ዋዜማ- በሱዳን አዋሳኝ አካባቢ በሕወሓት ሀይሎችና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ዛሬ ማለዳ ላይ ውጊያ መቀስቀሱንና እስከ ቀን ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ተኩስ እንደነበረ እማኞች ነግረውናል።
ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 25፣ 2018፣ ዓ፣ም ከንጋቱ 11፡20 ገደማ በከባድ መሳሪያ የተገደፈ ውጊያ የተቀሰቀሰው የህወሓቱ አርሚ 70 በሚንቀሳቀስበት ሸረሪና ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ላይ ሲሆን፣ በዚያው አቅራቢም በሚገኘው በረኸት አቅጣጫም ተኩስ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በተከታታይ የከባድ መሳሪያ ድምጽ ይሰማ እንደነበረ የጠቆሙት ምንጮች፣ ውጊያው የህወሓት ታጣቂዎች በስፋት ወደ ሚንቀሳቀሱበት ሸረሪና አቅጣጫ እንደሚያመዝን አመላክተዋል፡፡ የዛሬ ግጭት ከዚህ ቀደም በአካባቢው አልፎ አልፎ ከሚያጋጥሙ የተኩስ ልውውጦች የተለየ ነው ተብሏል፡፡
የከባድ መሳሪያ ተኩስ ድምጽ እሰከ ቀኑ 9፡00 ድረስ አልፎ አልፎ እንደሚሰማቸው የሑመራ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ውጊያ እንደተጀመረ ጠዋት ላይ ሲሰሙት የነበረው ተከታታይ የከባድ መሳሪየ ድምጽ ከስዓታት በኋላ ቀን በቀስ የሚተኮስበት ቆይታ እየቀነሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በህወሓት ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ግጭት ከመቀስቀሱ ቀደም ብሎ፣ የሱዳን ኃይሎች ልጉዲ በሚባል አካባቢ ሰርገው በመግባት አርሶ አደሮችን አፈናቅለው ነበር ተብሏል፡፡ በሱዳን ኃይሎች ትንኮሳ በአካባቢው በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ ስምንት ባለሀብቶች ንብረታቸው ተዘርፎ ወደ ከተማ መፈናቀላቸውን የጠቆመት ምንጮች፣ መከላከያ ሠራዊት ከሰሞኑ አከባቢውን ማስለቀቁን ጠቁመዋል፡፡
በኃይል ሥልጣን የተቆጣጠረው በደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የትግራይ አስተዳደር በሸረሪና በኩል ግጭት መቀስቀሱን አረጋግጧል፡፡ አስተዳደሩ ዛሬ ይፋ ባደረገው መግለጫው የፌደራል መንግሥት “በምዕራብ ትግራይ ሸረሪና አቅጣጫ ግልፅ ጦርነት ከፍቷል” በማለት ወንጅሏል፡፡
በፌደራል መንግሥት በኩል ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ስዓት ድረስ በጉዳዩ ላይ በይፋ የተሰጠ መረጃም ይሁን ማብራሪያም የለም፡፡
የሑመራ እንቅስቃሴ ገደብ
መከላከያ ሠራዊት ከሑመራ ከተማ ውጪ በአካባቢው የሚደረጉ የተሸከርካሪ እና የሰው እንቅስቃሴዎችን መገደቡ ምንጮች ነግረውናል፡፡ መከላከያ ዛሬ ረፋድ ጀምሮ በአካባቢው በጣለው ገደብ የእርሻ ቦታዎችን ጨምሮ ከሑመራ ከተማ ውጪ የሰው እንቅስቃሴ መቆሙ ተገልጧል፡፡
በእንቅስቃሴ ገደቡ ወደ ሑመራ ከተማ መግባት እንጂ፣ መውጣት እንደማይቻል የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጠዋል፡፡ መከላከያ በሑመራ ከተማ መውጫና መግቢያ በሮች ላይ አዲስ ኬላዎች ጥሎ ጥብቅ ፍተሻ እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ስዓት ድረስ በአካባቢው የሰው እንቅስቃሴ በያለበት መቆሙን ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች፡፡
የራያ አካባቢዎች ውጥረት
የመንግሥት ኃይሎች እና የህወሓት ታጠቂዎች በራያ በኩል ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በቅርብ ርቅት ላይ “ተፋጠዋል” ሲሉ ውጥረቱ ማየሉን ከስፍራው የሚገኙ ምንጮች ነግረውናል፡፡ በተለይም አፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎችን በሚያዋስኑ የራያ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መኖሩን በኣአካባቢው ካሉ የተለያዩ ምንጮች ስምተናል።
ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት እንደገባቸው የገለጡት የአካባበቢው ነዋሪዎች፣ በእግር ጭምር ወደ ራያ ቆቦ እየሸሹ መሆኑን ገልጠዋል፡፡
በተለይም የትግራይ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው የራያ አካባቢዎች ነዋሪዎች፣ “ጦርነቱ ከተጀመር መንገድ ይዘጋል” በሚል ስጋት ቀደም ብሎ በስፋት ሸሽተዋል፡፡ በዚህም በራያ ቆቦ ከተማ ከፍተኛ የተፈናቃዮች ፍሰት በመኖሩና የከተማዋ የማስተናገድ አቅም ውስን በመሆኑ በቅርብ የተፈናቀሉት ወደ ወልዲያና ደሴ እየሄዱ መሆኑን ተረድተናል። [ዋዜማ]
