ዋዜማ- የአፍሪካ እና የካረቢያን ፊልሞችን ለዕይታ በማቅረብ ፊልም ሠሪዎችን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ያቀደው አፍሮ ፒክስ (Afropix)፤ የኢትዮጵያ ፊልሞችን በድረ ገጽ አማካኝነት ለዕይታ ማቅረብ ጀምሯል። 100 ሺሕ ዕይታ ለሚያገኙ ፊልሞች 3 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር ለመክፈል ከፊልም ሠሪዎች ጋር ውል እየገባ የሚገኘው አፍሮ ፒክስ፤ በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ የፊልም ቦርዶች እና የፊልም ፌስቲቫሎች ጋር ወዳጅነት በመፍጠር እየሠራ ይገኛል። የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ደግሞ ከአፍሮ ፒክስ ጋር ስምምነት በመፈጸም የኢትዮጵያ ፊልሞች በ[afropix.com] ድረ ገጽ ለዕይታ እንዲበቁ እያደረገ ይገኛል። በድረ ገጹ እስካሁን፤ “ማንያዘዋል”፣ “የመስቀል ወፍ”፣ “ገመሃልያ” እና “አንድ ታሪክ” የተሰኙ ፊልሞች ለዕታ መብቃታቸውን ዋዜማ ተመልክታለች።

የድረ ገጹ አዲስ ነገር

አፍሮ ፒክስ ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች የሚያሟሉና ውል የሚፈርሙ ፊልም ሠሪዎች ፊልሞቻቸውን በድረ ገጹ ለዕይታ እንዲያርቀቡ፤ ለአንድ ዕይታ 0.03 ዶላር፣ ለ10 ሺሕ ዕይታ 300 ዶላር፣ ለ100 ሺሕ ዕይታ ደግሞ 3 ሺሕ ዶላር ክፍያ የሚፈጽምበት ቀመር በውሉ ላይ አካቷል። ይህ አሠራር በሶስት ወራት ውስጥ ለሚኖር የዕይታ መጠን ክፍያ የሚፈጸምበት ነው ያሉት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል መስራችና ዳይሬከተር ይርጋሸዋ ተሾመ፤ በድረ ገጹ ለዕይታ የቀረቡ ፊልሞች ሶስት ወራት ሲያስቆጥሩ በጊዜ ገደቡ ውስጥ ያገኙትን የዕይታ መጠን ታሳቢ ባደረገው ቀመር መሰረት ክፍያ እንደሚፈጸምላቸው ገልጠዋል።

አፍሮ ፒክስ የሚፈጽመው የክፍያ መጠን እንደ ዩቱብ ካሉ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ መድረኮች አንጻር የተሻለ ነው የሚሉት ይርጋሸዋ፤ በዕይታ መጠን አማካኝነት የሚፈጸመው ክፍያ እስከ 10 እጥፍ የሚበልጥ መሆኑን ነግረውናል። “እያንዳንዷ ዕይታ ዋጋ አላት፣ ፊልም ሠሪዎች እንዲሁም ፊልም ተመልካቹ ማህበረሰብ ይህን ድረ ገጽ በአግባቡ ከተጠቀመበት በዘርፉ ላይ የሚስተዋለን የፋይናንስ ችግር መቅረፍ ያስችላል” ሲሉም ያላቸውን እምነት ገልጠዋል።   

ፊልማቸው በድረ ገጹ ለዕይታ እንዲበቃ ስምምነት የፈጸሙ ፊልም ሠሪዎች ፊልማቸውን በሌሎች አማራጮችም ለዕይታ ማቅረብ እንደሚችሉ አክለው ያነሱት ይርጋሸዋ፤ በፊልም ፌስቲቫሎች ላይ የመሳተፍ ሙሉ መብት እንዳላቸውም ነግረውናል። “በሌሎች የዕይታ መድረኮች ተመሳሳዩ ዕድል የማይገኝ ነው፤ አፍሮ ፒክስ ፊልም ሠሪዎች የተሻለ ክፍያ እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ ሁሉንም ዕድሎች እንዲጠቀሙ የሚፈቅድ ነው” ሲሉም ከአፍሮ ፒክስ ጋር የሚፈጸም ስምምነት ብቸኛ (Exclusive) አለመሆኑን ጠቁመዋል። የፊልሞች የቅጂ መብት የባለቤቶቻቸው ሆኖ እንደሚቀጥልም ሰምተናል።

አፍሮ ፒክስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እይታ ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አዲስ የግንኙነት መስመር እንደሚከፍት ተጠብቋል። ድርጅቱ ለፊልም ሠሪዎች ስልጠና መስጠት፣ የመረጃ ቋት መገንባት እንዲሁም ሌሎች ዕቅዶች ያሉት መሆኑን አስታውቋል። 

የትኞቹ ፊልሞች ለዕይታ መብቃት ይችላሉ?

ፊልም ሠሪዎች ፊልሞቻቸው በአፍሮ ፒክስ ድረ ገጽ ለዕይታ እንዲበቁ ለማድረግ ማሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ስለመኖራቸው የሚናገሩት ይርጋሸዋ፤ ቀዳሚው ጉዳይ የእንግሊዝኛ የትርጉም ጽሑፍ (ሰብታይትል) መሆኑን ጠቁመዋል። ስምምነት የሚፈጸመው የፊልሙን ሙሉ የቅጂ መብት ከያዘ አካል ጋር ሲሆን፤ ከቅጂ መብት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች እንዳይነሱ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ሰምተናል። በይዘት ደረጃ የማህበረሰብን ባህል የማይቃረኑ እና መሰል መሰረታዊ ጉዳዮች ታሳቢ እንደሚደረጉም አውቀናል።

ድርጅቱ ፊልሞች በተሠሩበትና ለዕይታ በበቁበት ጊዜ ላይ ያስቀመጠው ገደብ ባይኖርም፤ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በተሠሩት ላይ ትኩረት መደረጉን ሰምተናል። ይሁንና በየትኛውም ጊዜ የተሠራ ፊልም በድረ ገጹ በኩል ለዕይታ መብቃት እንደሚችል ይርጋሸዋ ጠቁመዋል።   

ምን ያህል ፊልሞችን ለዕይታ ለማብቃት ታቅዷል?

