Mekele University- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በትግራይ ክልል የባንክ ሂሳባቸው የተዘጋባቸው ህንዳውያንን ሂሳብ ለማስከፈት በአዲስ አበባ የሚገኘው የህንድ ኤምባሲ ጥያቄ ማቅረቡን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።።

የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጃለሁ ብሎ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም መቀሌን ጨምሮ የትግራይ ክልልን ለቆ ከወጣ በኋላ በትግራይ ክልል የባንክ ሂሳብ ያላቸው ሰዎችን እና ድርጅቶች ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ መደረጉ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም በትግራይ ክልል በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲያስተምሩ የነበሩ ህንዳውያንም የባንክ ሂሳብም እንዳይንቀሳቀስ አብሮ ታግዷል።

ቁጥራቸው ከ50 በላይ የሆኑት ህንዳውያን ከትግራይ ክልል ወጥተው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ በአዲስ አበባ የሚገኘው የህንድ ኤምባሲ ማረፊያ ሆቴል እና የምግብ ወጪ ተሸፍኖላቸው ጉዳያቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።።

ዋዜማ እጅ በደረሰ የደብዳቤ መረጃ መሰረት ኤምባሲው ለሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፃፈው ደብዳቤ በትግራይ ክልል የሚገኘው የህንዳውያኑ የሂሳብ ደብተር እንዲከፈት ጠይቋል። በተጨማሪም በተለያዩ የትግራይ ዩንቨርሲቲዎች ሲያስተምሩ የነበሩት ሕንዳውያኑ የሰኔ እና ሃምሌ ደሞዛቸውም እንዲከፈላቸው ጭምር የሕንድ ኤምባሲ በደብዳቤው ጠይቌል።

መንግስት የትግራይ ክልልን ለቆ ከወጣ በኋላ በክልሉ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎችን ከብዙ ጥረት በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መደረጉ ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]