A girl fetching a water-Photo credit US Embassy in Addis Ababa
A girl fetching a water-Photo credit US Embassy in Addis Ababa

አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጲያውያን በከፋ የውሃ እጦት እየተሰቃዩ ነው፣ ኦሮሚያ ክልል በተነሳው ተቃውሞ ምክንያት ከግማሽ በላይ የሆኑትን መድረስ እንዳልተቻለ የዋዜማ ምንጮች ይናገራሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ቀስ በቀስ ስር እየሰደደ የመጣውን ግጭት ለመቆጣጠር መንግስት የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይል አልበቃ ብሎት የፌደራል ፖሊስን ቢጨምርም ግጭቱ እየበረደ ነው ሲባል መልሶ እየጋመ በክልሉ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ከተሰማራ ወራት ተቆጥረዋል፡፡

ለወራት ለመስክ ግዳጅ የተሰማራው የሃገር መከላከያ ሠራዊት የመንግስትን የበጀት እና የሎጀሰቲክ አቅም እየተፈታተን እንደሆነ እየተነገረ ቢሆንም አሁን ችግሩ በስድስት ክልሎች ለሚኖሩ በድርቅ ለተጎዱ አንገብጋቢ የውሃ ችግር ላጋጠማቸው 900 ሺህ ሰዎች ተርፏል፡፡

ችግሩ በሚታይባቸው ክልሎች የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን ለማደል እና ለማዳረስ 432 ውሃ ጫኝ መኪናዎች የሚያስፈልጉ እንደሆ የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) መጋቢት 12 ባወጣው ሳምንታዊ ሪፖርቱ አስታወቋል።

ሆኖም ችግሩን ለመታደግ መንግስት በራሱ ማቅረብ የቻለው 210 የውሃ ጫኝ መኪናዎችን በቻ ነው፡፡ ቀሪዎቹን ለማሟላት መንግስት ብቸኛ አማራጩ በአገር መከላከያ ውስጥ ያሉ ውሃ ጫኝ መኪናዎችን መጠቀም ነው።

“አቅሙ ያለው መከላከያ ጋር ነው፡፡የመከላከያ መኪኖች ደግሞ በኦሮሚያ ያለውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር በየቦታው ላሉ ወታደሮች ውሃ ለማቅረብ ስለተሰማሩ ሊገኙ አልቻሉም፡፡ ይህንን ያህል መኪኖች ከግለሰቦች ማግኘት አሰቸጋሪ ነው፡፡ ይህንንም የማቅረብ አቅሙ የላቸውም “እንደዋዜማ ምንጮች።

የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው 27 ውሃ ጫኝ መኪናዎችን ቢያቀርቡም አሁንም ቢሆን በኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ደቡብ፣ አፋር፣ ሶማሊ እና ሐረሪ ክልሎች 550 ሺህ ሰዎችን መድረስ እንዳልተቻለ ሪፖርቱ ይገልጻል።

በድርቁ ምክንያት የተባባሰውን ይህን የውሃ እጥረት ለመከላከል ከእርዳታ ድርጅቶች አቅም በላይ መሆኑን ያስረዳው ሪፖርቱ በተለይ በአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ውሃ በመኪና ለማጓጓዝ ያለው ርቀት እና አመቺ የመኪና መንገድ አለመኖር እንቅፋት ሆነዋል። በአማራ ክልል እንደ አበርገሌ፣ ሻላ አና ዝቋላ ወረዳ ውስጥ ላሉ ነዋሪዎች ውሃ ማድረስ ስላልተቻለ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወሩ ተገደዋል።

የውሃ ጉዳይ የተማሪዎችም ራስ ምታት ሆኗል። የውሃ እጦት ለተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መቅረት ገፋ ሲልም ማቋረጥ አንዱ ምክንያት ነው። በአገሪቱ ያሉ ትምህርት ቤቶች 75 በመቶ ምንም አይነት ውሃ የሌላቸው መሆናቸውን የሚገልጸው የማስተባበሪያ ቢሮው ሪፖርት በድርቁ ምክንያት ይህ አሃዝ የ10 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ያስረዳል። የወቅቱን የሰብዓዊ ቀውስ ትክክለኛ ሁኔታ ለማንፀባረቅ እንደሚከለስ በሚጠበቀው የእርዳታ ሰነድ ውስጥ በውሃ እጦት ምክንያት ከትምህርታቸው እንዲሰናከሉ የተገደዱ ተማሪዎች ቁጥርም አብሮ እንደሚታይ ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል።