ዋዜማ- ሀገራዊ የምምክር ጉባኤ ሰባተኛ ቀኑን ባስቆጠረበት ሐምሌ 14 ቀን 2018 ዓ.ም፤ ተመካካሪዎች በተመደቡበት  አጀንዳ ዙሪያ 10 ተመካካሪዎችን በሚይዘው “ጥቃቅን” ቡድን ደረጃ የሁለተኛ ቀን “ምክክራቸውን” አከናውነዋል። ይህ የምክክር ሂደት ለሦስት ቀናት ያህል እንደሚቆይ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለተመካካሪዎች ባቀረበው “የሥራ ቡድን የምክክር ስልት” ሰነድ ላይ የተመላከተ ቢሆንም፤ ከስድስት በላይ ንዑስ አጀንዳዎች ያሏቸው አጀንዳዎች ላይ እየተመከካከሩ የሚገኙ “ቡድኖች” በተቀመጠው ግዜ ሂደቱን ላያጠናቅቁ እንደሚችሉ ምንጮች ነግረውናል። 

በተለይም “የሀገር ግንባታ”፣ “የመንግስት አደረጃጀት እና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት” እና “የፌደራል ከተሞችን” ጉዳዮች የተመለከቱ አጀንዳዎች ላይ እየተደረገ ያለው የምክክር ሂደት ዘለግ ያለ ግዜ ሊፈጅ እንደሚችል ሰምተናል። ኮሚሽኑ በያዘው ዕቅድ መሰረት “በጥቃቅን” ቡድን ደረጃ እየተካሄደ ያለው የመጀመሪያው “ሀሳብ የማመንጨት ሂደት” ዛሬ ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ ይጠበቃል። በቀጣይ ሁለት ቀናት ደግሞ አምስት “ጥቃቅን” ቡድኖችን በሚያቅፈውና 50 አባላት እንዲኖሩት ተደረጎ በተደራጀው “ንዑስ” ቡድን ደረጃ “ምክረ ሀሳቦችን” የማደራጀት ሥራ እንዲከናወን ታቅዷል። ይህ ሂደት አምስት “ንዑስ” ቡድኖችን ወደሚያቅፍና 250 አባላት እንዲኖሩት ተደርጎ ወደሚደራጅ “ስልታዊ” ቡድን የሚያድግ ሲሆን፤ 500 አባላት ያሉት የሥራ ቡድን ደግሞ የአጀንዳውን ጥቅል “ምክረ ሀሳብ” የማቅረብ ኃላፊነት አለበት። ሁለቱ ሂደቶች ከአምስት እስከ ስድስት ቀናትን ይወስዳሉ በሚል ግዜ የተያዘላቸው ቢሆንም፤ “በጥቃቅን” ቡድን ደረጃ እየተካሄደ ያለው “ምክክር” የሚጠቃለልበት ግዜና ሁኔታ ቀጣዩን አካሄድ የሚወስን ይሆናል።

አራት አማራጮች የቀረቡላት አዲስ አበባ

ኮሚሽኑ ለተመካካሪዎች ባቀረበው “የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎች – የውይይት መሪ ጥያቄዎች” ሰነድ መሰረት፤ “የአዲስ አበባ ሕጋዊ አቋም” አራት አማራጮች ቀርበውለታል። ተመካካሪዎች አራቱን አማራጮች በመገምገም፤ የከተማዋን “ሕጋዊ አቋም” የተመለከተ ምክረ ሀሳብ “እንዲያመነጩ” የሚጠበቅ ሲሆን፤ በሰነዱ ከተዘረዘሩት አማራጮች ውጭ ተጭማሪ አማራጭ ማቅረብ ስለመቻል አለመቻሉ ሰነዱ አያመላክትም። 

አዲስ አበባን፤ “ሲቲ ስቴት (ራስ ገዝ)”፣ “የፌደራል አካል”፣ “ራሷን የቻለች ክልል”፣ “የኦሮሚያ አካል” ማድረግ የሚሉት ደግሞ በሰነዱ የቀረቡ አማራጮች ናቸው። 

“አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ያላት ግንኙነት”፣ “የከተማዋ በጀት ድርሻ ጉዳይ”፣ “የፌደራል ዋና ከተማ ጉዳይ”፣ “የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ፍርድ ቤት ጉዳይ”፣ “የተከተማዋ ወሰን እና የቦታዎች ስያሜዎች”፣ “የከተማዋ የሥራ ቋንቋ”፣ እንዲሁም “የከተማዋ ታሪካዊ ቅርሶች አካታችነት ጉዳይ”፤ ጥያቄዎች የተዘጋጁላቸው የምክክር “ንዑስ” አጀንዳዎች ሆነው በሰነዱ ቀርበዋል። አዲስ አበባ በፌደራል መንግስት ላይ ስለሚኖራት ውክልና እና የፌደሬሽን ምክር ቤት ውክልና ጉዳይ ግን በንዑስ አጀንዳነት ሳይካተቱ ቀርተዋል። 

