ዋዜማ- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በ11ኛ ቀን ውሎው በ”ንዑስ” ቡድን ደረጃ ሲደረጉ የነበሩ “ምክክሮችን” ማጠናቀቁን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታውቋል። በ”ንዑስ” ቡድኖች ውስጥ በሚገኙና 10 አባላት ባሏቸው “ጥቃቅን” ቡድኖች “መሪ ጥያቄዎች”ን መሰረት በማድረግ የተዘጋጁ ሰነዶች፤ ለየንዑስ ቡድኖች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው መሆኑን የገለጡ ምንጮች፤ “ንዑስ” ቡድኖች የ”ጥቃቅን” ቡድኖችን ሰነድ በማቀናጀት በ”ንዑስ” ቡድን ደረጃ “መሪ ጥያቄዎችን” መሰረት ያደረገ “ሰነድ” እንዲያዘጋጁ መደረጉን ጠቁመዋል።
ጉባኤው ሐምሌ 19 ቀን 2018 ዓ.ም “ዕረፍት” ካደረገ በኋላ ሰኞ ሐምሌ 20 ቀን 250 አባላት ባሉት “ስልታዊ” ቡድኖች ደረጃ “ምክክር” ማድረግ እንደሚጀምር ተገልጧል። አምስት “ንዑስ” ቡድኖችን የሚይዘው “ስልታዊ” ቡድንም ተመሳሳዩን ሰነድ እንደሚያዘጋጅ የሚጠበቅ ሲሆን፤ አንድ “የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ” ቡድን የሚያዋቅሩት ሁለት ስልታዊ ቡድኖች የሚያቀርቧቸው ሰነዶች፤ በሥራ ቡድን ደረጃ የሚቀርበውን “ምክረ ሀሳብ” ለማዘጋጀት በጥቅም ላይ እንደሚውሉ ኮሚሽኑ ለተመካካሪዎች ያቀረበውና ዋዜማ የተመለከተችው “የሥራ ቡድን የምክክር ስልት” ሰነድ ይጠቁማል።
እስካሁን ባለው ሂደት በተመካካሪዎች የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች እንደ አማራጭ ተይዘው የሚያልፉ ሲሆን፤ ከሚቀመጡ አማራጮች መካከል ምርጫ የሚከናወነው በሥራ ቡድን ደረጃ “የምክረ ሀሳብ” ሰነድ ከተዘጋጀ በኋላ መሆኑን ዋዜማ የተመለከተችው ሰነድ ይጠቁማል። በ”ስልታዊ” ቡድን ደረጃ ለሚዘጋጀው ሰነድ የሶስት ቀናት የጊዜ ዕቅድ የተያዘለት ስለመሆኑም ሰምተናል። በሥራ ቡድን ደረጃ ለሚዘጋጀው የምክረ ሀሳብ ሰነድም ተመሳሳይ የሦስት ቀናት ጊዜ ዕቅድ ተቀምጧል።
ሁለቱ የአዲስ አበባ አማራጮች
በንዑስ ቡድን ደረጃ በተካሄዱ የሰነድ ዝግጅት ሂደቶች ውስጥ፤ ለአዲስ አበባ ከቀረቡ አራት “የሕጋዊ አቋም” አማራጮች መካከል ሁለቱ ሚዛን መድፋታቸውን ምንጮች ነግረውናል። አዲስ አበባ “ሲቲ ስቴት (ራስ ገዝ)”፣ “የፌደራል አካል”፣ “ራሷን የቻለች ክልል”፣ “የኦሮሚያ አካል” የሚሉ አማራጮች እንደቀረቡላት መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ በጥቃቅን ቡድን እንዲሁም በንዑስ ቡድን ደረጃ በተደረጉ “ምክክሮች”፤“የፌደራል አካል” እና “የኦሮሚያ አካል” የሚሉት አማራጮች ጎልተው መውጣታቸውን ምንጮች ነግረውናል።
“የፌደራል ከተሞች” የሚል ርዕስ በተሰጠው አጀንዳ ቁጥር 3 ውስጥ በንዑስ አጀንዳነት የቀረበው “የአዲስ አበባ ሕጋዊ አቋም” ጉዳይ “የሞቀ የሀሳብ ልውውጥ” ከተካሄደባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን የገለጡት ምንጫን፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለምክክር ሂደቱ ባቀረበው “የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎች – የውይይት መሪ ጥያቄዎች” ሰነድ መሰረት ከቀረቡት አራት አማራጮች መካክል “ሲቲ ስቴት (ራስ ገዝ)”፣ “የፌደራል አካል”፣ እና “የኦሮሚያ አካል” የሚሉት አማራጮች በድጋፍና በተቃውሞ አስተያየቶችን ሲያስተናግዱ እንደቆዩ ጠቁመዋል። ኮሚሽኑ ያቋቋመው “የምሁራን ፓናል” ሐምሌ 16 ቀን፤ 2018 ዓ.ም በአጀንዳዎች ዙሪያ ለተመካካሪዎች ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ፤ ሁለቱ አማራጮች ጎልተው መውጣታቸውን ሰምተናል። የፓናሉ አባላት የአራቱን አማራጮች ምንነት የተመለከተ ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን፤ አዲስ አበባ “ራስ ገዝ” ትሁን የሚል አቋም ይዘው የነበሩ “ተመካካሪዎች” ከተማዋ “የፌደራል አካል” ትሁን የሚለውን አማራጭ ወደ መደገፍ ማዘንበላቸውን ምንጫችን ነግረውናል።
“ምክክሩ” ያለበት አሁናዊ ሂደት ምክረ ሀሳቦች ላይ ድምጽ የሚሰጥበት ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ሁለቱ አማራጮች ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገራቸው እርግጥ ሆኗል።