በየወሩ ከሶስት እስከ አምስት የሚደርሱ ፊልሞችን ለዕይታ ለማብቃት መታቀዱን ዋዜማ ሰምታለች። እስካሁን ለዕይታ ከቀረቡት ፊልሞች ባሻገር ሌሎች ፊልም ሠሪዎች ከድርጅቱ ጋር ስምምነት ለመፈጸም በሂደት ላይ መሆናቸውን የገለጡልን ይርጋሸዋ፤ ጥያቄ የሚያቀርቡ ፊልም ሠሪዎች የሚበራከቱ ከሆነ በየወሩ ለዕይታ የሚበቁ ፊልሞች ቁጥር ከፍ እንደሚደረግ ነግረውናል። ከዚህ ቀደም በድርጅቱ አሠራር ዙሪያ ከፊልም ሠሪዎች ጋር ለሁለት ጊዜያት ያህል ውይይት መደረጉን የሰማን ሲሆን፤ ፊልሞቻቸውን በድረ ገጹ ለዕይታ ለማብቃት ፍላጎታቸውን ያሳዩ በርካታ መሆናቸውን ሰምተናል።

ድርጅቱ የሚከፍለው ከፍተኛ ክፍያ እና ምንጩ

ፊልሞችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዕይታ ከማብቃት ባሻገር በዕይታ መጠን ልክ ክፍያ የሚፈጸምበት አሠራር ፊልም ሠሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው በሚል ተስፋ ተጥሎበታል። 100 ሺሕ ዕይታ ያለው አንድ ፊልም አሁን ባለው የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ተመን መሠረት ከ480 ሺሕ ብር በላይ ማግኘት ይችላል። “ድርጅቱ ይህንን ያህል ክፍያ መፈጸም የሚያስችለውን ገቢ እንዴት ያመነጫል?” የሚለውም ዋዜማ ለድርጅቱ ተወካይ ካቀረበቻቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ነው። አፍሮ ፒክስ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው የሚሉት ይርጋሸዋ፤ ለድርጅቱ ድጋፍ የሚያደርጉ ኢንቨስተሮች መኖራቸውን ነግረውናል። በድረ ገጹ ምዝገባ አድርገውና ክፍያ ፈጽመው ፊልሞችን የሚመለከቱ ደንበኞች መኖራቸውን አክለው የገለጡት ተወካዩ፤ በዚህ መንገድ ከምዝገባ የሚሰበሰብ ገቢ አንዱ የገቢ ምንጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

ክፍያ ሳይፈጽሙ ፊልሞችን በነጻ የሚመለከቱ ተመልካቾች ደግሞ በፊልሞች መካከል የሚተላለፉ ማስታወቂያዎችን መከታተል እንደሚጠበቅባቸው ሰምተናል። በዚህም ድርጅቱ ገቢ እንደሚያገንበት ተነግሯል። ድርጅቱ ከተለያዩ የክፍያ ድርጅቶች ጋር ስምምነት በመፍጠር አብሮ እየሠራ መሆኑንም ሰምተናል። ድርጅቱ በአፍሪካ የፊል ዕድገት ላይ የበኩሉን ለመወጣት ወደ ሥራ የገባ ስለመሆኑ በገለጠበትና ዋዜማ በተመለከተችው መግለጫው፤ ፊልም ሠሪዎች ተገቢውን ክፍያ እንዲያገኙ ማድረግ አንዱ ዓላማው መሆኑን ጠቁሟል።   

እነማን በድረ ገጹ እየተጠቀሙ ነው?

በድርጅቱ ድረ ገጽ [afropix.com] ከ35 በላይ ፊልሞች ለዕይታ መብቃታቸውን ዋዜማ ተመልክታለች። እነዚህ ፊልሞች ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጃማይካ የተውጣጡ ናቸው። በ54ቱም የአፍሪካ ሀገራት ከሚገኙ የፊልም ቦርዶችና ፌስቲቫሎች ጋር በመተባበር በርካታ ፊሎችን ለዕይታ ለማብቃት መታቀዱን የሰማን ሲሆን፤ በቀጣዮቹ ጊዜያት የፊልሞቹ ቁጥር ከፍ እንደሚል ይጠበቃል።

 ድረ ገጹን ለማስተዋወቅ ያቀዱት ፊልም ሠሪዎች

ፊልሞቻቸው በድረ ገጹ ለዕይታ የቀረቡ እና ለዕይታ ለማቅረብ በሂደት ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ፊልም ሠሪዎች ድረ ገጹን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ለማስተዋወቅ ማቀዳቸውን  ሰምተናል። ፊልሞች የሚያገኙት ዕይታ በተበራከተ ቁጥር ፊልም ሠሪዎች የሚያገኙት ገቢ የሚያድግ ከመሆኑ ጋር በተያያዘም፤ ተመልካቾች ድረ ገጹን እንዲጠቀሙ ማድረግ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ድርጅቱ ከፊልም ሠሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት አጽንኦት የተሰጠበት ጉዳይ መሆኑን ዋዜማ ሰምታለች። [ዋዜማ]