ዋዜማ- አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላን በመስጋት ወደትግራይ ክልል መመለስ ያልቻሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ክረምቱን በግቢው ውስጥ ለማሳለፍ ፍቃድ ማግኘታቸውን ዋዜማ ሰምታለች፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች፣ በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ እና አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ስጋት ምክንያት ወደ ክልላቸው መመለስ ባለመቻላቸው፤ ክረምቱን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እንዲያሳልፉ ተፈቅዶላቸዋል።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ተማሪዎች እንደገለጹት፤ ጥያቄው መጀመሪያ ላይ በዩኒቨርሲቲው በኩል ተቀባይነት አጥቶ ለሳምንታት የቆየ ቢሆንም፤ ከጊዜያት በኋላ ግን በትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ መፍትሔ ሊያገኝ ችሏል።
ተማሪዎቹ ወደ ትግራይ ላለመመለስ የወሰኑበትና አዲስ አበባ ውስጥ ለመቆየት የተገደዱበት ዋነኛ ምክንያት፤ በፌደራል መንግስቱ እና በህወሓት መካከል እየተካረረ የመጣውን ውጥረት ተከትሎ ሊከሰት የሚችል ጦርነት እና ተያያዥ የደህንነት ስጋቶች ናቸው።
ተማሪዎቹ አስገዳጅ ወይም በፈቃደኝነት የሚደረግ ማንኛውም አይነት ወታደራዊ ምልመላ፤ ለመደበኛ ህይወታቸውም ሆነ ለወደፊት የትምህርት ጉዟቸው ትልቅ አደጋ እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም አንዳንዶቹ ተማሪዎች የትራንስፖርት ወጪን የመሸፈን አቅም የሌላቸው በመሆኑ፤ አዲስ አበባ ለመቆየታቸው ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል።
ጥያቄው የቀረበበት መንገድና የዩኒቨርሲቲው ምላሽ
እንደ ተማሪዎቹ ገለጻ፤ ጥያቄው በተደራጀ መንገድ የቀረበው በሰኔ ወር መጀመሪያ አካባቢ ነው፡፡ የ2 መቶ 86 ተማሪዎች ስም ዝርዝር ተዘጋጅቶ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ልማት እና ስኬት ጽህፈት ቤት (Student Development & Success) በደብዳቤ ለማስገባት ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም፤ ዩኒቨርሲቲው «ከላይ የመጣ መመሪያ የለም፤ ጥያቄያችሁን ማስተናገድ አንችልም» በማለት ደብዳቤውን ሳይቀበል ቀርቷል።
ከሳምንታት ቆይታ በኋላ፤ ጥያቄ ያቀረቡት ተማሪዎች ቁጥር 3 መቶ 44 መድረሱን የገለጹልን ምንጮች፤ የዩኒቨርሲቲው አንድ ከፍተኛ አመራር፤ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ጣልቃ መግባት እንደሌለበት በመጥቀስ፤ ጥያቄያቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር ቢያቀርቡ የተሻለ እንደሚሆን እንደነገሩዋቸው አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሰረት ጥያቄው ለትምህርት ሚኒስቴር ከቀረበ ከ1 ወር በኋላ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥያቄውን በመቀበሉ፤ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው እንዲቆዩ ይሁንታ ተሰጥቷቸዋል።
አሁን ያሉበት ሁኔታ እና የበጀት ስጋት
በአሁኑ ወቅት ተማሪዎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በበጋው የትምህርት ክፍለ ጊዜ በተመደቡበት የተለመደው የመኝታ ክፍል እና የምግብ አገልግሎት አግኝተው ክረምቱን እያሳለፉ ይገኛሉ።
ሆኖም፤ የተመደበው የምግብ በጀት አነስተኛ መሆኑን የሚገልጹት ተማሪዎቹ፤ ዩኒቨርሲቲው ለአንድ ተማሪ በቀን 100 ብር ለምግብ የመደበ ሲሆን፣ ይህም በ100 ብር ቁርስ፣ ምሳ እና ራት መሸፈን እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል። ቀደም ሲል በቀን ይሰጥ የነበረው 1 መቶ 72 ብር እንደነበርና አሁን ግን በጀቱ ወደ 100 ብር እንዲቀነስ መደረጉ ተማሪዎችን ለከፍተኛ ችግር የሚዳርግ መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ
ጉዳዩ ‹‹ፖለቲካዊ ነው›› በሚል ለ 1 ወር ገደማ ምላሽ ሳያገኝ መቆየቱን የሚገልጹት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የትምህርት ሚኒስቴር አንድ ከፍተኛ ሃላፊ፤ የቀድሞው የመቀለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት እና በአሁኑ ወቅት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አማካሪ ክንደያ ገብረህይወት (ፕ/ር) ጉዳዩን በዋናነት እንደያዙት ነግረውናል፡፡ ሁኔታው ከህግ እና አሰራር ውጪ መሆኑ ተጠቅሶ ክርክር ሲደረግበት መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፤ ከብዙ ውይይቶች በኋላ በትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የይሁንታ ደብዳቤ መምራታቸውን አብራርተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሌሎቹ የሃገሪቱ ክፍሎች ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች በያሉበት ክረምቱን እንዲያሳልፉ ጥረት ሲደረግ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ላይ የደረሰበትን ደረጃ ግን በእርግጠኝነት መናገር እንደማይችሉ ነግረውናል፡፡
በራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አሰራር ጣልቃ መግባት ይቻላል?
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው እኝሁ ሀላፊ እንደሚሉት፤የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው መመሪያ መሠረት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ራስ-ገዝ (Autonomous) ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ቢወሰንም፤ ይህ የራስ-ገዝነት ሂደት በአንድ ጀምበር ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅ ሳይሆን፤ ለተወሰኑ ዓመታት የሚቆይ የሽግግር ጊዜ ያለው ነው።
ዩኒቨርሲቲው በራሱ የትምህርት አሰጣጥ ስርአት የመቅረጽ፣ የራሱን የውስጥ ደንቦችና መመሪያዎች የማውጣት፣ ተማሪዎችን በራሱ መስፈርት የመቀበልና የሰራተኞቹን ስምሪት የማስተዳደር ሰፊ ነፃነት እንዳለው ገልጸው፤ ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው አሁንም ቢሆን ዋናው የሥራ ማስሄጃ በጀት የሚመደብለት ከፌደራል መንግስት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹ዩኒቨርሲቲው የቱንም ያህል ራስ-ገዝ ቢሆን፤ ከሀገራዊ ደህንነት፣ ከተማሪዎች ጥበቃ እና ከትምህርት ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ትልልቅ ውሳኔዎች ላይ በትምህርት ሚኒስቴር እና በፌደራል መንግስቱ የበላይ ውሳኔ ስር ይወድቃል›› በማለት አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሰኔ 27 ቀን፤ 2018 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት፤ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ነው ባለው የግዳጅ ለወታደራዊ ምልመላ፤ ከሚታፈሱት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ከ18 ዓመት በታች መሆናቸውን ማረጋገጡን ጠቅሶ፤ በክልሉ የሚካሄደው ሰዎችን በግዳጅ ለወታደራዊ ምልመላ ወይም ለጦርነት የማሰማራት ተግባር እንደ ጉልበት ብዝበዛ እና የጦር ወንጀል ሊቆጠር እንደሚችልም መግለጹ ይታወሳል፡፡ [ዋዜማ]
