ዋዜማ- የአዲስ አበባ እና የሸገር ከተማ አስተዳደሮች የሕዝብ አሰፋፈር ጥናት ይፋዊ ባልሆነ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ዋዜማ ሰምታለች፡፡
የፌዴራል ስታትስቲክስ አገልግሎት ያሰማራቸው ባለሙያዎች በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች መረጃ እያሰበሰቡ ሲሆን፤ የስታትስቲክስ አገልግሎቱ በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች ያሰማራቸው ባለሞያዎች ቤት ለቤት በመዘዋወር ፤ በአንድ ቤት የሚኖሩ የቤተሠብ አባላትን ብዛት፣ ዕድሜ፣ ጾታ፣ ሃይማኖት፣ የትምህርት ደረጃ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ እንዲሁም ወርሃዊ ገቢን የተመለከቱ መረጃዎችን እያሰባሰቡ እንደሆነ የዳሰሳ ጥናት ጥያቄ የቀረበላቸው ነዋሪዎች ገልጸውልናል። በአንዳንድ መንደሮችም፤ መኖሪያ ቤቶቹ ያረፉበት መሬት ልኬት መወሰዱን ጠቅሰዋል፡፡
የፌደራል ስታትስቲክስ አገልግሎት የካርታ ዝግጅት እና የጂኦግራፊያዊ መረጃ ሥርዓት ክፍል ባለሙያዎች ቤት ለቤት በመዘዋወር ካለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን ዋዜማ አረጋግጣለች።
ይህን ጥናት በተመለከተ በክልልም ይሁን በፌደራል ደረጃ በይፋ የተገለፀ መረጃ እስካሁን ዋዜማ አላገኘችም።
ቤት ለቤት የሚሰበሰበው መረጃ አላማ መረጃ እንዲሠጡ ለሚጠየቁት ነዋሪዎች በግልጽ የማይነገር በመሆኑ፤ ጥያቄ እንደፈጠረባቸው የሚገልጹት ነዋሪዎቹ፤ የፌደራል ስታትስቲክስ አገልግሎት ባለሞያዎች ለዳሰሳ ጥናቱ በተመረጡ መንደሮች መረጃ የማሰባሰብ ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ከነዋሪዎቹ ለሚቀርብላቸው ‹‹መረጃውን የምንሰጥበት አላማ ምንድነው? ›› የሚል ጥያቄ፤ የሚሰጡት ምላሽ የተለያየ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ዋዜማ የዳሰሳ ጥናቱን ምንነት እና ዓላማ ለማወቅ ባደረገችው ጥረት፤ መረጃ የሚያሰባስቡት ባለሞያዎች እና የአገልግሎቱ ከፍተኛ አመራሮች የሰጡት ምላሽ ልዩነት እንዳለው ታዝባለች፡፡ መረጃ ሰብሳቢዎቹ የሚያቀርቡት ምክንያት፤ የሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ናሙና ለመውሰድ የሚደረግ የዳሰሳ ጥናት መሆኑን ነው፡፡
የአገልግሎቱ አመራሮች በበኩላቸው፤ ቤት ለቤት መረጃ እየተሰበሰበ ያለው ለሕዝብ እና ቤት ቆጠራ የሚደረግ የቅድመ ዝግጅት አካል በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ ከአገልግሎቱ መረጃ ሰብሳቢዎች እና አመራሮች ለዳሰሳ ጥናቱ የሚሰጧቸው ምክንያቶች የሚጋጩ መሆናቸውን ተከትሎ፤ ዋዜማ ጥናቱን በሚመለከት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠይቃለች።
ምንጮቹ እንደሚሉት፤ በሁለቱ ከተሞች ላይ እየተከናወነ ያለው ይህ ጥናት፤ የሕዝብ አሰፋፈር እና ስብጥር እንዲሁም የነዋሪዎችን ትክክለኛ መረጃ ለይቶ መሰነድ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ‹‹የዳሰሳ ጥናቱ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራም ቅድመ- ዝግጅትም ሆነ የማኅበረ-ኢኮኖሚ ጥናት ይዘት የለውም›› የሚሉት ምንጮች፤ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረገው ጥናት የህዝብ አሰፋፈር እና ስብጥር ምጣኔን ለማወቅ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልል አካል በሆነው እና ከጥቂት አመታት በፊት በተቋቋመው የሸገር ከተማ አስተዳደር፤ ከዚህ ቀደም የብሄር ማንነትን መሠረት ያደረገ የህዝብ አሠፋፈር እና ስብጥር ጥናት መካሄዱንም ጠቅሠዋል። ጥናቱ ከአንድ አመት በፊት በሸገር ከተማ አስተዳደር የራሱ ባለሞያዎች መካሄዱን በመጥቀስ፤ ዋና ዓላማውም በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ያለውን የብሄር ብሔረሰቦች ምጣኔ እና ስብጥር ለማወቅ የተደረገ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በናሙና ጥናቱ ውጤት መሠረት፤ የአማራ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ያሉ እንደ ጋሞ ያሉ ብሄረሰቦች 60 በመቶ ሲሆኑ፤ የኦሮሞ ተወላጆች ምጣኔ 25 በመቶ እንዲሁም ቀሪው 15 በመቶ በአስተዳደሩ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ብሄረሰቦች እንደሚያካትት አብራርተዋል፡፡ ጥናቱ ሲካሄድ የዲጂታል መታወቂያን ጭምር በማገናኘት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰውሰራሽ ክህሎት) የታገዘ ጥናት መካሄዱንም ጠቁመዋል፡፡ ጥናቱ «ዲሞግራፊክ ሳምፕል ቼኪንግ» ተብሎ እንደሚጠራ የገለጹት ምንጮች፤ መሰል ጥናት በውሳኔ አሰጣጥ ረገድ ዜጎችን እና መንግሥትን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚታመን አስረድተዋል፡፡
ዲሞግራፊክ ሳምፕል ቼኪንግ ምንድነው?
