Photo credit Save the Children

ዋዜማ-የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በኦሮምያ ፣ ደቡብና ሶማሌ ክልሎች በድርቅና ጎርፍ ለተፈጠረው አደጋ የሰጠው ምላሽ ዳተኛነት የታየበትና ከሚጠበቀው በታች በመሆኑ ችግሩን የባሰ እንዳወሳሰበው አስታውቋል፡፡

በድርቅና ጎርፍ አደጋ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች እየተደረገ ያለውን የሰብአዊና ቁሳዊ ድጋፍ ፣መሰረታዊ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የመልሶ የማቋቋም ስራ በተመለከተ  የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ያጠናቀረውን ሪፖርት ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ለጋዜጠኞች ይፋ አደርጓል፡፡ 

ተቋሙ ሶስት ቡድኖችን በማደራጀት በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን፣ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን እና በሶማሌ ክልል በዳዋ ዞኖች በተመረጡ 10 ወረዳዎች እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያዎች ከመጋቢት 11 እስከ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የቁጥጥር ስራ ማከናወኑን አስረድቷል፡፡

ባደረገው የመስክ ጉብኝትም የደረሰባቸውን ግኝቶች በተመለከተ የህዘብ አንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር በደሎች መከላከል ዳይሬክተር አቶ አደነ በላይ ማብራሪያ

በዳሰሳ ጥናቱ የተፈተሹና መረጃ የተሰባሰበባቸው አካላት መካከል የክልሎች ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤቶች፣ የክልሎች የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፤ የዞኖችና ወረዳዎች ኃላፊዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ ለአደጋ መከላከል የተቋቋሙ ግብረ ኃይሎችና በድርቅና ጎርፍ ምክንያት ተፈናቅለው የሚገኙ  ዜጎች ናቸው፡፡

በኦሮሚያ ክልል – ቦረና ዞን በአራት ወረዳዎች በተከሰተ ድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው የሚገኙ 59፣561 ዜጎች በ20 መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከ 1 ሚሊየን 300 መቶ ሺ በላይ እንሰሳት መሞታቸውን በሪፖርታቸው ገልፀዋል። 

በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በሁለት ወረዳዎች በተከሰተ ድርቅና ጎርፍ ምክንያት ተፈናቅለዉ በመጠለያ ጣቢያ ዉስጥ የሚገኙ ዜጎች 63፣970 ናቸው፡፡ በዚሁ ዞን በድርቅና በጎርፍ የሞቱ እንስሳት 76,200 ያህል መሆናቸው በጥናቱ ተለይቷል፡፡

በሱማሌ ክልል /ዳዋ ዞን ሶማሌ ክልላዊ መንግስት ዳዋ ዞን በአራት ወረዳዎች ተፈናቅለው በአራት መጠሊያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ብዛት 16፤344፣ በድርቅ ምክንያት ሃብት የወደመባቸው ዜጎች 19፣044 ናቸው፡፡ በዚሁ ክልል በድርቅ የሞቱ የቀንድ ከብቶች፣ ግመሎች እና ፍየሎች ብዛት 334 716 ፣ በአደጋ ላይ ያሉና አስቸኳይ መኖ የሚያስፈልጋቸው እንስሳት 420,160 ሲሆኑ በጎርፍ  ምክንት የሞቱ ደግሞ 8,330 ናቸው፡፡

የዋና እንባ ጠባቂ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው በቦረና ዞን የተፈጥሮ ድርቅ በተከታታይ ዓመታት የተከሰተ ቢሆንም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የሚቀርበዉን ሪፖርት በመቀበል ዜጎችና እንስሳት የጉዳቱ ሰለባ እንዳይሆኑ የቅድመ መከላከልና አስፈላጊ ቅድመ ጥንቃቄ ባለመደረጉ በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

በዚሁ ዞን የተፈጠረውን ድርቅና ጎርፍ አደጋ አስመልክቶ ጠንካራና ግልጽ የመረጃ ልዉዉጥ አለመኖር፣ ድርቁን ተከትሎ የሚመጣዉን በሽታ ለመከላከል የተደረገው ዝግጅት አናሳ መሆን፤ ለአደጋ ጊዜ የሚከማቸዉ እህል በፌደራል መንግስት እጅ የሚመራ በመሆኑ በክልል ደረጃ የሚከማች እህል ባለመኖሩ የሚደረጉ እርዳታዎችን በጊዜና በወቅቱ ማቅረብ እንዳልተቻለ ተጠቅሷል፡፡

በደቡብ አሞ ዞን የተደረገው ጥናት ክልሉ በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች እርዳታ እንዲደረግላቸው ለፌደራል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር በተደጋጋሚ ጊዜ ጥያቄ ቢቀርብም ምንም አይነት ምላሽና እገዛ አለመደረጉን ያሳያል፡፡

በዚሁ የደቡብ ኦሞ ዞን በአንዳንድ ወረዳዎች ለእርዳታው ሲባል ካላቸው የሰው ሃይል በላይ ሰው ማስመዝገብና አመራሮችም ጭምር በእርዳታው ውስጥ ለመካተት ጥረት ሲያደርጉ መታየቱንም ተመላክቷል፡፡

የሶማሌ ክልል ላይ የተካሄደው ጥንቅር እንደሚያሳየው ደግሞ በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎች ለሚደረግላቸው ሰብዓዊ ድጋፍና እርዳታ እንዲሁም የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሐዊ አለመሆን እንዲሁም ከድርቁ  ባለፈ በአሁኑ ሰዓት በተከሰተ ጎርፍ ለተደራራቢ አደጋ ለተጋለጡ ተፈናቃዮችና ሌሎች ማህበረሰብ ክፍሎች ፈጣን ምላሽና አስቸኳይ ድጋፍ አለመሰጠቱ ተገልጿል፡፡

በመንገድ መሰረተ ልማት እና ጎርፍ ችግሮች ምክንያት የሚደረገው ውስን ድጋፍ በአሁኑ ወቅት መቋረጡና ከሚመለከታቸው አካላት ትኩረት አለመኖር፣ ለሴቶች፣ ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞችና ለአረጋዊያን ለሚደረገው ልዩ ድጋፍና ጥበቃ የተዘረጉ አሠራሮች አለመኖራቸውን ሪፖርቱ ያትታል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ያጠናቀረውን ሪፖርት አሰመልከቶ ባቀረበው ምክረ ሃሳብ ፓርላማው የተፈጠሩ ክፍተቶችን ባለው የአሰራር ስርዓት መሰረት እርምት እንዲወሰድ ያሳሰበ ሲሆን ልዩ ትኩረት የሚያሻቸው ወገኖች በመንግስት በኩል የሚደረግላቸው ድጋፍ ጊዜውን ያልጠበቀና ተደራሽ ካለመሆኑም ባሻገር ለፌደራል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ለሚያቀርቡት ተደጋገሚ ጥያቄ ፈጣን ምላሽና እገዛ አለመደረጉ አጽንኦት ተሰጥቶት እንዲሰራበት ጠይቋል፡፡

የክልል መንግስታት በተፈጥሮ ድርቅና ጎርፍ ምክንያት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን በጀት አስጠንተው ለፈደራል መንግስትና ለሌሎች አጋር አካላት በማቅረብ የድጋፍ ቋት እንዲያዘጋጁ መክሯል። [ዋዜማ]