ዋዜማ- የክልል አስተዳደሮች ከመንግሥት ሠራተኞች እና ከተሿሚዎች ወርሃዊ ደመወዝ ላይ ከ0.5 እስከ 2 በመቶ የሚሆነው ገንዘብ ፤ለአደጋ ጊዜ ምላሽ ፈንድ የሚቆረጥበትን አዲስ ደንብና መመሪያ በተመሳሳይ ወቅት ማውጣታቸውን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች።
ከመንግሥት ሠራተኞች ወርሃዊ ደመወዝ ላይ የአደጋ ጊዜ ፈንድ በሀገር አቀፍ ደረጃ በቋሚነት እንዲሰበሰብ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፤ በፌዴራል ደረጃ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል። ይሁን እንጂ የፌዴራል መንግሥት ውድቅ ያደረገውን ይህን ከመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ላይ ፈንድ የመሰብሰብ አሠራር፤ ክልሎች ባወጧቸው ደንቦችና መመሪያዎች ውስጥ በማካተት ወደ ትግበራ እየገቡ ይገኛሉ፡፡ አንዳንድ ክልሎችም፤ ካለፈው ነሃሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ ወደ ትግበራ መግባታቸው ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አዋጅ ቁጥር 1386/2017 መሠረት፤ የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ የገቢ ምንጭ ወሰን በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ ቁጥር 576/2018 ላይ ተደንግጓል። በዚህ ደንብ መሠረት፤ የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ የገቢ አሰባሰብ፣ ምንጭ እና ምጣኔ በዝርዝር ሲወሠን፤ የመንግሥት ሠራተኞች ወርሃዊ ደመወዝ ግን አልተካተተም።
መንግስት የአደጋ ጊዜ ፈንድን ያቋቋመው ከተረጂነት ለመላቀቅ በያዘው እቅድና ፣ ከውጪ የሚገኝ ዕርዳታ እጅግ በተዳከመበት ወቅት የሚፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ነው።
የ‹‹ሀልዋ›› ፈንድ
በአብዛኞቹ ክልሎች ከመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠን ተመሳሳይ ቢሆንም፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግን ከሁሉም ክልሎች ከፍ ያለ መጠን የሚሰበስብበትን አሠራር ዘርግቷል። ክልሉ «ሀልዋ» ብሎ በሰየመው የገንዘብ አሰባሰብ እና አጠቃቀም ደንብ ቁጥር 187/2018 መሠረት፤ ከመንግሥት ሠራተኞች ወርሃዊ ደመወዝ ከ1 እስከ 2 በመቶ እንዲቆረጥ ይደነግጋል።
ዋዜማ የተመለከተችው በክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ጌታሁን አብዲሳ ተፈርሞ ለወረዳና ከተማ አስተዳደሮች የተላከው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፤ ከመንግሥት ሠራተኞች እና ከተሿሚዎች የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠን ልዩነት አለው። ከተሿሚዎች የተጣራ ደመወዝ በየወሩ ሁለት በመቶ (2%)፣ ከመደበኛ የመንግሥት ሠራተኞች ደግሞ አንድ በመቶ (1%) ተቆርጦ ለአደጋ ምላሽ ፈንድ ገቢ ይደረጋል።
ደብዳቤው የደረሳቸው የከተማ እና የወረዳ አስተዳደሮች ከነሐሴ ወር፤ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ገንዘቡን ሰብስበው፤ «ሀልዋ» በተሰኘው ለአደጋ ምላሽ ፈንድ ገቢ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ በማስገባት በደረሰኝ እንዲያወራርዱ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።
ይሁን እንጂ፤ የክልሉ መንግሥት ሠራተኞች በየወሩ ከደመወዛቸው ስለሚቆረጠው የገንዘብ መጠን ያሳወቃቸው አካል እንደሌለ ገልጸዋል። በዚህም «አስቀድመን ባልተስማማንበትና መጠኑን ባልወሰንንበት ሁኔታ ደመወዛችን መቆረጥ የለበትም» የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ምንጮች ነግረውናል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከነሐሴ ወር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ከመንግሥት ሠራተኞች ወርሃዊ ደመወዝ ላይ ፤ለአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ፈንድ የሚሆን ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚያስችል መመሪያ አውርዷል። ክልሉ ባወጣው የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ፈንድ ደንብ ቁጥር 112/2018 መሠረት፣ ከመንግሥት ሠራተኞችም ሆነ ከተሿሚዎች ወርሃዊ ደመወዝ ላይ እኩል 0.5 በመቶ (0.5%) ተቆራጭ ይደረጋል።
ክልሉ አዲሱን ደንብ ቢያጸድቅም፤ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ካሉ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት ማካሄዱን የገለጹት ምንጮች፤ አብዛኞቹ የመንግሥት ሠራተኞች በየወሩ ከደመወዛቸው በሚቆረጠው የገንዘብ መጠን ላይ በቃል ደረጃ ተስማምተዋል ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሐረሪ ክልሎች ከመንግሥት ሠራተኞች የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ፈንድ መሰብሰብ የሚያስችላቸውን መመሪያ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ተረድተናል። ሌሎች ክልሎችም የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ፈንድ ምንጫቸውን ለማስፋት ቀደም ሲል ሲጠቀሙበት የነበረውን መመሪያ እያሻሻሉ ይገኛሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ከመንግሥት ሠራተኞች ወርሃዊ ደመወዝ ላይ 0.5 በመቶ (0.5%) የሚሆነውን ገንዘብ በመቁረጥ አሠራሩን ቀደም ብሎ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል።
በወቅቱ የነበረው ክርክር
የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድን የገቢ ምንጭ ለማስፋት ረቂቅ ሕጉ ሲዘጋጅ ከተነሱት አማራጮች አንዱ፤ ከመንግሥት ሠራተኞች ወርሃዊ ደመወዝ ላይ በቋሚነት በመቶኛ ተቆርጦ ገቢ እንዲደረግ የሚል ሀሳብ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሀሳብ በሚኒስትሮች ምክር ቤትና በሕግ አውጪው አካል ውይይት ሲደረግበት በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ውድቅ ተደርጓል።
የመጀመሪያው ምክንያት በመንግሥት ሠራተኞች ላይ ያለውን የኑሮ ውድነት ጫና ከግምት በማስገባት፤ ከወርሃዊ ደመወዝ ላይ ተቆራጭ ማድረግ ያልተገባ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ይፈጥራል የሚል ስጋት መኖሩ ነው። ሁለተኛው ምክንያት፤ ገቢ የማሰባሰብ ስራው ‹‹በሕግ አገስዳጅነት ይፈጸም ወይስ በበጎ ፈቃድ?›› የሚለው ነጥብ አከራካሪ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ በመሆኑም፤ በቋሚነት ከደመወዝ በሚቆረጥ ገንዘብ ገቢ ከመሰብሰብ ይልቅ ትኩረቱን እንደ ባንክ፣ ቴሌኮም እና ከማንኛውም አክሲዮን ከሚገኝ የትርፍ ድርሻ ላይ የሚወሰድ አንድ በመቶ (1%)፣ እንዲሁም ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚገኙ ዕርዳታዎች ባሉ ሌሎች የገቢ ምንጮች ላይ ተደርጓል። በዚህም ምክንያት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 576/2018 መሠረት ከተወሰኑት 17 የገቢ ምንጮች ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ሳይካተት ቀርቷል። [ዋዜማ]
