ዋዜማ- ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በ13ኛ ቀን ውሎው በ”ስልታዊ” ቡድኖች ደረጃ የሚካሄደውን “ምክክር” አስጀምሯል። 250 ተመካካሪዎችን የሚይዘው ቡድኑ አምስት “ንዑስ” ቡድኖችን ያቀፈ ሲሆን፤ አምስቱ ቡድኖች ያጠናቀሩትን ሰነድ ለ”ስልታዊ” ቡድኑ አባላት አቅርበዋል። ቡድኖቹ ባቀረቡት ሰነድ ዙሪያ ውይይት ከተካሄደ በኋላ የስልታዊ ቡድኑ የአጀንዳ “ምክረ ሀሳብ” እንደሚጠናቀር ይጠበቃል። ኮሚሽኑ ይህ ሂደት ሦስት ቀናት ይወስዳል የሚል ዕቅድ ቢይዝም፤ ከዕቅዱ ያለፈ ግዜ ሊወስድ እንደሚችል ዋዜማ ሰምታለች።
በጉባኤው የእረፍት ቀን ስብሰባ የጠራው ብልጽግ ናፓርቲ
ጉባኤው እሁድ ሐምሌ 19 ቀን፤ 2018 ዓ.ም ዕረፍት ቢያደርግም፤ ብልጽግና ፓርቲን ግን በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ “አባሎቹን” ሰብስቦ መዋሉን የዋዜማ ምንጮች ገልጠዋል። ምክክሩ እየተካሄደ በሚገኝበት አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የተካሄደው ስብሰባ፤ የፓርቲው “አባል” ለሆኑ ተመካካሪዎች “አቅጣጫ” የተሰጠበት መሆኑን ነግረውናል።
የክልልና የከተማ አስተዳደሮች አመራሮች በመሯቸው መድረኮች፤ በክልልና ከተማ አስተዳደር ደረጃ የተካሄደው ስብሰባ፤ ፓርቲው በምክክሩ አጀንዳዎች ዙሪያ የያዘውን “አቋም” ግልጽ ያደረገበት መሆኑን ሰምተናል። አጠቃላይ የምክክሩን ሂደት አስመልክቶ ገለጻ በማድረግና፤ ፓርቲው በምክክሩ አጀንዳዎች ላይ የያዘውን አቋም፣ “አባላቱ” ሊከተሉት ስለሚገባ አካሄድና ሌሎች ጉዳዮችን መሠረት ያደረገ ንግግር ያደረጉት የክልልና ከተማ አስተዳደር አመራሮች፤ ከዚህ ቀደም ከተሰጡ አቅጣጫዎች “ወጣ ያለ” እንቅስቃሴ አድርገዋል ያሏቸውን “ተመካካሪዎች” ማስጠቀቃቸውን ምንጮች ነግረውናል።
የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ጉዳይ
በአዲስ አበባ “ሕጋዊ አቋም” ዙሪያ የብልጽግና ፓርቲ አባላት ለሁለት መከፈላቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ በእሁዱ የፓርቲው ስብሰባ ትኩረት ከተሰጣቸው አጀንዳዎች መካከልም ይህ ጉዳይ አንዱ ነው። ፓርቲው ሁለቱ ከተሞች “የፌደራል አካል” ይሁኑ የሚለውን አማራጭ እንደሚደግፍ በተለያዩ አዳራሾች በተደረገው ዝግ ስብሰባ መገለጹን ሰምተናል። በአመራር ደረጃ ያሉና አዲስ አበባ “የኦሮሚያ አካል” ትሁን የሚለውን አማራጭ የደገፉ የፓርቲው አባላት ወቀሳ እና ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው የገለጡት ምንጮች፤ በዚህ አቋማቸው የሚቀጥሉ አመራሮች “ከቦታቸው እስከ መነሳት” የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል እንደተነገራቸው ጠቁመዋል።
በ”ስልታዊ” ቡድኖች ደረጃ በሚደረገው የምክክር ሂደት የፓርቲው “አባላት” አዲስ አበባ እና ድሬ ዳዋ ከተሞች “የፌደራል አካል” ይሁኑ የሚለውን አማራጭ በመደገፍ እንዲንቀሳቀሱ “ግልጽ” አቅጣጫ መሰጠቱን ያረጋገጡልን ምንጮች፤ በተዋረድ ያሉ አመራሮች የአቅጣጫውን አፈጻጸም እንዲከታተሉ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ነግረውናል።
ምክክሩን “አቋርጦ” እስከመውጣት አቅጣጫ የተሰጠበት ሰንደቅ ዓላማ
