• በምክክሩ ከፍተኛ ሚና ባለው የክልል ጉባዔ የአባላት ቁጥር 211 የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 284 አድጓል
  • የስነምግባር ጥሰት የፈፀመ ተሳታፊ ከመታገድ እስከመባረር የደረሰ ቅጣት ይጠብቀዋል
  • የምክክሩን የስድስተኛ ቀን ሂደት ዋዜማ እንደሚከተለው አስናድታዋለች

ዋዜማ-ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስድስተኛ ቀኑ፣ በስምንቱ አጀንዳዎች ዙሪያ “ምክክር” ማድረግ ጀምሯል። ጉባኤው ሐምሌ 08 ቀን፤ 2018 ዓ.ም የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱን ካደረገ በኋላ፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን “ቴክኒካዊ” ባላቸው ጉዳዮች ምክንያት በአጀንዳዎቹ ዙሪያ “ምክክር” ሳይጀምር ቆይቷል። ከሐምሌ 13 ቀን፤ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ፤ 500 “ተመካካሪዎችን” የሚይዘው “የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን” 50 ተመካካሪዎችን ወደሚይዙ 10 “ንዑስ” ቡድኖች ተከፍሎ በተመደቡለት አጀንዳዎች ዙሪያ መመካከር መጀመሩን ኮሚሽኑ አስታውቋል። በዚህም በአጠቃላይ 80 “ንዑስ” ቡድኖች ምክክር በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በነዚህ ቡድኖች የሚደረገውን ”ምክክር” እንዲያስተባብሩ 160 “አወያዮች” እና 256 “የቃለ ጉባኤ ጸሐፊዎች” መሰማራታቸውም ተነግሯል። 

በንኡስ ቡድኖች ሥር 10 አባላትን የሚይዙ አምስት  “ጥቃቅን” ቡድኖች ተመስርተው የምክክር ሂደቱ እንደሚጀመር ኮሚሽኑ ያዘጋጀው “የሥራ ቡድን የምክክር ስልት” የሚል ርዕስ የተሰጠው ሰነድ የሚያመላክት ሲሆን፤ በ”ጥቃቅን” ቡድን ደረጃ “ምክክር” መጀመሩን ዋዜማ ሰምታለች።

ኮሚሽኑ “ተመካካሪዎች“ በተመደቡላቸው አጀንዳዎች ዙሪያ “ሃሳብ እንዲያመነጩ” ያስችሉልኛል ያላቸውን “የውይይት መሪ ጥያቄዎች” የያዘ ሰነድ ማቅረቡን የገለጡ የዋዜማ ምንጮች፤ በመሪ ጥያቄዎች ላይ የተመሰረተ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ነግረውናል። 

“መሪ ጥያቄዎችን” የያዘው ሰነድ  

የምክክር ጉባኤው በስምንት አጀንዳዎች ዙሪያ “እንደሚመካከር” ኮሚሽኑ ቀደም ብሎ ማሳወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ በነዚህ አጀንዳዎች ውስጥ የተካተቱ ንዑስ አጀንዳዎችም “የምክክሩ” አካል ናቸው።“በጥቃቅን ቡድኖች” ደረጃ የተጀመረው “ምክክር” ለንዑስ አጀንዳዎች በተቀመጡ “መሪ ጥያቄዎች” መሠረት  እንዲከናወን፤ ኮሚሽኑ ምክክሩን “ይመሩልኛል” ብሎ ባዘጋጃቸው “አወያዮች” በኩል ትዕዛዝ አስተላልፏል።

17 ንዑስ አጀንዳዎችን የያዘው “የመንግስት አደረጃጀት እና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት” አጀንዳ፣ 16 ንዑስ አጀንዳዎችን የያዙት “የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶች” እንዲሁም “ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የአርሶ አደሮች እና የአርብቶ አደሮች ጉዳዮች” አጀንዳዎች፣ 9 ንዑስ አጀንዳዎችን የያዘው ”የፌደራል ከተሞች ጉዳይ” አጀንዳ፣ 7 ንዑስ አጀንዳዎችን የያዘው ”የሀገር ግንባታ” አጀንዳ፣ 6 ንዑስ አጀንዳዎችን የያዘው “የሰላም ግንባታ አጀንዳ”፣ 4 ንዑስ አጀንዳዎችን የያዙት “የሃይማኖት ጉዳዮች” እንዲሁም “የሙስና እና መልካም አስተዳደር” አጀንዳዎች፤ “መሪ ጥያቄዎች” የተዘጋጁላቸው ሲሆን፤ በርካታ ንዑስ አጀንዳዎች ያሏቸው አጀንዳዎች በርካታ ጥያቄዎች እንደተዘጋጁላቸው ከሰነዱ ተመልክተናል።

