የፀጥታ መዋቅሩ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለማከበር እየተባባሰ የመጣ ችግር መሆኑን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሳይቀር አቤት ቢሉም የፌደራል ፖሊስ ግን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማክበር “ቀይ መስመራችን” ነው ብሏል። የፌደራሉ ፓሊስ ኀላፊዎችን የፓርላማ ምላሽ ተመልክተነዋል። አንብቡት

Demelash Gebremichael, Head of Federal Police

ዋዜማ-የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ባላፉት ዘጠኝ ወራት 26 ቢሊዮን ብር የሚገመት የአገር ሀብት በመመዝበር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን ጉዳይ እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ህገወጥ ንግድ፣ ኮንትሮባንድ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በርካታ አይነት ትልልቅ ወንጀሎች ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የገለጸው ሚየዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም የተቋሙን የዘጠኝ ወር ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅተ ነው፡፡

በዚሁ ሪፖርት ላይ የምክርቤት አባላቱ የፌደራል ፖሊስ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች  በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድቤት መቅረብ ሲኖርባቸው ሳይቀርቡ ከህግ ውጭ ከሳምንት በላይ በእስር ላይ መቆየት፤ የፍርድቤት ትዕዛዝ አለመከበር ለአብነትም ፍርድቤት ቀርበው ፍርድቤቱ ጥፋት አላገኘሁባቸውም ብሎ የሚያሰናብታቸውን ሰዎች ፖሊስ አልፈታም ማለቱንና ይህንንም ቋሚ ኮሚቴው በመስክ ምልከታ ስራው ማረጋገጡን ጠቅሶ ፣ ለምን እንዲህ ሆነ?  ሲል ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይ የፍርድቤት ትዕዛዝ ተግባራዊ አለመደረግን በተመለከተ ከምክርቤቱ እንደቀረበው የፌደራል ፖሊስ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በፍርድቤት እንዲቀርቡ ከታዘዙ 2, 945 ተከሳሽ ውስጥ ፖሊስ ይዞ ወደ ፍርድቤት ማቅረብ የቻለው 1,169 ወይንም የተጠየቀውን 39 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ነው፡፡

ከምክርቤቱ የተነሳውን ጥያቄ አስመልከተው ማብራሪያ የሰጡት  ዋና ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካዔል ፤ የፍርድ ቤት ውሳኔ አለመፈጸምን በተመለከተ ሲመልሱ ‹‹የምጠረጥረው ስህተት እንዳይሆን ነው፤ እኛም መብት አለን፤ ተጠርጣሪው አደጋ ያደርሳል ብለን ስናስብ ነገር ግን ፍርድቤት ተጠርጣሪውን ሊለቅብን  ሲል በየደረጃው እየቀረብን እናመለክታለን፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ ተጠርጣሪው አልተለቀቀም ተብሎ የሚቀርብ ከሆነ ደግሞ የህግ አካሄድ ስላለ ህጉን ማየት ነው ያሉት ኮሚሽነር ደመላሽ ፤ አሁን እየታየ ያለው ፍርድቤት ዋስትና ከፈቀደ ለምን አትለቁም የሚል ነው፤ ነገር ግን መልቀቅ በሌለብን ቦታ ላይ  የህግ ሂደቱን እየተከተልን የምንሰራቸው ስራዎች ስላለሉ ህጉ በደንብ ሊታይ ይገባል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የህግ የበላይነት ይከበር፤ ይህ አገር ሰላም ይኑረው ከተባለ ሀላፊነቱ የምክርቤቱ፣ የፍርድቤቱ፤የህዝቡ፤ የፖሊሱ ፤ የሰብዓዊ መብት ውስጥ ያሉትም ሆነ የሌላውም አካል መሆኑን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ‹‹በጣም የምንጠነቀቀውና እያወቅንና ቀጥሎ ችግር እንደሚፈጥር እየታወቀም ቢሆን የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ማክበር ላይ ነው›› ብለዋል፡፡ 

