
ዋዜማ- የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱን ያካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፤ በስምንቱ አጀንዳዎች ዙሪያ ምክክር ማድረግ ሳይጀምር ሶስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል። 4 ሺሕ ተሳታፊዎችን በስምንት ቡድኖች ከፋፍሎ ምክክሩን ለማከናወን ያቀደው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ ከተሳታፊዎች ቅሬታ እየቀረበበት መሆኑንም የዋዜማ ምንጮች ገልጠዋል። በምክክሩ እየተሳተፈ የሚገኝ “ተመካካሪ”፤ በተመደበት የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን አማካኝነት በአንድ አጀንዳ ላይ ብቻ እንዲመካከር የተቀመጠው አሠራር ዋና የቅሬታ ምንጭ መሆኑንም ሰምተናል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችን እና በተጽዕኖ ፈጣሪነት የተመረጡ ተመካካሪዎችን ጨምሮ በርካቶችን በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን ቅሬታ ለኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ማቅረባቸውን የገለጡት ምንጮች፤ ኮሚሽነሮች “ሁሉም የሥራ ቡድኖች ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸው ይደረጋል” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
የተመካካሪ መታወቂያ ያላገኙ ተመካካሪዎች
የፌደራል መንግስት አደረጃጀትን እንዲሁም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው በምክክሩ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከከተሙ ተሳታፊዎች መካከል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩት አሁንም በምክክሩ መሳተፍ የሚያስችላቸውን መታወቂያ ማግኘት አለመቻላቸውንም ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ቀደም ሲል ባወጣው መርሃ ግብር መሠረት ለተመካካሪዎች መታወቂያ አድሎ የሚጨርሰው ማክሰኞ ሐምሌ 07 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ነበር። ይሁንና “መታወቂያ አልታተመም፣ አንዳንድ ተቋማት በምክክሩ እንዲሳተፉ የወከሏቸው ተመካካሪዎች ዝርዝር ለኮሚሽኑ አልደረሰም፣ ለተሳታፊዎች የተቀመጠው ኮታ ሞልቷል” በሚሉና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ፤ እስከ አርብ ሐምሌ 09 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የተሳታፊነት መታወቂያ ያልደረሳቸው “ተመካካሪዎች” መኖራቸውን ምንጮች ነግረውናል።
የትግራይ ክልል ተመካካሪዎች
ኮሚሽኑ በ11 ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ተግባራዊ ያደረገ ቢሆንም፤ የትግራይ ክልል አጀንዳን ግን ወደ ክልሉ አቅንቶ ማሰባሰብ አለመቻሉን ማስታወቁ ይታወሳል። ኮሚሽኑ “ከትግራይ ክልል በመጡና በአዲስ አበባ ከሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆች” ጋር በአዲስ አበባ ከመጋቢት 23 እስከ 25 ቀን ድረስ በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፤ የክልሉን አጀንዳዎች በምክክር ሂደቱ ማካተቱን ገልጧል። በሀገራዊ የምክክር ጉባኤውም ትግራይ ክልልን ለሚወክሉ ተመካካሪዎች ጥሪ ማድረጉን መግለጹ ይታወሳል።
“ከኮሚሽኑ በደረሰን ጥሪ መሰረት በምክክር ጉባኤው ለመሳተፍ መጥተናል” ያሉ የክልሉ ተወላጆች ግን፤ በምክክሩ መሳተፍ የሚያስችላቸውን መታወቂያ ማግኘት አለመቻላቸውን ለዋዜማ ገልጠዋል። የኮሚሽኑ ባልደረቦች ስልክ በመደወልና የጽሑፍ መልዕክት በመላክ ለምክክር ጉባኤው ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ እንደጋበዟቸው የገለጡና፣ በትግራይ ክልል በሚገኝ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ውስጥ እንደሚሠሩ የተናገሩ ግለሰብ፤ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው አዲስ አበባ ከገቡና ኮሚሽኑም በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ማረፊያ ከሰጣቸው በኋላ፤ “ስምህ በዝርዝር ውስጥ የለም” ተብለው የተመካካሪነት መታወቂያ ሳይሰጣቸው መቅረቱን ነግረውናል።
መሰሉ ሁኔታ ሌሎች ሰዎችንም እንዳጋጠማቸው የገለጡት ግለሰቡ፤ “ለትግራይ ክልል የተሰጠው ኮታ ተሟልቷል” የሚል ምላሽ ከኮሚሽኑ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። በምክክሩ እንዲሳተፉ ጥሪ የደረሳቸው ግለሰቦች በምን አይነት መስፈርት እንደተመረጡ እንደማያውቁ አክለው ያነሱት ምንጫችን፤ “ኮታው ሞልቷል” የሚለው ምላሽ የመጣው የኮሚሽኑ ሠራተኞች በርካታ ግለሰቦችን ለምክክሩ “ጋብዘው” ከመሆኑ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ጠቁመዋል። ከትግራይ ክልል ተሳታፊዎች ባለፈም የሌሎች ክልልና ከተማ አስተዳደር ተወካዮችም ተመሳሳይ ችግር እንዳጋጠማቸው ሰምተናል።
የኮሚሽኑ ማጣሪያ
