Takele Uma , Minster of Mine and Petroleum-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- እንደ ኦፓል ፣ ሳፋየርና ኤመራልድ አይነት የከበሩ ማዕድናት ለውጭ ገበያ ሲቀርቡ የተወሰነ መጠናቸው እሴት እንዲጨመርበት የሚያስገድደው ህግ መነሳቱን ተከትሎ የማዕድን የገበያ ሰንሰለቱ መዛባት ገጥሞታል።


ማዕድናት በማስዋብና ጌጣጌጦችን በመስራት ወደ ገበያ ያቀርቡ የነበሩ የንግድ ተቋማት ይህ የመንግስት ውሳኔ በስራችን ላይ ያልተጠበቀ ኪሳራ ያደርስብናል ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።


ቀድሞ የነበረው ህግ ማንኛውም የከበሩ ማዕድናትን የሚልኩ ኩባንያዎች ከሚልኩት የከበሩ ድንጋዮች መካከል 20 በመቶውን አስውበው እሴት በመጨመርና 80 በመቶውን ደግሞ በጥሬው እንዲልኩ የሚያዝ ነበር።


ባለፈው ወር የወጣው አዲስ ሕግ የቀደመውን ሕግ በመሻር የከበሩ የጌጣጌጥ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ማዕድናቱን ያለ ምንም ገደብ በጥሬው ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ፈቅዷል።


የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ታከለ ኡማም በወቅቱ ህጉ ስለመሻሻሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩ ሲሆን ማዕድናቱ የሚሸጡበት ዋጋ ማሻሻያ እንዲረግበት መወሰኑንም ጠቁመዋል።


 ይህን ተከትሎም የኢንዱስትሪ ባለቤቶች በከበሩ ማዕድናት የውጭ ገበያ ላይ የተደረገው የህግ ለውጥ ኢትዮጵያ ከማዕድን ማግኘት ያለባትን ጥቅም የሚያሳጣ እና የከበሩ ማዕድናትን በማስዋብና ጌጣጌጥ ለመስራት ኢንዱስትሪ ያቋቋምን ኩባንያዎችን “የሚጎዳ ነው” በማለት ለዋዜማ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።


የኢንዱስትሪ ባለቤቶቹ እንደሚሉት የከበሩ ድንጋዮች ላይ እሴት ጨምረን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ኩባንያ ያቋቋምነው በማዕድናቱ ላይ እሴት መጨመርን የሚያግዝ ህግ እንዳለ ተማምነው እንደሆነ ይናገራሉ። አሁን የተደረገው የሕግ ለውጥ ማዕድናቱን ለማስዋብና ጌጣጌጥ ለመስራት ላቋቋምናቸው ኢንዱስትሪዎች ግብአት የሚሆኑ ጥሬ የከበሩ ድንጋዮችን አቅራቢዎቻችንን ያሳጣናል ሲሉ ለዋዜማ ተናግረዋል።


በዚህና ተያያዥ ምክን ያቶች በዘርፉ ለመሰማራት ያወጣነውን ሀብት ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ ያስከትልብናል የሚል ስጋት አላቸው። በኢትዮጵያ እንደ ኦፓል ያሉ ማዕድናትን ከማስዋብ አንስቶ ጌጣጌጥ ሰርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ የተሰማሩ 200 ኩባንያዎች አሉ። 


አዲሱ ህግም ለአነስተኛ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ሲባል ብዙ ገቢ ሊገኝባቸው የሚችሉ የኢትዮጵያ ሀብቶችን በገፍ እያወጡ ለሌሎች ሀገራት መስጠትን የሚያበረታታ መሆኑን ያነሱልን አንዱ የከበሩ ማዕድናት ጌጣጌጥ መስሪያ ኩባንያ ባለቤት ለዚህ መከራከሪያቸው ኦፓል የተሰኘውን ማዕድን በምሳሌነት ያቀርባሉ። ኦፓል የተሰኘው የከበረ ማእድን ምንም ጌጣጌጥ ሳይሰራበት ተጠርቦና ተውቦ ብቻ አንድ ኪሎ ግራሙ ከ10 ሺህ እስከ 40 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በሆነ ዋጋ ለውጭ ገበያ እንደሚሸጥ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የመሸጫ ዋጋን በማጣቀስ ያስረዳሉ። 40 ሺህ ዶላር የሚሸጠው አንደኛ ደረጃው የተዋበ ኦፓል ሲሆን ሁለተኛ ደረጃው 25 ሺህ ዶላር ፣ ሶስተኛ ደረጃው ደግሞ 10 ሺህ ዶላር ይሸጣል። አንድ ኪሎ ግራም የተዋበ ኦፓል ለመስራትም አምስት ኪሎ ግራም ጥሬ ኦፓል ያስፈልጋል። በዚህ ሂደት ውስጥም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ከማምጣት ባለፈ ለበርካታ ሰዎች ስራን መፍጠር ይቻላል።


