ዋዜማ- በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 17ኛ ቀን ውሎ የክልል ተወካዮች ጉባኤ አባላት ተመርጠዋል። ጉባኤው በርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን የተዘጋጁ ውሳኔዎች ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ከማለፋቸው በፊት የምክረ ሀሳቦችን ተቀባይነት የማረጋገጥ ስልጣን የተሰጠው መሆኑን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን “የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት” በሚል ርዕስ ያዘጋጀውና ዋዜማ የተመለከተችው ሰነድ ይጠቁማል። ጉባኤው 211 አባላት እንደሚኖሩት ኮሚሽኑ ቀደም ብሎ አሳውቆ የነበረ ቢሆንም፤ የተለያዩ አካላት “በጉባኤው መካተት አለብን” ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት፤ የጉባኤው አባላት 336 እንዲሆኑ መወሰኑን ሰምተናል። ኮሚሽኑ ይህንን ቢወስንም አሁንም በጉባኤው አልተወከልንም የሚሉ ጥያቄዎች መቀጠላቸውንም ምንጮች ነግረውናል።

በክልሎች፤እነማን የጉባኤው አባል ሆኑ?

12ቱ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በጉባኤው እያንዳንዳቸው 22 መቀመጫዎችን አግኝተዋል። እነዚህ 22 መቀመጫዎች ደግሞ ለዘጠኝ ባለድርሻ አካላት ተከፋፍለዋል። የክልል ወይም የከተማ አስተዳደር መንግስት አራት መቀመጫወች የተመደቡለት ሲሆን፤ የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች የወከሏቸውን የምክክሩ አካል የሆኑ ባለስልጣናት በደብዳቤ ለኮሚሽኑ እንዲያሳውቁ መደረጉን ምንጮች ነግረውናል።  

የሃይማኖት ተቋማት አምስት መቀመጫዎችን ያገኙ ሲሆን፤ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባል የሆኑት አምስቱ ሃይማኖቶች ማለትም፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ካቶሎካዊት ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል እና የኢትዮጵያ የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን፤ እያንዳንዳቸው አንድ መቀመጫ አግኝተዋል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች አራት መቀመጫዎች የተመደቡላቸው ሲሆን፤ በክልሎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በራሳቸው ባደረጉት የምርጫ ሂደት ተወካዮችን እንዲመድቡ ተደርጓል። የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ደግሞ ሶስት መቀመጫዎችን ያገኙ ሲሆን፤ አንዱ መቀመጫ ለአካል ጉዳተኞች፣ ቀሪ ሁለት መቀመጫዎች ደግሞ ለሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ተመድበዋል። “ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” ሁለት መቀመጫዎችን ያገኙ ሲሆን፣ የመምህራን ማህበር፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ሴቶች እና ወጣቶች እያንዳንዳቸው አንድ መቀመጫ አግኝተዋል።   

በፌደራል ውክልና እነማን መቀመጫ አገኙ?

የፌደራል መንግስት አራት መቀመጫዎችን ያገኘ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ አራት የመንግስት ተወካዮችን ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸውን ሰምተናል። ሦስቱ የመንግስት አካላት ማለትም፤ ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ ሦስቱን መቀመጫዎች እንዲይዙ መደረጉን የገለጡልን ምንጮች፤ አራተኛው መቀመጫ ደግሞ ለጸጥታ ኃይሎች ተወካይ መመደቡን ጠቁመዋል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች አራት፣ የሃይማኖት ተቋማት (ዋቄ ፈና እምነትን ጨምሮ) ስድስት፣ “ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” ሦስት፣ የመምህራን ማህበር አንድ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አንድ፣ ሴቶች አንድ እና ወጣቶች አንድ መቀመጫ ያገኙ ሲሆን፤ ለማን እንደተሰጠ ያላወቅነውን ሌላ አንድ መቀመጫን ጨምሮ፤ በፌደራል ደረጃ 22 መቀመጫዎች ተመድበዋል።

በ”ልዩሁኔታ” የተሰጡ ስድስት መቀመጫዎች

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ በጉባኤው አባላት ምርጫ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፤ ከ12ቱ ክልሎች፣ ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እና ከፌደራል ባለድርሻዎች ከእያንዳንዳቸው 22 ተወካዮችን በመውሰድ 330 አባላት ያሉት ጉባኤ መቋቋሙን ገልጠው የነበረ ቢሆንም፤ ዋና ኮሚሽነሩ መግለጫ ከሰጡ ከሰዓታት በኋላ ኮሚሽኑ በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ የጉባኤው አባላት ቁጥር 336 መሆኑን አስታውቋል። ስድስቱ ተጨማሪ የጉባኤ አባላት እነማን እንደሆኑ ምንጮችን የጠየቀችው ዋዜማም፤ በልዩ ሁኔታ መቀመጫ የተሰጣቸው ተመካካሪዎች መኖራቸውን ተረድታለች።

በልዩ ሁኔታ መቀመጫ ካገኙ ተመካካሪዎች መካከል “ትጥቅ ፈትተው” በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ወገኖች እንደሚገኙበት ሰምተናል። “የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት” በጉባኤው መቀመጫ ካገኙ አካላት መካከል አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ምንጫችን፤ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ መቀመጫውን ያገኙ መሆናቸውን ገልጠዋል። በመሰል ሁኔታ መቀመጫ ያገኙ ሌሎች አካላት መኖራቸውንም ዋዜማ ሰምታለች። 