የመንግስት እና ገዢው ፓርቲ ተወካዮች አቋም
በአዲስ አበባ “ሕጋዊ አቋም” ዙሪያ “እነማን የትኛውን አቋም ያዙ?” የሚለው ጉዳይ በምክክር ሂደቱ አነጋጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል እንዱ ሲሆን፤ መንግስትን እና ገዢውን ብልጽግና ፓርቲ ወክለው በምክክሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ “ተመካካሪዎች” የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ መስተዋላቸውን ምንጮች ነግረውናል። አዲስ አበባ የፌደራል አካል ትሁን የሚለውን አማራጭ ደግፈው የተስተዋሉ የመንግስት እና የብልጽግና ፓርቲ ተወካዮች በርካታ መሆናቸውን የገለጡት ምንጫችን፤ የኦሮሚያ ክልል መንግስትን የወከሉ እንዲሁም በብልጽግና ፓርቲ ውክልና እየተሳተፉ የሚገኙ ሌሎች ተመካካሪዎች፤ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል አካል ትሁን” የሚለውን አማራጭ በጽኑ ደግፈው መስተዋላቸውንም ጠቁመዋል።
አንዱ አማራጭ ያመዘነበት የድሬዳዋ ጉዳይ
በድሬ ዳዋ ከተማ ጉዳይ የተደረገው “ምክክር” ከተማዋ “የፌደራል አካል ትሁን” የሚለው አማራጭ ሚዛን የደፋበት መሆኑን ሰምተናል። ለድሬ ዳዋ “ሲቲ ስቴት (ራስገዝ)”፣ “የፌደራል አካል”፣ “ራሷን የቻለች ክልል” የሚሉ አማራጮች መቅረባቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ ጉዳዩን አስመልክቶ በ“ጥቃቅን” ቡድን እና በ”ንዑስ” ቡድን ደረጃ በተደረገው ምክክር፤ “የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎች – የውይይት መሪ ጥያቄዎች” ሰነድ ላይ ለድሬ ዳዋ ከተማ የቀረቡ የ”ሕጋዊ አቋም” አማራጮች፣ ሌሎች አማራጮችን ሊያካትት ይገባ ነበር የሚል ጥያቄ ማስነሳቱን ሰምተናል። ከተማዋ “የኦሮሚያ ክልል አካል”፣ እና “የሶማሌ ክልል” አካል ትሁን የሚሉ አማራጮች መካተት አለባቸው የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሱ “ተመካካሪዎች” መኖራቸውን የገለጡልን ምንጫን፤ በአጀንዳ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከሰኞ ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደው የ”ምክክር” ሂደት፤ “ድሬ ዳዋ የፌደራል አካል ትሁን” የሚለው አማራጭ ሚዛን ደፍቶ መስተዋሉን ነግረውናል።
የተራዘመው የክልል ተወካዮች ጉባኤ አባላት ምርጫ
ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች እና ባለሙያዎች፤ በሥራ ቡድኖች ደረጃ የምክክር ሂደቱን አስመልክቶ ለ”ተመካካሪዎች” በሰጡት ማብራሪያ፤ የክልል ተወካዮች ጉባኤ አባላት እስከ ሐምሌ 18 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚመረጡ ገልጠው የነበረ ቢሆንም፤ ምርጫው ሳይካሄድ መቅረቱን ምንጮች ነግረውናል። በጉባኤው የአባልነት ውክልና ልናገኝ ይገባል የሚሉ ጥያቄዎች እየቀረቡ መሆናቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ ኮሚሽኑም እስካሁን የጉባኤው አባላትን ብዛትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ “የመጨረሻ” ያለውን ውሳኔ አላሳወቀም። ምርጫው ሐምሌ 20 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ በምክክሩ በአወያይነት እየተሳተፉ ለሚገኙ “ባለሙያዎች” ቢነገርም፤ ለምርጫው የተቀመጠው ቀን ጊዜያዊ መሆኑን ምንጫችን ነግረውናል።
ኮሚሽኑ የጉባኤው አባላት 211 እንደሚሆኑ ቀደም ብሎ ቢያሳውቅም፤ በቀረቡ ጥያቄዎች መሠረት ወደ 284 ከፍ ማለቱ ተነግሮ ነበር። የአባላቱ ቁጥር አሁንም ከፍ ማለቱ እንደማይቀር የጠቆሙት ምንጫችንም፤ የኮሚሽኑን 8 ኮሚሽነሮች ያቀፈው “የኮሚሽነሮች ምክር ቤት” የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አለመድረሱን ገልጠዋል። በሥራ ቡድን ደረጃ ምክረ ሀሳብ የሚደራጅበት ጊዜ ከመቃረቡ ጋር ተያይዞ የጉባኤው መቋቋም አስፈላጊ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ እስካሁን ምርጫው የሚደረግበትን ትክክለኛ ቀን ይፋ አላደረገም። [ዋዜማ]
