ዋዜማ-የአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ድርጅት (USAID) በስልጣን ላይ ባለው የአሜሪካ አስተዳደር ከተዘጋና አለማቀፍ ድጋፉን ካቋረጠ አንድ ዓመት ደፈነ። በአለም ከልማት ድርጅቱ ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኝ የነበረችው ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት እስከ 13 በመቶ በጀቷን ከዚሁ ድጋፍ ታገኝ ነበር። በኢትዮጵያ ስልሳ አመታትን ያስቆጠረው ዩኤስ ኣይ ዲ በመዘጋቱ በጤና፣ በትምህርትና በግብርና ዘርፍ የተከሰቱ መጓደሎችን ከዓመት በኋላ ተመልሰን ከድጋፉ ተጠቃሚ የነበሩትን አካላት አነጋግረን ይህን ዘገባ አዘጋጅተናል።
በቀደሙት ሀያ አመታት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ 17 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ አግኝታለች። በዓመት እስከ 1.3 ቢሊየን ዶላር ተቀባይም ነበርን።
የአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስ አይ ዲ) እ.ኤ.አ ጥር 15 ቀን 2025 በዓለም ዙሪያ የሚሰጠውን የውጭ እርዳታ በድንገት ማገዱን ተከትሎ በኢትዮጵያ ለዘመናት የተገነቡ ሰብአዊ ፕሮጀክቶች በአንድ ጀምበር አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡ ውሳኔውን ዛሬ ላይ ሆኖ ወደ ኋላ ለሚመለከተው ፤ በኢትዮጲያ መጠነ-ሰፊ ዘርፎች ፤ በተለይም በጤና፣ በትምህርት እና የአደጋ ስጋት ምላሽ ዘርፍ ላይ በቀውስ ደረጃ የሚገለጽ ጥልቅ ችግር የፈጠረ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ከአንድ ሚሊየን የሚልቁ ስደተኞችና ተፈናቃዮች የዕለት ደራሽ እርዳታ ተቋርጦባቸዋል። መንግስት ከጎረቤት ሀገራት ተሰደው በኢትዮጵያ ለሚገኙና አዲስ ለሚመጡ ስደተኞች ምግብና መሰረታዊ አገልግሎት ለማቅረብ እንደተሰናው ከወራት በፊት ይፋ አድርጓል። የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ተቋማትም እንዲሁ ከአሜሪካ መንግስት የሚቀበሉት ድጋፍ በመቋረጡ የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት አቅማቸው መመናመኑን አሳውቀዋል።
የድርጅቱ መዘጋት በአፍሪቃ በቅርብ እስከ ሶስት ሚሊየን በቀጣዮቹ አመታት ደግሞ እስከ ሰባት ሚሊየን ሰዎች ህይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉበትን ቀዳዳ ከፍቷል። ሀገራችንም የዚህ አስከፊ ትንበያ አካል ናት።
የጤናው ዘርፍ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ
የእርዳታው መቋረጥ በተሰማ በሳምንታት ውስጥ የካቲት 24 ቀን 2025 በተለያዩ የጤና ተቋማት እንዲሁም ጤናን ማእከል ባደረጉ ፕሮጀክቶች ውስጥ ዩኤስ አይ ዲ በመደበው በጀት ስር ተቀጥረው የነበሩ 15 ሺህ የጤና እና የዳታ ባለሙያዎች ውላቸው እንዲቋረጥ ሆኗል፡፡
ይህ በሰራተኞች ውል መቋረጥ ብቻ አላበቃም፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ፕሮግራም ሚያዚያ 8 ቀን ፤ 2025 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት፤ በአዲስ አበባ የሚገኘው ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታልን የመሳሰሉ ግዙፍ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የሕክምና ማዕከል ያላቸው የመንግስት ሆስፒታሎች፤ የታካሚዎችን መረጃ መመዝገብና መድኃኒት ያቋረጡ ሰዎችን መከታተል ፈታኝ ሆኖባቸዋል።
በሆስፒታሉ የረጅም ጊዜ ታካሚ የሆኑት ወ/ሮ አስቴር (ለታሪኩ ሲባል ስማቸው የተቀየረ) ሁኔታውን ሲያብራሩ፤ “ከዚህ ቀደም መድኃኒት ብቻ ሳይሆን በባዶ ሆዳችን መድሃኒት እንዳንወስድ የተመጣጠነ ምግብ ይሰጡን ነበር፤ አሁን ግን መድኃኒቱን በባዶ ሆዳችን ለመውሰድ ተገደናል፤ መድሃኒቱ በባዶ ሆድ ሲወሰድ ደግሞ ያዞራል፤ ያቅለሸልሻል›› ይላሉ፡፡