የምርጫ ሂደቱን የተቃወሙት ፓርቲዎች

ኮሚሽኑ አራቱ ፓርቲዎች በምን አይነት መስፈርት መመረጥ እንዳለባቸው ያስቀመጠው ነገር አለመኖሩን የገለጡት ምንጫችን፤ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤታቸው በኩል ተወካዮቻቸውን እንዲያሳውቁ መጠየቁን ጠቁመዋል። ይሁንና ጥቂት በማይባሉ ክልሎች የፓርቲ ተወካዮች የተመረጡበት ሂደት ጥያቄ ማስነሳቱን ሰምተናል። የፓርቲ ተወካዮችን ለመምረጥ የተካሄደው እንቅስቃሴ ላይ ቅሬታ ያላቸው ፓርቲዎችም ለኮሚሽኑ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን ዋዜማ ሰምታለች። የክልሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢዎች በራሳቸው ፍላጎት የፓርቲ ተወካዮችን የመረጡበትና ግልጽ የምርጫ ሥርዓት ያልተከናወነበት ሁኔታ መኖሩን ያነሱ ፓርቲዎች፤ የፓርቲ ተወካዮች ዳግም እንዲመረጡ መጠየቃቸውን ምንጮች ገልጠዋል።  

የብልጽግና ፓርቲ ውክልና ጉዳይ

ገዥው ብልጽግና ፓርቲ በክልሎች መንግስታትና በፌደራል መንግስት በኩል ውክልና አግኝቷል የሚል አስተያየት የሰነዘሩ ፓርቲዎች፤ በክልሎችና በፌደራል ደረጃ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጠውን ኮታ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች  እንዲተው መጠየቃቸውን ምንጮች ገልጠዋል። ይሁንና ብልጽግና እንደ ሌሎች ፓርቲዎች፤ በምርጫ ሂደቱ መሳተፉን ሰምተናል። በዚህም ብልጽግና ፓርቲ በገዢነቱ በክልሎችና በፌደራል በድምሩ ካገኛቸው 60 መቀመጫዎች ተጨማሪ የሚሆኑ ሌሎች መቀመጫዎችን በፓርቲዎች ውክልና እንዳገኘ ተረጋግጧል። 

የዜግነታቸው ጉዳይ ያወዛገበው ተመራጭ

በፌደራል ደረጃ በተካሄደው የክልል ተወካዮች ጉባኤ አባላት ምርጫ፤ “ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን” በመወከል ከተመረጡ ተመካካሪዎች መካከል አንዱ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም ናቸው። ፕሮፌሰሩ የኢትዮጵያ ዜግነት የላቸውም የሚል መከራከሪያ ያቀረቡ ተመካካሪዎች፤ ለኮሚሽኑ ቅሬታ ማቅረባቸውን ዋዜማ ሰምታለች። ቅሬታ አቅራቢዎች፤ “ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው ሰዎች በምክክር ሂደቱ ሊሳተፉ አይገባም፤ ኮሚሽኑ በአፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት።” ማለታቸውንም ምንጮች ገልጠዋል። ኮሚሽኑ የተመራጩን ዜግነት አጣርቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ መግለጡን የነገሩን ምንጮች፤ ቅሬታ አቅራቢዎች ቅሬታቸውን በጽሑፍ ለኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል።

ቅሬታ የቀረበባቸው “ተጽዕኖ ፈጣሪዎች”

ኮሚሽኑ “ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” በሚል ውክልና በምክክሩ እንዲሳተፉ ያደረጋቸው ግለሰቦች በምን መመዘኛ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው እንደተረጋገጠ ጥያቄ ያቀረቡ አካላት መኖራቸውን ዋዜማ ተረድታለች። በክልል ተወካዮች ጉባኤ በክልሎችና በፌደራል ደረጃ በድምሩ 31 “ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” እንዲካተቱ ተደርጓል። ይህ ውክልና፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ መምህራን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ወጣቶች እና ሴቶች ካገኙት ውክልና የሚበልጥ መሆኑን ያነሱ ቅሬታ አቅራቢዎችም፤ ኮሚሽኑ ጉዳዩን ዳግም እንዲያጤነው ጠይቀዋል። 

የታዛቢነት ሚና የተሰጣቸው ተመካካሪዎች

የክልል ተወካዮች ጉባኤ ድምጽ መስጠት በሚያስችል ውክልና ከተቀላቀሉ ተመካካሪዎች ውጭ፤ ያለ ድምጽ በ”ታዛቢነት” እንዲከታተሉ የተፈቀደላቸው አካላት መኖራቸውንም ዋዜማ ተረድታለች። ዲያስፖራዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች ያለ ድምጽ ጉባኤውን በታዛቢነት እንዲቀላቀሉ እያንዳንዳቸው ሁለት መቀመጫ እንደተሰጣቸው የገለጡልን ምንጮች፤ ሁለቱም አካላት ድምጽ የመስጠት መብት እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄ በኮሚሽኑ ተቀባይነት አለማግኘቱን አረጋግጠውልናል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለሁለት ቀናት እረፍት ካደረገ በኋላ ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን ደረጃ ምክክር ማድረጉን እንደሚቀጥል ኮሚሽኑ ገልጧል። [ዋዜማ]