በመረጧቸው አጀንዳዎች ላይ እንዲወያዩ የተፈቀደላቸው ፓርቲዎች

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ አግኝተው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ፓርቲዎች አራት ተወካዮቻቸውን በምክክሩ እንዲያሳትፉ ቢወሰንም፤ በርካታ ፓርቲዎች “አራቱም ተወካዮቻችን በአንድ አጀንዳ ላይ እንዲወያዩ ተመድበዋል” የሚል ቅሬታ ለኮሚሽኑ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ኮሚሽኑ መሰሉን “ችግር” እንደሚያስተካክል በሰጠው ምላሽ መሰረት፤ ጥያቄ ያቀረቡ ፓርቲዎች በመረጧቸው አጀንዳዎች ላይ እንዲሳተፉ መደረጉን ነግረውናል። በዚህም ፓርቲዎች ተወካዮቻቸውን በመረጧቸው አራት አጀንዳዎች ላይ እንዲሳተፉ እያደረጉ መሆናቸው ታውቋል። በተለይም “የሀገር ግንባታ”፣ “የመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት” እና “የፌደራል ከተሞች ጉዳይ” አጀንዳዎች የፓርቲዎችን ትኩረት ያገኙ መሆናቸውን ምንጮች ገልጠዋል።

ከ50 በላይ ተመካካሪዎችን ያስተናገዱት “ንዑስ ቡድኖች”

አንድ ንዑስ ቡድን 50 ተመካካሪዎችን እንዲያስተናግድ በኮሚሽኑ ቢወሰንም፤ አንዳንድ ንዑስ ቡድኖች ግን እስከ 60 የሚደርሱ ተመካካሪዎችን መያዛቸውን ምንጮች ነግረውናል። ይህ የሆነበትን ምክንያት የሚያስረዱት ምንጮች፤ የፓርቲ ተወካዮች “አንገብጋቢ” ባሏቸው አጀንዳዎች ዙሪያ ለመምከር በቅድሚያ የተመደቡበትን የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን እየለቀቁ ወደ መረጡት “ቡድን” እየተቀላቀሉ መሆናቸውን አንስተዋል። ከ50 በላይ ተመካካሪዎችን የያዙ “ንዑስ” ቡድኖች የመኖራቸውን ያህል አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ተመካካሪዎች የያዙ ቡድኖች መኖራቸውንም ሰምተናል። 

ማሻሻያ የተደረገበት “የክልል ተወካዮች ጉባኤ”

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በምክክር ጉባኤ ውሳኔ አሰጣጥ ዙሪያ ከፍተኛ ሚና ባለው የክልል ተወካዮች ጉባኤ አወቃቀር ላይ ለውጥ ማድረጉን ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል። እያንዳንዱ ክልልና ከተማ አስተዳደር 14፣ የፌደራል መንግስት ደግሞ 15 ተወካዮችን በመወከል በድምሩ 211 አባላት እንደሚኖሩት ተነግሮለት የነበረው ጉባኤ፤ የአባላቱን ቁጥር ወደ 284 የሚያሳድግ ማሻሻያ እንደተደረገበት ምንጮች ነግረውናል።

የለውጡ ምክንያት “በተለያዩ አካላት የቀረቡ አስተያየቶች” መሆናቸውን የጠቆሙ ምንጮች፤ “ተጽዕኖ ፈጣሪ” በሚል በምክክሩ የተካተቱ “ተመካካሪዎች” በጉባኤው ውክልና ልናገኝ ይገባል የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ማሻሻያው እንደተደረገ ጠቁመዋል። በዚህም “ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” በእያንዳንዱ ክልልና ከተማ አስተዳደር፣ እንዲሁም በፌደራል ደረጃ የሶስት ሰዎች ውክልና እንዲኖራቸው መደረጉን ሰምተናል። በድምሩ 45 “ተጽዕኖ ፈጣሪ” በሚል ውክልና በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች በጉባኤው እንዲሳተፉ የሚያደርገው ማሻሻያው፤ ለክልሎች የተጨመሩ የሴቶች ተወካዮች ኮታን እና ሌሎች ማሻሻያዎችን ጨምሮ 73 ተጨማሪ የጉባኤ አባላትን እንዲያካትት መደረጉ ተነግሯል።

ይህ ማሻሻያ ለተመካካሪዎች በተሰጠው “የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የውሳኔ አሰጣጥ” ሰነድ ላይ ያልተካተተ ሲሆን፤ ለተመካካሪዎች በቃል ደረጃ መነገሩን ሰምተናል።

