Ethiopian Opal

ዋዜማ ራዲዮ- ኦፓል የተሰኘው ውድ ዋጋ የሚያወጣው የጌጣጌጥ ማዕድን (የከበረ ድንጋይ) በአዲስ አበባ ባልተለመ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ በህገ ወጥ መንገድ እየተቸበቸበ መሆኑን ዋዜማ ሬድዮ ከምንጮቿ ሰምታለች። በከተማው እየታየ ያለው ህገ ወጥ የኦፓል ንግድ በህገ ወጥ መንገድ ሀብትን ከሀገር የማሸሽ አንዱ ስልት መሆኑን ከተለያዩ ምንጮች መረዳት ችለናል።
     
በስፋት እየተቸበቸበ ያለው ኦፓል ከወሎ የመጣው ሲሆን በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ግለሰቦች ማእድኑን እየገዙ በኮንትባንድ በማሸሽ ላይ መሆናቸውንም ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።የኦፓል ማእድን ህገ ወጥ ንግዱ ከሚካሄድባቸው ስፍራዎችም ውስጥ በዋነኝነትም የሁለቱን የግብይት ቦታዎች የሰማን ሲሆን ሌላ ሶስተኛ ግለሰብም ለጊዜው ባልተገለጸ ስፍራ ግብይቱን እንደሚፈጽም ባደረግነው ክትትል ለመረዳት ችለናል።

አንደኛው ግለሰብ ከቦሌ ወደ መገናኛ መሄጃ ባለ አንድ ቢሮው የወሎ ኦፓልን እየገዛ በጎረቤት አገር ሶማሊያ ዜጎች አጋዥነት ማእድኑን በዚያው በኩል እንደሚያወጣው ተረድተናል።ይህ ግለሰብ ኦፓል ካሉት ሶስት የጥራት ደረጃዎች ማለትም ከፍተኛ ደረጃ (high grade) : መካከለኛ ደረጃ (medium grade) እና ዝቅተኛ ደረጃ (low grade) ውስጥ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚመደቡትን በስፋት በመግዛት ላይ ሲሆን እያንዳንዱን ኪሎ እስከ 20 ሺህ ብር ነው የሚገዛው።

ሌላኛው ደግሞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ መንገድ ላይ ባለው ቢሮው ከፍተኛ ጥራት ያለውን ኦፓል በኪሎ እስከ 500 ሺህ ብር የሚገዛ ሲሆን በቀን ውስጥም በአማካይ አምስት ኪሎ ባለ ከፍተኛ ደረጃውን ኦፓል ይገዛል። እነዚህ ግለሰቦች በዚህ መልኩ ከወሎ ኦፓልን ከሚያመጡ ሰዎች ላይ የከበረ ማእድኑን ከገዙ በሁዋላ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር እያስወጡት ነው። በዚህ ሂደትም ሀገሪቱ ከግብርና ከሀገር ውጭ ከወጣው ማእድን ማግኘት ያለባትን በሚሊየን ዶላሮች የውጭ ምንዛሬ እያጣች ነው። እንደ አሰራሩ ከሆነ ይህ ማእድን ከሀገር ወጥቶ ሲሸጥ ህጋዊ ፍቃድ ባላቸው አዘዋዋሪና ላኪዎች በኩል በማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እውቅና መሸጥ ነበረበት ።እስካሁን ባለው ሂደት ግን መንግስት ስለጉዳዩ የሚገባውን ያህል ትኩረት አልሰጠውም ወይም የችግሩን ስፋት መረዳት አልቻለም።

ያነጋገርናቸው የማዕድን ሚኒስቴር ባለሙያዎች ዘርፉ ወትሮም ስፋት ያለው ህገ ወጥ ንግድ የሚፈፀምበት በመሆኑና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በራሱ አቅም ማድረግ የሚችለው ውሱን መሆኑን አስረድተውናል። ይሁንና ከህግ አካላት ጋር ተነጋግሮ ለመስራት የተደረጉ ሙከራዎች ፍሬያማ እንዳልነበሩ ይናገራሉ።

ዋዜማ ሬድዮ እንደሰማችው ከሆነ የአሁኑ የኦፓል ህገ ወጥ ንግድ ከሌላውም ጊዜ ለየት ያለ ነው። የዚህም አንዱ ማሳያ የከበረ ድንጋዩን ለመግዛት ህገ ወጥ ነጋዴዎቹ እያወጡት ያለው ገንዘብ ነው። ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በሁዋላ እንደ ኦፓል ያሉ የከበሩ ማእድናት ፍላጎት በአለም አቀፍ ደረጃ ዝቅ ስላለ ዋጋቸውም ወርዷል። ለአብነት የኮሮና ቫይረስ የኢኮኖሚ ስጋት ከፈጠረ ጀምሮ በጥራቱ አንደኛ ደረጃ የሆነው ኦፓል ዋጋው በኪሎ ግራም በመቶ ሺህ ብሮች ወርዶ : በግራም 300 ብር በኪሎ ግራም ደግሞ እስከ 300 ሺህ ብር ድረስ ነበር የሚሸጠው። ታድያ የኮሮና ቫይረስ ተጽእኖ ተባብሶ በቀጠለበት ጊዜ የማዕድኑ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ቅድመ ኮሮና ወደ ነበረበት ዋጋ በላይ መገኘቱ ግራ አጋቢ ሆኗል።

ይህ የተጋነነ የኦፓል ማዕድን ግብይት በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ የማሸሽ አቋራጭ መንገድ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች አጥብቀው ያስረዳሉ።

እንደ ኦፓል ያሉ የከበሩ ማዕድናት ከዚህ ቀደምም ከኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን በህገ ወጥ መንገድ ሲወጡ ነበር።በተለይም በህንዳውያን ነጋዴዎች በስፋት የተዘረፈ ሀብት ነው። በዚህም ማእድኑ በራሱ የሚያስገኘውን የውጭ ምንዛሬ ሀገሪቱ አጥታለች። እንዲሁም የከበረ ድንጋዩን ከጥሬነት አንስቶ በመጥረብና ጌጣጌጥ በመስራት ሂደት ውስጥ ሊፈጠር የሚችል ከፍተኛ የስራ እድልም ታጥቷል። አውስራሊያና ሜክሲኮ ከበርካታ አመታት በሁዋላ የኦፓልን ማእድን በአለም ገበያ ከተጠቀሙበት በሁዋላ ተፈላጊ ሆኖ የመጣው የኢትዮጵያ ኦፓል ነው። ሀገሪቱ ነጭ ኦፓልና በአይነቱ ለየት ያለው ቀዩ የአፋር ኦፓልም ባለቤት ነች። ሆኖም በዘርፉ ላይ ባለ ሰፊ ህገ ወጥነት የሚታሰበውን ጥቅም ማግኘት አልቻለችም። ማእድኑ ትንሽ እሴት ቢጨመርበት ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ ቢታወቅም በጥሬ ደረጃ በገፍ ወደ ውጭ ወጥቶ የሌሎች መጠቀሚያ ሆኗል። [ዋዜማ ራዲዮ]