ዋዜማ- መንግስት ጥቅል ሀገራዊ ምርትን (Gross Domestic Product-GDP) የሚለካበትን ስሌት ለመቀየር ለመቀየር እየተዘጋጀ መሆኑን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል።
መንግስት ከመስከረም ወር 2019 ዓ. ም ጀምሮ በሚተገብረው አዲስ ጥቅል ሀገራዊ ምርት (GDP) ምጣኔ ስሌት መሰረት ኢትዮጵያ አሁን አላት ተብሎ የተሰላው ሀገራዊ ምርት ከሃያ እስከ አርባ በመቶ ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ከወዲሁ የባለሙያዎች ግምት ተቀምጧል። ይህም ሀገሪቱን በአፍሪቃ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ያሰልፋታል ተብሎ ይጠበቃል።
ጥቅል ሀገራዊ ምርት የሚለካበትን ስሌት መቀየር ለምን አስፈለገ ?
የጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ስሌት ዘመንን መቀየር (GDP Rebasing) በመሠረቱ የሚቀየረው ነባሩ የዋጋ መነሻ / ማጣቀሻ ዓመት የአንድን ሀገር ምጣኔ ሀብት አሁናዊ ሁኔታ መግለጽ አይችልም ከሚል ዕሳቤ ነው፡፡
በ2008 ዓ.ም. በገበያው ውስጥ የነበረው የእያንዳንዱ ምርትና አገልግሎት ዋጋ (Price) በ2018 ዓ.ም. ካለው ዋጋ ጋር እጅግ በመራራቁ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ አሁናዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ መግለጽ አይችልም ፡፡ በተጨማሪም በ2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ በስፋት ያልነበሩ ለምሣሌ እንደ ቴሌ ብር፣ ሳፋሪኮም፣ ኮሪደር ልማት ፣ ህዳሴ ግድብና እያደገ የመጣው የወርቅ የውጭ ገቢ ዓይነት የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች በነባሩ የጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ስሌት ውስጥ የተካተቱ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም አሁን ያሉትን አዳዲስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በስሌት ውስጥ ሊያስገባ የሚችል የስሌት መነሻ ዋጋ እንዲሆን 2017 ዓ.ም. ተመርጧል ፡፡
ከሁለት ሳምንታት በፊት የፕላንና ልማት ሚንስትሯ ፍፁም አሰፋ እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ የጥቅል ሀገራዊ ምርቷን ለማሳየት ላለፉት አሥር ዓመታት ስትጠቀም የቆየችው የፈረንጆቹ ዘመን 2015/16 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2008 ዓ.ም.) ሲሆን በአዲሱ ውሳኔ ግን ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ስሌት መነሻ ዓመት የሚሆነው የፈረንጆቹ ዘመን 2024/5 ወይም በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2017 ዓ.ም. ይሆናል ተብሏል፡፡
ለመነሻ የተመረጠው አመት ሀገሪቱ ገበያ መር የውጪ ምንዛሪ ግብይት ተግባራዊ ያደረገችበትና የብርና የዶላር ልዩነት እጅጉን የሰፋበት ወቅት ነው።
‹‹የመረጃ ሉዓላዊት ለፖሊሲ ነፃነት›› በሚል በስብሰባ እና ኤግዚቢሽን ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ‹‹የራሳችን የሆነ ዳታ (መረጃ) ማመንጨት ለኢትዮጵያ አስፈላጊ መሆኑንና የሀገሪቱን ትክክለኛና ተጨባጭ እድገት የሚያሳይ መረጃ እንጂ በውጭ አካላት የሚመነጭ የተውሶ ዳታ (መረጃ) ላይ መመርኮዝ የለብንም›› ብለዋል፡፡
በዚሁ ውሳኔ መሠረት ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት፣ በዚህ የምጣኔ ሀብት ስሌት ማሻሻያ ላይ እየሠራ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር ሥልጠና መስጠት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ይህን እርምጃ በመውሰድ መንግስት ምን ያተርፋል?
