ምቹ ሁኔታ የሚያገኙበትን አስራር ከመንግስት ጋር እየተነጋገረ የሚያመቻች ግብረ ሀይል መኖሩንም ተረድተናል። 

ወደ አዲስ አበባ ከሚደረግ ሽሽት በተጨማሪ ወደ ጎረቤት ሀገር ኬንያና ዩጋንዳ ሸሽተው የሚሄዱ የትግራይ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን በቅርቡ ናይሮቢ የነበረ የዋዜማ ሪፖርተር ከወጣቶቹ ሰምቷል። [ዋዜማ]