በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ በተለያዩ ሀገራት በመዞር ላይ ይገኛል። ልዑኩ በአሜሪካ የተባበሩት መንግስታት መቀመጫ በሆነችው ኒውዮርክ እና በዋይት ሀውስ መናኸሪያ ዋሽንግተን ዲሲ ቆይታ እንደሚያደርግ የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ዋና ፅህፈት ቤት እና የአውሮፓ ፓርላማ በሚገኝባት የቤልጄየሟ ብራስልስም ቀጠሮ ተይዞለታል። እዚያው አውሮፓ ወደ ለንደን እና በርሊንም ጎራ ይላል ተብሎ ይጠበቃል። እስከ መጋቢት 19 እንደሚቆይ በሚጠበቀው የዚህ ጉብኝት ዋና አላማ የኢትዮጵያ መንግስትን እየተፈታተነው የሚገኘው የድርቅ ሁኔታ ነው። ልዕኩ በሚጓዘባቸው ሀገራት ላሉ የየመንግስታቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የተቋማት መሪዎች ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን እርዳታ በአፋጣኝ እንዲለግሱ የማግባባት ኃላፊነት ተጥሎበታል።