ይህ የጥቅል ሀገራዊ ምርት ስሌት መነሻ ዋጋን የመቀየር ውሳኔ ዘርፈ ብዙ አንድምታ አለው፡፡ የመጀመሪያው የሚያስከትለው ዋነኛ ለውጥ የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርት (GDP) አሁን ካለበት ከ20 በመቶ እስከ 40 በመቶ በሚደርስ መጠን በአንድ ጊዜ ከፍ ብሎ አሁን ካለበት 170 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ወደ 200 ቢሊዮን ዶላር ይስፈነጠራል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ያደረገችው የምንዛሬ ለውጥና እሱን ተከትሎ የመጡት የምርትና አገልግሎቶች ዋጋ መናር፣ እና ሌሎችም ምክንያቶች ተደማምረው የኢትዮጵያን ጥቅል ሀገራዊ ምርት በአዲሱ ስሌት መሠረት እጅጉን ከፍ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡
ለምሣሌ ናይጄሪያ በፈረንጅ አቆጣጠር 2014 የምጣኔ ሀብት ስሌቷን (ዓመቱን) ስታስተካክል ኢኮኖሚው ወዲያው በ89 በመቶ ከፍ ብሎ ደቡብ አፍሪካን ገልብጣ የአፍሪካ አንደኛ ኢኮኖሚ እንድትባል አስችሏት ነበር፡፡ በተመሳሳይ ኬንያም ስሌቷን ብቻ በመቀየር ኢኮኖሚዋ በ25 በመቶ ከፍ ብሎ እንዲታይ በማድረግ ከታችኛው መካከለኛ ገቢ ሀገራት ተርታ (Lower middle Income Status) እንድትመደብ በቅታለች፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያም ከመስከረም 2019 ዓ.ም. በኋላ ከፍተኛ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ተብላ በነፍስ ወከፍ ገቢዋም ከፍ ብሎ ከመካከለኛ ገቢ ሀገራት ተርታ ልትመደብ ትችላለች፡፡
ከደረጃና ከዕውቅናው በዘለለ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን እርምጃ እንዲወስድ ያስገደደው ገፊ ምክንያት እንዳለ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ያሰምሩበታል።
ከስሌት ለውጡ በኋላ ኢኮኖሚው በቁጥር ደረጃ እጅግ ስለሚለጠጥ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የመንግሥት ዕዳ ለጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ሲካፈል አሁን ካለበት 50 በመቶ አካባቢ በእጅጉ ያሽቆለቁላል፡፡ ይህም መንግሥትን ለውጭ ዕዳ ሽግሽግ ከመርዳቱም በላይ መንግሥት ተጨማሪ ብድሮችን እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡
ባለሙያዎች ይህን ይላሉ
ሌላው ትልቁ ስጋት በታክስ ዘርፉ ላይ የሚያስከትለው ሸክም ነው፡፡ ከስሌት ለውጡ በኋላ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከታክስ ጋር ያለው ጥመርታ (Tax to GDP ratio) አሁን ካለበት 7 በመቶ አካባቢ ወደ ታች ስለሚወርድ፣ እንዲሁም የአይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ጫና ተጨምሮበት የታክስ ምጣኔውን ከፍ ለማድረግ መንግሥት አሁን ካለበት የባሰ ከፍተኛ የታክስ ጫና በሕዝቡ ላይ ያመጣል፡፡
በብርቱ ብናግባባቸውም ስማቸውን መግለፅ ያልፈቀዱ ሁለት ባለሙያዎች እንደሚሉት መንግሥት የስሌት ዓመት ለውጥን (Rebasing) የሚያደርገው በዋነኛነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቁጥር ደረጃ ግዙፍ መስሎ እንዲታይ ለማድረግ ነው ይላሉ፡፡
‹‹Rebasing›› በረጅም ዓመታት ውስጥ አንዴ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የምትመርጠው ዓመት ወሳኝ ነው፡፡ አዲሱ ስሌት የሚያርፍበት ዓመት ወይ አዲሱ የዋጋ ማጣቀሻ ዓመት የግድ የነገሮች ዋጋ ባንፃራዊነት የተረጋጋበት ወይም የኑሮ ውድነት (Inflation) የወረደበት ዓመት መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ግን አሁን የመረጠችው ከምንዛሬ ለውጥ ማግስት ያለው ዓመትና Inflation የተባባሰበት ዓመትን ነው፡፡ በመሆኑም በአዲሱ ስሌት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብትና ተያያዥ ጥቅል ሀገራዊ ምርቱንና ሀገራዊ ቁጥሮች እጅግ የተጋነኑ ሆነው ይቀርባሉ›› ይላሉ አንድ ረጅም ልምድ ያላቸው የኢኮኖሚ ምሁር፡፡
ሌላኛው ምሁር ደግሞ ስለተጨባጩ ኢኮኖሚ አጥብቀው ተከራክረዋል፡፡ ‹‹እንኳን Rebase ተደርጐ ይቅርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለበት ሁኔታም የሚቀርበው የእድገት አሀዝ የተጋነነ ነው፡፡ መንግሥት በ10.2 በመቶ እያደግን ነው ሲል አይኤምኤፍ በ9.2 በመቶ አድጋችኋል እያለ ነው፡፡ በተጨባጭ ግን ይህ እድገት መሬት ላይ የለም፡፡ ግብርናው ነው፣ አገልግሎት ነው ወይስ ኢንዱስትሪው ነው በዚህ ሁሉ እያደገ ያለው? የት ነው ያለው ይህ እድገት? አይኤምኤፍ ራሱ የመራውን ፕሮግራም እድገት እያመጣ አይደለም ማለት ስለማይፈልግ 9.2 በመቶ ብሎ ሰቅሎታል›› ይላሉ፡፡ [ዋዜማ]