የፍርድቤት ትእዛዝ መከበር ቀይ መስመር እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነር ደመላሽ፤ ፍርድቤቶች ግልጽ የሆነ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉ ጋዜጠኞች ጋር በተገናኘ፤ አንዱና ትልቁ ንትርክ የተለያዩ ሃይሎች አደረጃጀቶችን  በመጠቀም በአገር ወስጥና ከአገር ውጭ ተቀናጅተው ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ እያገኙ፤ አንዳንዶቹም የገቢ ምንጭ አድርገውት የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ወደ ፍርድቤት ሲቀርቡ የፍትህ አካላት ከእኛ ጎን ሊቆሙና ሁኔታው ስርዓት እንዲይዝ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል ኮሚሽነር ደመላሽ፡፡

በመሆሙም በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍርድቤቶች ጋር የጋራ መድረክ ቢፈጠር ካልሆነ ደግሞ ቋሚ ኮሚቴው ለፍርድ ቤቶች አጽንኦት ሰጥቶ በጋራ መቆም ያለብን ይመስለኛል ብለዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 26 ቢሊዮን ብር የመንግስትና የህዝብ ሃብት የመዘበሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ሃብቱን የማዳን ስራ እየሰራና ምርመራ እካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተቋማቸው የሪፎርም ስራ ካካሄደ ወዲህ ‹‹ፍርድ-ቤት በየትኛውም ጊዜ በደብዳቤም ይሁን በሌላ መንገድ የወሰንኩት ውሳኔ አልተከበረልኝም በሚል በእኛ ላይ ያቀረበልን አቤቱታም ይሁን ቅሬታ የለም›› ብለዋል፡፡

ፍርድቤቶች አካባቢ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ችግር አለ ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ፌደራል ፖሊስ ሰበር ችሎት ድረስ በመሄድ የተለያዩ ጉዳዮችን ይዞ መጠየቅ እንደሚችልና የምርመራ ሂደቱን በተለያየ ደረጃ ለማስኬድ ከጊዜ ቀጠሮ ጀምሮ እስከ ሰበር ችሎት ድርስ ይግባኝ ለመጠየቅ ህጉ እንደሚፈቅድላቸው ተናግረዋል፡፡ 

‹‹ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ላይ ምርመራ እያካሄድን ነው፤ ከዚህ አንጻር ተፈላጊ የሆኑ ሰዎች ዛሬ ወጥተው ነገ የማይገኙበት ሁኔታ ስለሚፈጠር እኛ ደረጃውን ጠብቀን እስከሰበር ችሎት ድረስ ይግባኝ እየጠበቅን ጉዳዩን ለማየት በሚል የምንከተለው አካሄድ አለ፤ ነገር ግን እኔ እስከማቀውቀው ድርስ እስካሁን ትዕዛዜ አልተከበረም በሚል ከፍርድቤት የመጣ ጉዳይ የለም›› ብለዋል፡፡

ኮሚሽነር ዘላለም በቁጥጥር ስር ዋሉ ጋዜጠኞችን በተመለከተ፤ እነዚህ አካላት ይህን መንግስትና ህገመንገስት በሃይል ለመጣል ትላልቅ ዶክሜንቶች አዘጋጅተው ፤ በትላልቅ ክንፎችና መዋቅር ተደራጂተው በሚዲያና በጋዜጠኝነት ሽፋን ፍቃድ ወስደው የሚሰሩ አክቲቪስት ነን ባዮች ናቸው ብለዋል፡፡ 

ከአንድ ወር በፊት የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ወደ ተመረጡበት አካባቢ በመሄድ ህዝብ አወያይተው ከተመለሱ በኋላ ከህዝብ የተነሱ ጥቄዎችን በተመለከተ ከመንግስት አስፈጻሚ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት የጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት  የፍርድቤት ውሳኔ አለመከበር አብይ ችግር መሆኑን አንስተው ከፓርላማው ጭምር እገዛ እንደሚፈልጉ መድረክ ላይ ጠይቀው ነበር፡፡ [ዋዜማ]