ዋዜማ- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሁለት ሳምንታት በፊት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደን የስልጣን ጊዜ ለ 1 አመት ማራዘማቸውን ተከትሎ ፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሹመቱን እንደማይቀበለው እና ከጦርነቱ በፊት የነበረውን መንግስት ለመመለስ መወሰኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

በ2012 ዓ.ም የነበረውን መንግስታዊ መዋቅር እና ምክር ቤቶች ለመመለስም ባለፉት አስር ቀናት ዉስጥ ከድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጀምሮ፣ የማእከላዊ ኮሚቴ፣ የዞን፣ የወረዳ እና የከተማ ምክር ቤቶችን ስብሰባ እያካሄደ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም፤ የህወሃት አመራሮች በየደረጃው ያሉ ካድሬዎችን፣ የቀድሞ ሚሊሻዎችን፣ በጡረታ የተሰናበቱ ወታደሮችን፣ የአርሶአደሮች ማህበራትን እንዲሁም የሴቶች እና የወጣቶች ማህበራትን ስብሰባ በመጥራት ውሳኔውን የተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን ዋዜማ በስብሰባው ከተካፈሉ ምንጮች አረጋግጣለች፡፡

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በመጪው፤ ሚያዚያ 23 ቀን፤ 2018 ዓ.ም የክልሉን ምክር ቤት ስብሰባ እንደሚያካሂድ እና አዲስ ፕሬዚደንት ለመምረጥ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ዋዜማ ለጉዳይ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ሰምታለች፡፡

አዲሱ ፕሬዚደንት ማን ሊሆኑ እንደሚችሉ በእርግጠኝነት መናገር ባይችሉም፤ የድርጅቱ ሊቀ-መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር)፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ አማኑኤል አሰፋ ወይም በፕሪቶሪያው ስምምነት ወቅት አንዱ ተደራዳሪ የነበሩት ፍስሃ ሃፍተጽዮን (ዶ/ር) ሊሆኑ እንደሚችሉ ምንጫችን ግምታቸውን ነግረውናል፡፡

ከሰኞ ጀምሮ ለመጪው አርብ የምክር ቤት ጉባዔና ለምርጫው የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን፣ የሕወሓትን ድርጅታዊ አቋም በተመለከተ ለበታች መዋቅር በሰፊው ማብራሪያ እየተሰጠ መሆኑን ቢያንስ ከሶስት የትግራይ ከተሞች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሙሉ በሙሉ ፈርሶ በቀድሞው መንግስት ከተተካ በኋላ ክልሉ በጊዜያዊነት በኮማንድ ፖስት እንዲመራ የማድረግ እቅድ መኖሩንም ሰምተናል፡፡ የቀድሞው መንግስት ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እስከሚገባ ድረስ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚደንት በኩል የሚሰጡ መመሪያዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ቢወሰንም፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግን መደበኛ ስራቸውን እንዲቀጥሉ መመሪያ መውረዱን ነው የገለጹት፡፡

ድርጅቱ ከፌደራሉ መንግስት ጋር የገባበትን ውጥረት ተከትሎም፤ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ በሰሜኑ ጦርነት የተሳተፉ እና ትጥቅ የፈቱ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ምድባቸው እንዲመለሱ ጥሪ ማድረጉን የገለጹት የዋዜማ ምንጮች፤ በርካቶች ወደ ቀድሞው ምድባቸው መመለሳቸውን ነግረውናል፡፡

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚደንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ፤ የህወሃትን እንቅስቃሴ እንደሚቃወሙት በመግለጽ፤ ‹‹አደገኛ መዘዝ ያመጣል›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በጉዳዩ ላይ የሕወሓትን አስተያየት ለማካተት ያለመታከት ያደረግነው ጥረት ዘለፋ ባዘለ እምቢታ ሳይሳካ ቀርቷል።

በትግራይና በፌደራል መንግስቱ መካከል የተካረረ አለመግባባት መፈጠሩንና በራሳቸው በትግራይ ፖለቲካዊና  ወታደራዊ ቡድኖች መካከል የበረታ ክፍፍል መከሰቱን ተከትሎ ሕወሓት አዲስ ወታደራዊ አደረጃጀትንና የፖለቲካ አስተዳደር መዋቅር መዘርጋቱን ከሶስት ሳምንት በፊት ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ ተገንዝባለች።

ከተደረጉት አዳዲስ አደረጃጀቶች መካከል የትግራይ ተዋጊ ሀይሎች (TDF) የተደራጁበት የዕዝ ሰንሰለት ይገኝበታል። አዲሱ አወቃቀር ሕወሓት በማናቸውም መንገድ በክልሉ ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ እንዲሆን የሚያስችለው መሆኑንም ምንጮቻችን ነግረውናል።

የትግራይ ተዋጊ ሀይሎች (TDF)፤ በተለይም ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ የታችኛውን እርከን ያማከለ መዋቅራዊ ለውጥ፤ የከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ሽግሽግ እና የሰራዊት ድልድል ስራዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ከፌደራሉ መንግስት እስካሁን በይፋ የተሰጠ አስተያየትና መግለጫ የለም። [ዋዜማ]