ሳፋየርና ኤመራልድም በኢንዱስትሪ ሲያልፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ማመንጨት የሚችሉ ናቸው። ምንም አይነት የማስዋብ ስራ ያልተሰራባቸው ኦፓልና ሌሎች ማዕድናት ግን ከ650 ዶላር ጀምሮ ባለ አነስተኛ ዋጋ ነው በኪሎ ግራም እንደሚሸጡ ባለሀብቱ አስረድተውናል።


የከበሩ ማዕድናትን በጥሬው ለውጭ ገበያ ማቅረብ ኢትዮጵያን ከሀብቷ ተጠቃሚ እንዳትሆን እንዳደረጋት የሚጠቅሱት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላኛው የዘርፉ ባለሀብት ከሰባትና ስምንት አመታት በፊት በየአመቱ ከ10 ሺህ ቶን በላይ ኦፓል በጥሬው ህንድ ተልኮ ብዙ ገቢ እና የስራ እድል ስትፈጥርበት ኢትዮጵያ ግን ከሁለቱም ሳትሆን ቀርታለች ብለዋል።


ኢትዮጵያ በወቅቱ ከ10 ሚሊየን ዶላር ያነሰ ገቢ ነበር የምታገኘው። ሀገሪቱ ከሀብቷ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝም ከጥቂት አመታት በፊት የከበሩ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶች ከሚልኩት ውስጥ 50 በመቶውን እሴት ጨምረው ቀሪውን ደግሞ በጥሬው እንዲልኩ ይገደዱ ነበር። ቀስ ብሎም ላኪዎች ከሚልኩት ማዕድን ውስጥ እሴት እንዲጨምሩ የሚገደዱት ከ5ዐ በመቶ ወደ 20 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጎ ቆይቷል። አሁን ደግሞ እሴት መጨመርን የሚያስገድደው ህግ ሙሉ በሙሉ መቅረቱ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ይጎዳል ይላሉ ባለሀብቶቹ።


የማዕድን ዘርፍ ለህገ ወጥ ንግድና ሀብትን ከሀገር ለማሸሽ በስፋት መጠቀሚያ ሲሆን የቆየ ዘርፍ ነው


የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ሀላፊዎች በተቋሙ ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በኩል በሰጡት ምላሽ የከበሩ ማዕድናትን አስውቦ መላክን አስመልክቶ የነበረው አስገዳጅ ህግ መቅረቱ የተባለውን ጉዳት ያደርሳል ብሎ ሚኒስቴሩ እንደማያምን ገልጿል።
አስገዳጅ ህጉን ማስቀረት ያስፈለገውም አንዳንድ ኩባንያዎች የተከማቸ ኦፓልና ሌሎች ማእድናትን ይዘው እሴት ይጨመርበት የተባለውን መጠን ማሟላት ባለመቻላቸው ማእድናቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተቸግረናል በማለታቸው እንደሆነም መስሪያቤቱ ለዋዜማ ገልጿል።


ማእድናቱን አስውቦ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚጠቅመው ላኪውንም ስለሆነ የሚበረታታ መሆኑን ያነሳው ሚኒስቴሩ ገደቡ መነሳቱ የሚባለውን ያክል ጉዳት የሚፈጥር ከሆነም ጉዳዩ ለውይይት ክፍት ነው ብሏል።


ኢትዮጵያ በዚህ አመት ከማዕድን የወጪ ንግድ 682 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያገኘች ሲሆን ከዚህ ውስጥ 671 ሚሊየን ዶላሩ ከወርቅ የተገኘ ሲሆን ቀሪው ከከበሩ ድንጋዮችና ሌሎች ማዕድናት የተገኘ ነው።አጠቃላይ የማዕድን ሽያጭ ካለፈው አመት የ207 ሚሊየን ዶላር እድገት አሳይቷል።  [ዋዜማ ራዲዮ]