ለክልሎች እንዲሁም ለተቋማት የተሰጠው ኮታ “ተሟልቷል” በሚል የተመካካሪዎች መታወቂያ ያላገኙ፤ ነገር ግን ለተመካካሪነት ተመርጠው ከኮሚሽኑ ጥሪ የቀረበላቸው ግለሰቦች፤ “የኛን ኮታ ማን ወስዶት ነው?” በሚል ላቅረቡት ጥያቄ፤ “ያለ አግባብ የተመካካሪነት መታወቂያ የወሰደ አካል ካለ አጣርተን እርምጃ እንወሳዳለን” የሚል ምላሽ ከኮሚሽኑ አስተባባሪዎች ማግኘታቸውን ምንጮች ነግረውናል።
ኮሚሽኑ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባወጣው ማሳሰቢያ፤ በክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ በፌደራል ደረጃ እንዲሁም በዲያስፖራው ማህበረሰብ በተካሄዱ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች፤ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ወኪሎችን ማስመረጡን በማስታወስ፤ በእነዚህ ሂደቶች ያልተመረጡ ግለሰቦች “በጉባኤው ለመሳተፍ የመሻት አዝማሚያ” ማሳየታቸውን መግለጡ ይታወሳል። ኮሚሽኑ በማሳሰቢያው በጉባኤው እንዲሳተፉ ያልተመረጡ፣ በኮሚሽኑ ጥሪ ያልደረሳቸውና ስማቸው በኮሚሽኑ ቋት ውስጥ የሌለ ግለሰቦችን እንደማያስተናግድ አስታውቆ ነበር።
የተመካካሪዎች እንግልት
የተመካካሪ መታወቂያ ያልደረሳቸው “ተመካካሪዎች” በቂ መረጃ የሚሰጣቸውና በአግባቡ የሚያስተናግዳቸው አካል ማጣታቸውን ምንጮች ነግረውናል። ከማክሰኞ ሐምሌ 07 ቀን፤ 2018 ዓ.ም ዕለት ጀምሮ የተመካካሪ መታወቂያ ለማግኘት እየጣሩ መሆናቸውን የገለጡ አንድ “ተመካካሪ” ተገቢውን መረጃ የሚሰጥና፤ በሥርዓት የሚያስተናግዳቸው አስተባባሪ ማጣታቸውን አስረድተውናል። ኮሚሽኑ ተመካካሪዎችን የሚያስተናግዱ በቂ ሠራተኞችን “መድቧል” ብለው እንደማያምኑ የገለጡት ምንጫችን፤ የተመካካሪ መታወቂያ “ሲያድሉ” የነበሩ የኮሚሽኑ ሠራተኞች፤ ተመካካሪዎችን “ለዕንግልት” መዳረጋቸውን ጠቁመዋል።
ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት “ኮንቬንሽን ማዕከል”
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተመካካሪዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥበቃ እንደሚደረግ ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ ለተመካካሪዎች በተሰጠው የምክክር ሂደት ማብራሪያ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት የስብሰባውን ቦታ ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው ተገልጧል። ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው እንዲካሄድበት የተመረጠው በአዲስ አበባ በተለምዶ “የተባበሩት” በሚል በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው “አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል” ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት የሚገኝ ሲሆን፤ የማዕከሉን መግቢያ በሮች የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ባልደረቦች እየተቆጣጠሩት እንደሚገኙ ምንጭች ነግረውናል።
በማዕከሉ መግቢያ በሮች ባለው ጥብቅ ቁጥጥር የተነሳ፤ የኮሚሽኑን ሠራተኞች ጨምሮ፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ሌሎች በተለያየ ሚና የመግቢያ መታወቂያ (ባጅ) የተሰጣቸው ባለድርሻዎች ወደ ማዕከሉ ለመግባት መቸገራቸውን ሰምተናል። ከኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች መካከል አንዷ ወደ ማዕከሉ ለመግባት ተቸግረው እንደነበር ማስተዋላቸውን የገለጡልን ምንጫችን፤ የትኛው ባለድርሻ አካል በየትኛው መግቢያ በር መግባት እንዳለበት በግልጽ አለመታወቁ እንግልት ማስከተሉን ነግረውናል።
ራሳቸውን ከምክክሩ ያገለሉ “ተመካካሪዎች”
አንድ ተመካካሪ በአንድ አጀንዳ ላይ ብቻ እንደሚመካከር መነገሩን ተከትሎ ለኮሚሽኑ ከቀረቡ ቅሬታዎች ባሻገር፤ በዚህ ምክንያት የተነሳ ራሳቸውን ከምክክር ሂደቱ ማግለላቸውን ሁለት ግለሰቦች ለዋዜማ ተናግረዋል። መገናኛ ብዙኃንን ወክለው በምክክሩ ለመሳተፍ መመረጣቸውን የነገሩን ግለሰብ “30 ቀናት ያህል በአንድ አጀንዳ ላይ ብቻ እንድንመካከር ለማድረግ መታቀዱ ትክክል አይደለም፤ ሁሉም አጀንዳዎች ላይ እንድንመካከር መደረግ ነበረበት” ያሉ ሲሆን፤ በዚህ ምክንያት ራሳቸውን ከሂደቱ ማግለላቸውን ገልጠዋል። ተጽዕኖ ፈጣሪ ተብለው በምክክሩ እንዲሳተፉ መመረጣቸውን የነገሩን ሌላ ግለሰብም ተመሳሳዩን ምክንያት በማንሳት በምክክሩ ላለመሳተፍ መወሰናቸውን አረጋግጠውልናል።
መዘግየት
ምንም እንኳን ረቡዕ ሐምሌ 08 ቀን፤ 2018 ዓ.ም የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ቢካሄድም፤ የምክክር ጉባኤው ግን እስከ አርብ ሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ አልተጀመረም። ተመካካሪዎች አጀንዳዎች ላይ ምክክር በሚደረግበት ሥርዓት ላይ ያቀረቡት ጥያቄ፣ ጥቂት የማይባሉ ተመካካሪዎች መታወቂያ ማግኘት አለመቻላቸው፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የምክክር ጉባኤው በጊዜው እንዳይጀመር ማድረጋቸውን ምንጮች ነግረውናል። [ዋዜማ]