OLA Flag

ዋዜማ- በመንግስትና በ”ኦሮሞ ነፃነት ጦር” መካከል ነገ የሚጀመረውን ድርድር አስመልክቶ አማፂው ባወጣው መግለጫ ያቀረባቸው ሁሉም የድርድር ቅድመ ሁኔታዎች “ተቀባይነት ማግኘቱን” አስታውቋል።


አማፂው የኦሮሞ ነፃነት ጦር እንዳለው ድርድሩ በሶስተኛና ገለልተኛ ወገን አደራዳሪነት እንዲካሄድ ያቀረበው ቅድመ ሁኔታ በመንግስት በኩል “ተቀባይነት አግኝቶ” ወደ ደርድር ለመግባት ወስኗል። ሌሎች ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ አልዘረዘረም።


ትናንት ለትግራዩ የሰላም ድርድር ዕውቅና ለመሰጠት በአዲስ አበባ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እንደተናገሩት የመንግስት ተደራዳሪ ቡድን ከኦነግ ሸኔ ጋር ታንዛኒያ ውስጥ ይፋዊ ድርድር ይጀምራል። የአደራዳሪዎቹን ማንነት ግን ሁለቱም ወገኖች አልገለፁም።


የኦሮሞ ነፃነት ጦር በመግለጫው የቆመለትን አላማ ለማሳካት ጦርነት አማራጭ ነው ብሎ እንደማያምንና ከዚህ በፊትም በተዳጋጋሚ ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ሲገልፅ እንደነበር አውስቷል።


በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚንስትሩ የአማፂ ቡድኑን ሲገልፁ “ኦነግ ሸኔ” ብለው መጥራታቸው እንዳሳዘነው የገለፀው የኦሮሞ ነፃነት ጦር ፣ “ኦነግ ሸኔ” የሚለው ስያሜ የድርጅቱን ዓላማና ጥያቄ ለማንኳሰስ ያለመ መሆኑን ገልጿል።

ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች እንደሰማችው በመንግስትና በአማፂው መካከል ድርድር ለማስጀመር ከታህሳስ ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግ የነበረ ሲሆን ድርድሩን ሲያመቻቹ የነበሩት ታዋቂ የኦሮሞ ምሁራንና ፓለቲከኞች ነበሩ።
በአማፅያኑ በኩል አንድ ወጥ አቋም ስላልነበርና ድርጅቱ በነበረው የተበታተነ መዋቅር ድርድር ለመጀመር አስቸጋሪ ሆኖ መሰንበቱንም ስምተናል።[ዋዜማ]