Yilkal Kefale, Head of Amhara region- FILE

ዋዜማ- የፌደራሉ መንግስት የክልል ልዩ ኀይልን አፍርሶ በሌሎች መዋቅሮች ለማደራጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ በአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞና የፀጥታ ቀውስ አምስተኛ ቀኑን ይዟል።

ዋዜማ ባሰባሰበችው መረጃ ትናንት በአማራ ክልል አስራ አንድ ከተሞች የማዕከላዊውን መንግስት እርምጃ የሚቃወም ሰልፍ ተደርጓል።


በቆቦ ከተማ አቅራቢያ በፀጥታ ኀይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል።
የአማራ ልዩ ኀይል አባላት በቡድን በቡድን ከተለያዩ ካምፖች እየወጡ ወደ ሌሎች ሰዋራ አካባቢዎች መሄዳቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።


የአማራ ክልል መንግስት የልዩ ኀይል አባላት ባሉበት ካምፕ እንዲቆዩ ለማግባባት ከመሪዎቻቸው ጋር ውይይቶች ማድረጉንም ስምተናል።


የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ የልዩ ኀይል አባላትን በክልል ፖሊስ፣ በፌደራል ፖሊስና በመከላከያ እንዲታቀፉና የክልል የልዩ ኀይል አደረጃጀት እንዲፈርስ ከማዕከላዊው መንግስት ጋር አስቀድመው መነጋገራቸውንና መስማማታቸውን ገልፀዋል።

የክልሉ ህዝብ ያለበትን ስጋት እንረዳለን ያሉት ይልቃል፣ የመንግስት ዕርምጃ የሀገሪቱን የወደፊት መረጋጋትና አንድነት ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ወደ ኋላ እንደማይሉ አረጋግጠዋል።


“የአማራ ክልል ልዩ ኀይልን በተለየ መንገድ የሚጎዳ ነገር እና ውሳኔ ለብቻው አልተደረገም” ብለዋል ይልቃል
ካምፕ ጥሎ እየተበተነ ያለው የልዩ ኀይል አባላት ወደ ካምፑ እንዲመለስም ጥሪ አቅርበዋል።


የአማራ ሕዝብ በሁኔታው ቅሬታ ውስጥ መግባቱን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ቅሬታው የመነጨው ለሕዝቡ ትክክለኛ መረጃ ባለመድረሱ ነው ብለዋል፡፡


ማናቸውም ስጋትና ልዩነትን በውይይት ለመፍታት መንግስታቸውም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።

በልዩ ኀይል መልሶ ማደራጀት ሳቢያ የተፈጠረው ቀውስ በዋናነት በተዛባ መረጃና ቅስቀሳ ሳቢያ መሆኑን አስምረውበታል።


በአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑ አስራ አራት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አባላት በበኩላቸው ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ በጉዳዩ ላይ እንዲወያይ የሚጠይቅ ደብዳቤ አስገብተዋል።


የመንግስት አካላት ባለፉት አራት ቀናት ስድስት ያህል መግለጫዎችን ቢሰጡም በአማራ ክልል ያለው ውጥረት ከመርገብ ይልቅ እየተባባሰ መጥቷል።


ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እሁድ ማለዳ በማህበራዊ ገፃቸው ባወጡት መግለጫ “የሚከፈለው ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን” የመንግስት ዕቅድ ተግባራዊ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።


ለዘላቂ የሀገር ጥቅም ሲባል እርምጃውን መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ያስታወሱት ዐቢይ የተዛባ መረጃ አሁን ለተፈጠረው መደነጋገር ምክንያት ሆኗል ብለዋል ።

የመከላከያ ሰራዊት ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ የመከላከያ ሰራዊት ለሀገር አንድነትና ሉዐላዊነት ሲል የተሰጠውን ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ ነው ካሉ በኋላ የልዩ ኀይል መልሶ ማደራጀት የልዩ ኀይል አባላቱን ትጥቅ ማስፈታት ሳይሆን ጥቅምና መብታቸው ተከብሮ በተሻለ ትጥቅ ሀገራቸውን የሚያገለግሉበት ዕድል ነው ሲሉ ለፋና ብሮድካስት ተናግረዋል። [ዋዜማ]