ዲሞግራፊክ ሳምፕሊንግ የአንድን ህብረተሰብ እንደ ዕድሜ፣ ጾታ፣ ገቢ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ የብሔር ወይም የቋንቋ ስብጥር እና በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖረውን የቤተሰብ መጠን ያሉ ሁኔታዎችን ለማወቅ የሚደረግ የናሙና መረጣ ዘዴ ነው። በአንድ አካባቢ ያሉ ሰዎችን በሙሉ በአንድ ጊዜ ጠይቆ መረጃ መሰብሰብ ጊዜ የሚወስድ እና ብዙ ወጪ ያለው በመሆኑ፣ ሁሉንም ሊወክል የሚችል የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል እንደ ናሙና መርጦ ጥናት ለማካሄድ ያገለግላል።
ይህ የናሙና አሰባሰብ ዘዴ የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርት እና የጤና አገልግሎቶችን እቅድ ለማዘጋጀት፤ የመንግሥት ድጎማዎች እና ማህበራዊ ፕሮግራሞች ለትክክለኛው የህብረተሰብ ክፍል መድረሳቸውን ለማረጋገጥ፤ ቆጠራ ከመደረጉ በፊት የሕዝቡን ስርጭት እና አሰፋፈር አስቀድሞ ለመገመት፣ እንዲሁም የልማት እና የንግድ ሥራዎች የታለመላቸውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ለማድረግ እንደሚረዳ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የሸገር ከተማ አስተዳደር መዋቅር መመሥረትን ተከትሎ ቀደም ሲል የተከናወኑት ጥናቶች በዋናነት መሠረታዊ የሕዝብ ቁጥር ስብጥርን በማወቅ ላይ ብቻ የተገደቡ እንደነበሩ የገለጹት የዋዜማ ምንጮች፤ የመሬት ይዞታ አስተዳደር እና የማካካሻ ሥርዓት መቅረጽ፣ የምግብ ዋስትና እና የማኅበራዊ ኑሮ ደረጃ ክትትል እንዲሁም የቆጠራ ዞን ግንባታ በዚህ ጥናት ውስጥ እንደሚያልፍ ተናግረዋል፡፡
እየተሰበሰበ ያለው መረጃ የሰዎችን ቁጥር ማወቅ ብቻ ሳይሆን፤ በአዲስ አበባና በሸገር ከተማ ዙሪያ ያለውን የወደፊት የሀብት ክፍፍል፣ የመሬት ባለቤትነት እና አጠቃላይ የበጀት አወቃቀርን የሚወስን ትልቅ መዋቅራዊ ጥናት ነው ብለዋል፡፡
የሕዝብ ቆጠራ ቅድመ–ዝግጅት እና መደበኛ የሕዝብ ቁጥር ጥናት የመረጃ አሰባሰብ ልዩነቶች
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች ላይ እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ ለመረዳት፤ በሕዝብ ቆጠራ ቅድመ-ዝግጅት እና በመደበኛ የሕዝብ ቁጥር ጥናት መካከል ያለውን ሳይንሳዊ ልዩነት መገንዘብ ወሳኝ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
የሕዝብ ቆጠራ ቅድመ-ዝግጅት አጠቃላይ ሀገራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ከመደረጉ በፊት፣ ሀገሪቱን በትናንሽ ቀጠናዎች የመክፈል የቅድመ-ዝግጅት ሂደት ሲሆን፤ ባለሙያዎች በእያንዳንዱ መንደር ቤት ለቤት በመዞር የሁሉም መኖሪያ ቤቶች፣ ሕንፃዎች፣ ተቋማት እና ነባር የድንበር ወሠኖች ትክክለኛ የሳተላይት መገኛ ምልክት (Geo-coding) ያከናውናሉ።
በዚህ ሒደት የሚሰበሰበው መረጃ ሙሉ በሙሉ መልክዓ ምድራዊ ይዘት ያለው ሲሆን፤ የቦታ መጋጠሚያዎች፣ የቤት ቁጥሮች፣ የቤተሰብ አባላት ብዛት እና የመንገዶች ስም ስብስብን ያካትታል። ይህም፤ ወደፊት የህዝብ እና ቤት ቆጠራ ሲካሄድ ባለሞያዎች ተሰማርተው ቆጠራ የሚያካሂዱበት ቦታ እንዳይደራረብባቸው ወይም የሚታለፍ መኖሪያ ቤት እንዳይኖር፤ ሀገሪቱን በአማካይ ከ150 እስከ 200 አባወራዎች/እማወራዎች በሚይዙ ትናንሽ የቆጠራ ክልሎች በቴክኖሎጂ ከፍሎ ማደራጀት ነው።