ሚያዝያ 08 ቀን 2025 ዩኤን ኤድስ (UNAIDS) ባወጣው መግለጫ፣ ከ500 ሺህ በላይ ታካሚዎች የጸረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒትን የማጣት ስጋት እንደተጋረጠባቸው አስጠንቅቆም ነበር።
ሌላኛው የድጋፉ መቋረጥ ያስከተለው ችግር የሚታየው በላብራቶሪ ግብአቶች ላይ ነው፡፡ በሀገሪቱ ትልቁ በሆነው ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለካንሰር ታካሚዎች አስፈላጊ የሆኑ የምርመራ ኬሚካሎች (Reagents) እጥረት በተለይም በተያዘው አመት መጋቢት ወር በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱን ‹‹ሃኪሞች ለሰብአዊ መብቶች›› (physicians for human rights) የተሰኘው የህክምና ባለሞያዎች ስብስብ ሪፖርት ያመላክታል፡፡
ዋዜማ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ተገኝታ ባደረገችው ምልከታ፤ በተለይም የጨረር ህክምናን ለማግኘት ረጃጅም ሰልፎችን የያዙ፤ መቆም ተስኗቸው በየወለሉ የተኙ፤ በሰው ድጋፍ ወረፋ የሚጠብቁ በርካታ ታካሚዎችን ተመልክታለች፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም ከዚህ ቀደም ሁለት የነበረው የጨረር ህክምና መስጫ መሳሪያ በብልሽት ምክንያት 1 በመቅረቱ ነው፡፡ የቀረው አንድ መሳሪያም ካለው የታካሚ ብዛት አንጻር በተደጋጋሚ የሚበላሽ በመሆኑ አገልግሎት የማይሰጥባቸው በርካታ ቀናት እንዳሉም ከታካሚዎቹ ለመረዳት ችላለች፡፡
ከኮምቦልቻ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የጨረር ሕክምና ቀጠሮ የሚጠብቁት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው አንድ ታካሚ፤ “ከ 8 ወራት በላይ ቀጠሮዬን ጠብቄ ዛሬ ላይ ብደርስም፤ምርመራው የለም ተባልኩ፤ ወደ ግል ላብራቶሪ ሂዱ ይሉናል፤ እኛ ደግሞ ለትራንስፖርት ከዘመድ አዝማድ፤ እሱ ሲታጣም ቤተክርስቲያን ውስጥ ገንዘብ ተዋጥቶልን ነው የምንመጣው፤ እዚህ 1500 ብር የምንከፍልበት ምርመራ፤ የግል ሆስፒታል ላይ ከ15 እስከ 20 ሺህ ነው የምንጠየቅበት›› በማለት የችግሩን መጠን አብራርተዋል፡፡
የቤተሰብ ምጣኔ ህክምናዎች በተለይም የእርግዝና መከላከያ እና ጽንስ ማቋረጥ ህክምናዎችም የተጽእኖው ሰለባ ከሆኑት መካከል የሚገኙ ሲሆን በክንድ ስር የሚቀበሩ፣ በመርፌ፣ በእንክብል እና በሌሎችም መልክ የሚሰጡ የእርግዝና መቆጣጠሪያዎች ከ90 እስከ 100% የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸውን ዋዜማ በጤና ጣቢያዎች ከሚሰሩ ባለሞያዎች ሰምታለች፡፡
‹‹ ለ3 ወር በመርፌ መልክ የሚሰጠው የእርግዝና መቆጣጠሪያ ከአንድ አመት በፊት 25 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን አሁን ከ120 እስከ 150 ብር እየተሸጠ ነው፤ ከቲቢ መድሃኒት በስተቀር የኤች አይ ቪ፣ የቤተሰብ ምጣኔ እና ተያያዥ አገልግሎቶች እርዳታው ስለተቋረጠ እንጂ በነጻ ነበር የሚሰጡት፤ የሄፕታይተስ ‹ቢ› ክትባት ክፍያ ከሌሎቹ በበለጠ መልኩ ከ100 ፐርሰንት በላይ ጭማሪ አለው፤ ለጽንስ ማቋረጥ ህክምና የሚውሉ በጤና ጣቢያዎች ውስጥ የሌሉ ነገር ግን በግል ሆስፒታሎች ውስጥ ያሉ መድሃኒቶችም ከዚህ ቀደም ከ400 እስከ 500 ብር ይሸጡ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ከ1500 እስከ 1700 ብር እየተሸጡ ነው›› በማለት ባለሞያዎች አብራርተዋል፡፡
የትምህርቱ ዘርፍ
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ እርዳታ ትንታኔ ማዕከል (ACAPS) መጋቢት 13 ቀን 2025 ባወጣው ሪፖርት፣ ለኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ ተመድቦ የነበረው 18 ሚሊዮን ዶላር መቋረጡን የጠቆመ ሲሆን፤ በዚህ ምክንያት በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች በሚገኙ 1,500 ትምህርት ቤቶች ይደረግ የነበረው የምግብ ፕሮግራም እንዲሁም ተጓዳኝ የተጨማሪ ክህሎት ትምህርት መቋረጡን ገልጻል፡፡
ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው ወደ ተለያዩ ስራዎች፤ ሁኔታዎች ባስ ሲሉም ወደ ስደት አምርተዋል። በተለይም ታዳጊ ሴቶች ያገኙት የነበረው የንፅህና መጠበቂያ በመቋረጡ፣ ከትምህርት ውጤታቸው በተጨማሪ በማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳርፏል።
የጦርነት ወቅት ጥቃት ሰለባዎችና የማገገሚያዎች መዘጋት
በተባበሩት መንግስታት የሴቶች ድርጅት (UN Women) እና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከ 2 ወራት በፊት በጋራ ያወጡት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በጦርነት ወቅት ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች መጠለያና ህክምና ይሰጡ የነበሩ 22 የማገገሚያ ማእከላት (Safe Houses) በእርዳታ መቋረጥ ሳቢያ ተዘግተዋል። በዚህም ምክንያት ከመቐለ እስከ ደሴ ያሉ ከ15,000 በላይ እናቶችና ልጃገረዶች መሰረታዊ ጥበቃና ድጋፍ አጥተዋል። ሪፖርቱ እንዳረጋገጠው፣ መጠለያዎቹ በመዘጋታቸው የጥቃት ሰለባዎቹ ወደ ነበሩበት የችግር ቀጠና እንዲመለሱና ለተደራራቢ ጥቃት እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል። በተለይም በጦርነት ወቅት ከሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ ያለው የግንዛቤ መጠን እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ ከስነ-ልቦና እና አካላዊ ቀውስ ባሻገር መጠነ-ሰፊ ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ እንደሚገኝ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በመቀለ ከተማ የሚገኘውና በአሜሪካ አለማቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስ አይ ዲ) ድጋፍ ይንቀሳቀስ የነበረው የጥቃት ሰለባዎች መጠለያ (Safe House) በድጋፍ መቋረጥ ምክንያት እ.ኤ.አ በጥር ወር 2026 በሩን ሲዘጋ፣ እንደ ሜላት (ስሟ የተቀየረ) ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ተስፋቸው ጨልሟል። የ24 ዓመቷ ሜላት ከሁለት አመታት በላይ በተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት ወቅት በደረሰባት ጾታዊ ጥቃት ለከፍተኛ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት መዳረጓን ተከትሎ፤ ለማገገም ስትል በማገገሚያ ማእከል ውስጥ ለወራት የሕክምና እና የስነ-ልቦና እርዳታ ስታገኝ ቆይታለች፡፡
‹‹መጠለያው ለእኔ ሁለተኛ ቤቴ ነበር፤ እዚያ ሳለሁ ነው መኖር እንደምችል ያመንኩት። አሁን ግን በሩ ሲዘጋብን፣ የት እንደምንሄድ አናውቅም›› ስትል በጭንቀት ተውጣ ትገልጻለች።
ከመቐለ ከተማ በመቶዎች ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው ደሴ ከተማም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የ30 ዓመቷ ሰብለ (ስሟ የተቀየረ) በጦርነቱ ወቅት የደረሰባትን ጾታዊ ጥቃት ተከትሎ በማገገሚያው ውስጥ ተጠልላ የነፃ የሕግ ምክርና የስነ-ልቦና ድጋፍ ታገኝ ነበር። መጠለያው በእርዳታ መቋረጥ ምክንያት እ.ኤ.አ መጋቢት ወር 2025 ሲዘጋ ግን ሰብለ ወደ ጎዳና ለመውጣት ተገዳለች።
ግብርና እና የአደጋ ስጋት ምላሽ