መንግስት የሚያገኛቸው መቀመጫዎች ብዛት

የፌደራል እንዲሁም የክልል መንግስታት በክልል እና ፌደራል ደረጃ እያንዳንዳቸው 4 ተወካዮችን ከመያዛቸው ጋር በተያያዘ ከ284ቶቹ የጉባኤው አባላት 60ዎቹ በቀጥታ የመንግስት ተወካዮች ናቸው። ይህም ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል አንጻር የመንግስት ተወካዮች ከፍተኛውን መቀመጫ እንዲይዙ አድርጓቸዋል።

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ደግሞ በእያንዳንዱ ክልልና ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በፌደራል ደረጃ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከተሰጠው የአራት ወንበር ኮታ (በድምሩ 60 ወንበር) ውስጥ፤ ተጨማሪ ወንበሮችን የማግኘት እድል አለው። በወጣቶች፣ ሴቶች እና በሌሎች አደረጃጀቶች አማካኝነትም ገዢው ፓርቲ ተጭማሪ ወንበሮችን የሚያገኝበት ዕድል ያለ ሲሆን፤ በሁሉም ክልሎች ያሉ መንግስታትን የመሰረተው ብልጽግና ፓርቲ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ ፓርቲው በጉባኤው ከፍተኛ ውክልና ያለው እንዲሆን ያስችለዋል።

በዚህ ሳምንት የሚካሄደው “ምርጫ”

የክልል ተወካዮች ጉባኤ አባላትን ለመለየት በዚህ ሳምንት “ምርጫ” እንደሚካሄድ የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል። የጉባኤው አባላት “ምርጫ” የሚካሄደው በክልልና ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በፌደራል ደረጃ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፤ አንድን ክልል ወይም ከተማ አስተዳደር ወክለው በምክክሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎች ተሰብስበው በተሰጠው ኮታ መሰረት ተወካዮቻቸውን እንዲመርጡ እንደሚደረግ ነግረውናል። ኮሚሽኑ እስካሁን ስለምርጫው ሂደት ይፋ ያደረገው መረጃ የለም።

ይህ የክልል ተወካዮች ጉባኤ በምክክሩ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ያነሱ ተመካካሪዎች፤ ምርጫው በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲካሄድ ለኮሚሽነሮች ጥያቄ ማቅረባቸውን ምንጮች ጠቅሰዋል። ኮሚሽነሮችም ምርጫው የሚካሄደው በክልል ደረጃ መሆኑን በማንሳት፤ ተመካካሪዎች ተወካዮቻቸውን በአግባቡ እንዲመርጡ ማሳሰቢያ መስጠታቸውን ምንጮች ነግረውናል።

ተመካካሪዎችን እስከ “ማገድ”የሚደርሰው የሥነ ምግባር መመሪያ

ለተመካካሪዎች  ማብራሪያ የተሰጠበት “የተመካካሪዎች የሥነ ምግባር መመሪያ” አንድን ተመካካሪ “በግዜያዊነት” ወይም “ሙሉ በሙሉ” ከምክክር ሂደቱ እንዲወጣ የሚደረግበትን አንቀጽ አካቷል። ተመካካሪዎች ከምክክር ሂደቱ እንዲታገዱ የሚያደርጉ ምክንያቶች ተብለው ከተለዩ ጉዳዮች መካከልም፤ “የሀገርን ክብር የሚነኩ እና ሰላምና ጸጥታን የሚያውኩ ንግግሮች”፣ “የጥላቻ፣ አዋራጅ እና ተንኳሽ ንግግሮችን ማድረግ”፣ “ሁከትን የሚፈጥሩና መረጋጋትን የሚከለክሉ ንግግሮችን ማድረግ”፣ “ሌሎች ተመካካሪዎችን መነካካት፣ መጎሻሸም እና ግልጽ የጥላቻ የፊት ገጽታ” የሚሉት ተዘርዝረዋል። እነዚህን ተግባራት ለፈጸሙ ተመካካሪዎች፤ ኮሚሽኑ የመደባቸው “አወያዮች” በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጧቸው የሚገልጸው መመሪያው፤ ከማስጠንቀቂያ በኋላ ከምክክሩ ሊታገዱ እንደሚችሉ ይጠቅሳል። የምክክር ሂደቱን “የሚያስተባብሩ” ኮሚሽነሮች “የሥነ ምግባር ጉድለት” የታየባቸውን “ተመካካሪዎች” ከምክክር ሂደቱ ሙሉ ለሙሉ የማገድ ስልጣን እንዳላቸውም በመመሪያ ተመላክቷል። ኮሚሽነሮች ጉድለት አሳይተዋል ያሏቸውን ተመካካሪዎች “እንደየሁኔታው” በግዜያዊነት ለቀናት የሚዘልቅ እገዳ እንዲሁም፤ ሙሉ በሙሉ ከምክክሩ ማገድ እንደሚችሉ ነው መመሪያው የደነገገው። [ዋዜማ]