የድሬዳዋ ሦስት አማራጮች 

“የፌደራል ከተሞች” በሚለው አጀንዳ ሥር የተካተተችው ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ሦስት “የሕጋዊ አቋም” አማራጮች ቀርበውላታል። “ሲቲ ስቴት (ራስገዝ)”፣ “የፌደራል አካል”፣ “ራሷን የቻለች ክልል” የሚሉት ደግሞ ለከተማዋ የቀረቡ አማራጮች ሲሆኑ፤ ድሬ ዳዋ በኦሮሚያ ወይም በሶማሌ ክልል ውስጥ እንድትሆን የሚጠቁሙ አማራጮች በሰነዱ አልተካተቱም። 

“የድሬ ዳዋ ከተማ የወደፊት አስተዳደራዊ ሁኔታ፣ የሕዝቦቿ አስተዳደራዊ ሁኔታ፣ የሕዝቦቿ ውክልና፣ እና ከኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ጋር ያላት ግንኙነት”፣ “በፌደራል መንግስት የሚኖር የውክልና ጉዳይ”፣ “ድሬ ዳዋ በፌደሬሽን ምክር ቤት የመወከል ጉዳይ” ደግሞ በንዑስ አጀንዳነት ተጠቅሰዋል። 

ምክክሩንእየታዘቡየሚገኙተቋማት

የምክክር ሂደቱን ለመታዘብ ጥያቄ ያቀረቡ የሀገር ውስጥ ተቋማት የትዝብት ሥራ መጀመራቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን ሂደቱን “እየታዘቡ” ናቸው። ከምንጮች ባሰባሰብነው መረጃ መሠረት፤ ኮሚሽኑ ተቋማቱ የትዝብት ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡለት “በማሳሰብ” ፍቃድ መስጠቱን ተረድተናል። የትዝብት ሥራቸውን ከጀመሩ ተቋማት መካከል አንዳንዶቹ በዚህ ሳምንት “የመጀመሪያ ደረጃ” የትዝብት ሪፖርታቸውን ይፋ ሊያደርጉ እንደሚችሉም የሰማን ሲሆን፤ ኮሚሽኑ የሰጠው ማሳሰቢያ የትኛውም የትዝብት ሪፖርት ከመውጣቱ በፊት እንዲመለከተው የሚጠይቅ መሆኑን ሰምተናል።

የአካታችነት ጥያቄ የቀረበለት የክልል ተወካዮች ጉባኤ

 ቀደም ሲል 211 አባላት እንደሚኖሩት ተነግሮለት የነበረውና ሰነድ የተዘጋጀለት “የክልል ተወካዮች ጉባኤ” የአባላቱ ቁጥር ወደ 284 ከፍ እንዲል መወሰኑን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ “ምክር ቤቱ ያላካተተው የማህበረሰብ ክፍል አለ!” የሚል ጥያቄ ተነስቶበታል። ከ”ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” ለቀረበው “የውክልና” ጥያቄ መልስ የሰጠው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌደሬሽን ተመሳሳዩ ጥያቄ እንደቀረበለት ምንጮች ነግረውናል። የፌደሬሽኑ አመራሮች፣ “ሴቶች እና ወጣቶችን” ጨምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በክልልና በፌደራል ደረጃ ተወክለው የምክር ቤት አባል እንዲሆኑ ሲደረግ፣ “አካል ጉዳተኞች” በምክር ቤቱ ውክልና አላገኙም የሚል ጥያቄ ለኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ማቅረባቸውን ምንጮች ነግረውናል። 

ዋና ኮሚሽነሩ ለፌደሬሽኑ አመራሮች በሰጡት ማብራሪያ “ተመሳሳዩ ጥያቄ ከተለያዩ አቅጣጫዎች” እየቀረበ መሆኑ መጥቀሳቸውን የገለጡት የዋዜማ ምንጮች፤ ፌደሬሽኑ ላቀረበውን ጥያቄ “ተነጋግረን መልስ እንሰጣችኋለን፤ ግዜ ስጡን” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አረጋግጠውልናል።

“የደህንነት ስጋት” አለብን ያሉ “ተመካካሪዎች” 

በምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ ከሚገኙ “ተመካካሪዎች“ መካከል “የደህንነት ስጋት አለብን” ያሉ መኖራቸውን ለመረዳት ችለናል። በተለይም ከአማራ ክልል ተነስተው ለምክክሩ ወደ አዲስ አበባ ካቀኑ “ተመካካሪዎች” መካከል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና የኮሚሽኑ የካሜራ ባለሙያዎች ቀረጻ በሚያከናውኑበት ወቅት፤ “ምቾት” እንደማይሰማቸው የገለጡ አሉ። “በምክክሩ ላይ እየተሳተፍን መሆናችን ከታወቀ የደህንነታችን ጉዳይ ስጋት ውስጥ ይወድቃል” በሚል ለኮሚሽኑ ጥያቄ ያቀረቡ ተመካካሪዎች፤ “ማንነታቸው” እንዲታወቅ በሚያደርግ ቀረጻ ውስጥ እንዳይካተቱ መጠየቃቸውን የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል። 

የኮሚሽኑ ባልደረቦች፤ መሰሉን ጥያቄ ያቀረቡ “ተመካካሪዎች” ባሉባቸው “ስብስብቦች” የሚደረጉ ቀረጻዎች ለመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ እንደማይውሉ መግለጣቸውን ሰምተናል። [ዋዜማ ]