በመጋቢት 2026 በግብርና ሚኒስቴር እና በአለም የምግብ ፕሮግራም በጋራ የወጣ ግምገማ እንደሚያሳየው፣ በዩኤስ አይ ዲ (USAID) ድጋፍ ይቀርቡ የነበሩ ድርቅን የሚቋቋሙ ምርጥ ዘሮች አቅርቦት በ 50% ቀንሷል። አሜሪካ በዚሁ ተቋም በኩል ታደርገው የነበረው የአደጋ ስጋት አመራር ድጋፍ በመቆሙም፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱ ተስተጓጉሏል። ኦሮሚያ አማራና ሶማሊ ክልሎች ከዚህ ፕሮግራም እጅጉን አትራፊ ነበሩ። የእርዳታው በድንገት መቋረጥ የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ ራሷን የመቻል ጉዞ ክፉኛ እየጎዳው እንደሆነ የሚገልጹት ብዙዎች ቢሆኑም፤ የኢትዮጲያ መንግስት ግን ለችግሩ ‹‹መፍትሄ አለኝ›› ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሀገሪቱ ከተረጂነትና ከዕርዳታ ነፃ ወጥታ ራሷን መቻሏን ለማወጅ እቅድ ነድፎ ሲንቀሳቀስ ቢቆይም ውጥኑ ከምን እንደደረሰ አልገለፀም። በሀገር ውስጥ ከህዝብ በሚሰበሰብ ገንዘብ ለስብዓዊ ድጋፍ ቋት የማበጀት ስራ የተጀመረ ቢሆንም በተፈለገው ደረጃ የሰመረ አልሆነም።
የፓርላማው ስጋትና የመንግስት ምላሽ
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ፤ ባለፈው አመት ግንቦት ወር ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት፣ እርዳታው በመቋረጡ ምክንያት የ300 ሚሊዮን ዶላር የበጀት ጉድለት ማጋጠሙንና የክትባት ሽፋን ከ90% ወደ 75% ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል። በወቅቱም በጅቡቲ ወደብ የታገደው 35,000 ሜትሪክ ቶን የምግብ እርዳታ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የትራንስፖርት በጀት መታጣቱ ሌላው አሳሳቢ አጀንዳ ነበር። መንግስት ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሀገር ውስጥ ሀብት አሰባሰብንና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድንን ለማጠናከር ቢጥርም፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የዋጋ ግሽበት ስራውን ፈታኝ አድርገውት ቆይተዋል፡፡ አሁን ላይ በተለይም የሀገር ውስጥ ሃብት አሰባሰብ ሂደቱ በህግ ድንጋጌ ተደግፎ ወደ ትግበራ መግባቱ በአንዳንዶች ዘንድ እንደ መልካም ጅምር ሲታይ፤ ሌሎች ደግሞ ህዝቡ ባለበት ዘርፈ-ብዙ ቀውስ ላይ ‹‹ተጨማሪ ራስ ምታት›› ይሉታል፡፡
አዲሱ የአሜሪካ የድጋፍ መዋቅር
ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ሰብአዊና አስተዳደራዊ ቀውስ ፤አዲስ መልክ እየያዘ ይገኛል። ጥር 2026 የወጣው የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ ለበርካታ አስርት ዓመታት የውጭ እርዳታን ሲመራ የቆየው የዩኤስ አይ ዲ መዋቅር ፈርሶ፣ ተግባራቱ በቀጥታ በስቴት ዲፓርትመንት ስር እንዲሆን ተደርጓል። ይህ መዋቅራዊ ለውጥ እርዳታው ከአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት እና የውጭ ፖሊሲ ግቦች ጋር ይበልጥ እንዲቆራኝ የሚያደርግ ነው፡፡
ታህሳስ 15 ቀን 2025 በተፈረመው አዲስ ስምምነት መሠረት፣ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚውል ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ የተመደበ ሲሆን፣ ትኩረቱም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ግልጽነት እና የመሰረተ ልማት ጥገና ላይ መሆኑ ተገልጿል።
እያንዳንዱ ድጋፍ ለተረጂው መድረሱን ለማረጋገጥ ‹‹Biometric›› እና ‹‹Blockchain›› የተሰኙ ዳሰሳን ማእከል ያደረጉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም መጀመሩን የስቴት ዲፓርትመንት መረጃ ያሳያል። ምንም እንኳን ይህ አዲስ አሰራር እርዳታን ‹‹በብቃትና ለሚፈለገው አላማ ማዋል›› የሚል ትልም ቢኖረውም፣ ባለፈው አንድ ዓመት በሀገሪቱ የጤና፣ የትምህርትና የአደጋ ስጋት ዘርፎች ላይ የደረሰውን ጥልቅ ስብራት ምን ያህል ይክሳል የሚለው ግን አሁንም ትልቁ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል።
ይህ አዲሱ የኣሜሪካ የድጋፍ ስምምነት በሰነድ ደረጃ ቢፈረምም በተግባር ድጋፉ ለተረጂዎች ስለመድረሱ እስካሁን ማረጋገጫ አላገኘንም። ይልቁንም የድጋፍ ስምምነቱ አወዛጋቢ ይዘት ያለውና በአንዳንድ ሀገሮች ተቀባይነትን ያላገኘ ሆኗል። [ዋዜማ]