በ”ሀገር ግንባታ” አጀንዳ ውስጥ ከተካተቱ “ንዑስ” አጀንዳዎች መካከል የ“ሀገራዊ ምልክቶችና መገለጫዎች” ጉዳይ አንዱ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ለ”ንዑስ” አጀንዳው ካዘጋጃቸው “መሪ” ጥያቄዎች አንዱ “የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ (ቀለማቱ እና አርማው)፣ ብሔራዊ መዝሙር እና በዓላት፤ ሁሉንም ማህበረሰቦች ወካይ እንዲሆኑ ምን መለወጥ ያስፈጋል?” የሚል ነው። ተመካካሪዎች ይህን “መሪ” ጥያቄ መነሻ አድርገው ባካሄዱት “ምክክር” የተለያዩ አማራጭ “ሀሳቦችን” አቅርበዋል። ሰንደቅ ዓላማው “ሙሉ በሙሉ ይቀየር”፣ “የመደቡ ቀለማት ይጨመሩ”፣ “አርማው” ይቀየር የሚሉና ሌሎች አማራጮች በምክክር ሂደቱ መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች መካካል ይገኝበታል።
ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ “የመደብ” ቀለማት ጉዳይን ለድርድር የማያቀርበው መሆኑን በስብሰባው “አቅጣጫ” እንደተሰጠበት የገለጡት ምንጫችን፤ በዚህ ጉዳይ “ምክክር” በሚደረግበት ወቅት ምክክር “አቋርጦ” እስከመውጣት የሚደርስ “ጽኑ” አቋም የሚያዝበት ጉዳይ መሆኑ ስለመነገሩ አረጋግጠውልናል። በሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው “አርማ” አሁን ባለበት ይቀጥል የሚለው በፓርቲው የሚደገፍ “አቋም” ቢሆንም፤ እንደ “መደብ ቀለማቱ” ጥብቅ “አቅጣጫ” የተሰጠበት አለመሆኑን ሰምተናል።
ፕሬዝዳንታዊ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት
በ“መንግስት አደረጃጀት እና ቅርጽ” አጀንዳ ውስጥ የሚገኘው “የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ዓይነት” ንዑስ አጀንዳ ከተዘጋጁለት “መሪ” ጥያቄዎች መካከል፤ “ፓርላሜንታዊ”፣ “ፕሬዝዳንታዊ”፣ አልያም “የሁለቱም ቅይጥ” የመንግስት አስተዳደር ሥርዓትን እንደ አማራጭ ያቀረበው ጥያቄ አንዱ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል። ብልጽግና ፓርቲ “ፕሬዝዳንታዊ” የመንግስት አስተዳደር ሥርዓትን “ምርጫው” እንዳደረገ የገለጡልን ምንጮችም፤ በእሁድ ዕለቱ ስብሰባ “አቅጣጫ” የተሰጠበት ሌላኛው ጉዳይ መሆኑን ነግረውናል።
ድጋፍ ያገኙት የማንነትና አስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎች
በምክክሩ ሂደት ውስጥ “አነጋጋሪ” ከሆኑ ጉዳዮች መካከል፤ የማንነትና አስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎች የሚጠቀሱ ሲሆን፤ በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ “እየተመካከሩ” የሚገኙ የባለድርሻ አካላት ተወካዮች የተለያዩ “የማንነትና አስተዳደር መዋቅር” ጥያቄዎችን እያነሱ መሆናቸውን ሰምተናል። ብልጽግና ፓርቲ ባደረገው ስብሰባ፤ ለመሰል ጉዳዮች ፓርቲው ያለውን አቋም አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረቡ የፓርቲው “አባላት”፤ ፓርቲው የማንነትና አስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎች መነሳታቸውን “እንደሚደግፍ” የሚጠቁም ምላሽ ማግኘታቸውን ከምንጮች አረጋግጠናል።