መደበኛ የሕዝብ ቁጥር ጥናት ደግሞ ባለሙያዎች በተመረጡ መኖሪያ ቤቶች በመዞር፣ በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ ስላለው የቤተሰብ አባል ሁለንተናዊ መገለጫዎችና ማኅበራዊ ኑሮን መሠረት ያደረጉ መረጃ የመሰብሰብ ስራዎች የሚሠሩበት ነው፡፡
በዚህ ሒደት የሚሰበሰበው መረጃ ሙሉ በሙሉ ቁጥራዊ ይዘት ያለው ሲሆን፤ የሰዎች ዕድሜ፣ ጾታ፣ የወሊድ መጠን፣ የሞት መጠን፣ የፍልሰት ሁኔታ፣ የትምህርት ደረጃ እና የሃይማኖት ወይም የብሔር ስብጥርን ያካትታል።
የሕዝብ አሠፋፈር ለውጥ ስጋት?
በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች የሚደረጉ መረጃ የመሰብሰብ ሥራዎችን በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ የተለያዩ ስጋቶች እና «የሕዝብ አሰፋፈር ለውጥ ለማድረግ ታስቦ ነው» የሚሉ ጥርጣሬዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የፌደራል ስታትስቲክስ አገልግሎት አንድ ከፍተኛ ኃላፊ ግን፤ «ሁሉንም ነገር በፖለቲካ መነጽር መመልከት ተገቢ አይደለም» ብለዋል። ኃላፊው እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው ሥራ የካርታ እና የቦታ ዝግጅት (Spatial preparation) እንጂ የሕዝብ አሰፋፈር ጥናት ወይም የአስተዳደር ወሰን የመቀየር ሥራ አይደለም።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ እየተካሄደ ያለው ሥራ ለሚመጣው ሀገራዊ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ሥራ እንዲያመች የታቀደ «የቆጠራ ቦታ» የመለየት ተግባር ነው። ይህም በከተማ ደረጃ በአንድ የቆጠራ ቦታ ውስጥ ከ150 እስከ 200 የሚደርሱ ቤተሰቦችን በመለየት፣ በአንድ ወይም በሁለት የቆጠራ ባለሙያዎች አማካኝነት ሥራው ሳይበታተን እና አንድም ሰው ሳይቀር በሳይንሳዊ መንገድ እንዲቆጠር የሚያስችል አሰራር ነው።
በቅርብ ጊዜያት በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ የመሠረተ ልማት እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች መካሄዳቸውን ተከትሎ የሕዝብ አሠፋፈሩ እና የቤቶች ሁኔታ በእጅጉ መለወጡን የጠቆሙት ኃላፊው፤ አሁን የሚደረገው በዲጂታል መረጃ ላይ የሚገኝን አንድ ቦታ፣ ሕንፃ ወይም የመሬት ስፋት ከእውነተኛው የፎቶ ወይም የካርታ ቦታ ጋር የማገናኘት (Geo-reference) እና የካርታ ማሻሻያ ሥራ ለከተሞቹ ዕድገት እና ለቀጣይ ዕቅዶች አስፈላጊ በመሆኑ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት እና ከተሜነትን የማስፋፋት ሥራ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ ዘርፈ-ብዙ ሁነቶች መቀየራቸውን በመጥቀስ፤ ቀደም ሲል የነበሩ ወሠኖች፣ የቤት ቁጥሮች እና የሕዝብ አሠፋፈሮች በመቀየራቸው አዲስ የቆጠራ ቦታ (ካርታ) ማዘጋጀት አስገዳጅ መሆኑን አመልክተዋል። ካርታ የማዘጋጀት ሥራው 70 በመቶ መጠናቀቁን የጠቀሱት ኃላፊው፤ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አክለዋል። [ዋዜማ]