ይህ ጉዳይም በፓርቲው አባላት መካከል “ልዩነት” የፈጠረ መሆኑን የገለጡልን ምንጮች፤ በምክክሩ የተነሱ የማንነትና አስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎችን በጽኑ የተቃወሙ የፓርቲው አባላት መኖራቸውን ነግረውናል። ይህ ጉዳይ ፓርቲው በቀጥታ አቅጣጫ ከሰጠባቸው አጀንዳዎች መካከል ባይሆንም፤ ከፓርቲው አባላት ጉዳዩን አስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄ መልስ የሰጡ “ከፍተኛ አመራሮች” በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ “ተቃውሞ” እንደሌለ ማሳወቃቸውን ሰምተናል።
በማደሪያ ቦታዎች የሚደረጉ ስብሰባዎች
ብልጽግና ፓርቲ እሁድ ዕለት “በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል” በሰፊው ካካሄደው ስብሰባ በተጨማሪ፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለ”ተመካካሪዎች” ባዛጋጃቸው የማደሪያ ቦታዎች “አነስተኛ” ስብሰባዎች እንደሚካሄዱ ሰምተናል። በእነዚህ ስብሰባዎች በዕለታዊና “ድንገተኛ” ጉዳዮች ዙሪያ ለ”ተመካካሪዎች” ገለጻ እንደሚሰጥ የነገሩን ምንጮች፤ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አመራሮች በተሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት ለተመካካሪዎች “አቅጣጫ” እንደሚሰጡ ገልጠዋል።
“ማስታወሻ” ደብተር የያዙ ተመካካሪዎች
በ”ጥቃቅን” ቡድን እንዲሁም በ”ንዑስ” ቡድን ደረጃ በተካሄዱ “ምክክሮች” በ”ማስታወሻ ደብተር” የተጻፉ ጽሑፎችን “እያነበቡ” አስተያየት የሚሰጡ “ተመካካሪዎችን” ማስተዋላቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ በአንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ መሰል “ዝግጅት” የተደረገባቸው “ጽሑፍ መር አቋሞች”ን መመልከታቸውን ገልጠዋል። በአጀንዳዎች ዙሪያ በተካሄዱ የ”ምክክር” ሂደቶች በተነሱ ሀሳቦች ላይ “ተመካክሬ አስተያየት እሰጣለሁ” የሚሉና “ከሻይ” እንዲሁም “ከምሳ” እረፍቶች በኋላ “የተመካከሩበትን” አስተያየት የሚሰነዝሩ መኖራቸውንም ሰምተናል።
ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ በተጨማሪ ሌሎች “የተደራጀ” እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቡድኖች ስለመኖራቸው አክለው የነገሩን ምንጮች፤ በ“ማህበራዊ ሚዲያ” አማራጮች በተከፈቱ መወያያ “ግሩፖች” እንዲሁም በጽሑፍ በሚሰራጩ መረጃዎች አማካኝነት፤ “የተናበበ” ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጠዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እስካሁን በመሰል እንቅስቃሴዎች ዙሪያ የሰጠው መግለጫም ሆነ ያጋራው መረጃ የለም። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ሐምሌ 16 ቀን፤ 2018 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “በማህበራዊ ሚዲያዎች ያልተረጋገጡ መረጃዎች እየተሰራጩ ነው” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ሌሎች የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ደግሞ “ያልተረጋገጡ” ያሏቸው መረጃዎች “ባሰራጩ” ተመካካሪዎች ላይ “እርምጃ” እንደሚወሰድ ለ”ተመካካሪዎች” ገለጻ በተሰጠባቸው መርሃግብሮች ላይ ገልጸው ነበር። ይሁንና በዋና ኮሚሽነሩም መግለጫ ሆነ በሌሎች ኮሚሽነሮች ገለጻ፤ “መደበኛ ያልሆኑትን” አደረጃጀቶች አስመልክቶ የተባለ ነገር የለም። [ዋዜማ]
