Lemma Megerssa, Oromia regional president
Lemma Megerssa, Oromia regional president

ዋዜማ ራዲዮ- ከያዝነው አመት መጀመሪያ አንስቶ ፌደራል መንግስቱ እና ሌላኛው ለህዝባዊ አመጽ የተጋለጠው አማራ ክልል በዋናነት ለሥራ አጥ ወጣቶች ሥራ በሚፈጥሩ መርሃ ግብሮች ላይ ብቻ ተጠምደው ይታያሉ፡፡ ባንጻሩ ኦሮሚያ ክልል በይዘቱ ለአመጹ የሚሰጠውን ምላሽ ባንድ ርምጃ ወደፊት በማሳደግ አዲስ የሚመስል ሃሳብ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ በተለይ ካለፈው ወር ወዲህ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ለማ መገርሳ በክልሉ የኢኮኖሚያዊ አብዮት የመፍጠርን አስፈላጊነት በመስበክ የህዝቡን በተለይም የወጣቶችን ቀልብ ለመሳብ በመጣር ላይ ይገኛሉ፡፡

እቅዱ እውን ከሆነ በኦሮሚያ ክልል ከሌሎች ክልሎች በተለይም ከአማራ እና ደቡብብ ክልል ጋር ያለውን ሚዛን ይነካል፡፡ አራቱ ትላልቅ ክልሎች በኢህአዴግ በቀጥታ የሚተዳደሩ በመሆናቸው እና ተመሳሳይ የኢንቨስትመንት እና ሃብት ክፍፍል አሰራር ስለሚከተሉ እድገታቸው ተቀራራቢ ነው፡፡ በኦህዴድ፣ ብአዴን እና ደኢህዴን መካከልም የሃብት ክምችት እሽቅድድም እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የተቀጣጠለው ህዝባዊ አመጽ ክልሎችን በሚመሩት የፖለቲክ ድርጅቶችም ሆነ በገዥው ግንባር ውስጥ ይህ ነው የሚባል የሃይል አሰላለፍ ሽግሽግ አላመጣም፡፡ ሆኖም ህዝባዊ አመጹ በኦህዴድ ላይ አሻራውን ሳይጥል አላለፈም፡፡ በተለይ ለአመጹ እውቅና በመስጠት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እና በጠባብ ብሄረተኝነት የሚከሳቸውን በውጭ ያሉ ሃይሎች በማውገዝ እና የህዝቡን ጥያቄዎች ባስቸኳይ እንደሚፈታ ቃል በመግባት ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ጥሯል፡፡ አመጹ በየትኛው ተቃዋሚ ድርጅት ያልተመራ መሆኑ ደሞ ጠቅሞታል፡፡

ኦህዴድ ቀጥሎም ተቃዋሚዎች የሚሰብኩትን አጀንዳ በመጥለፍ ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ የሚኖረውን ልዩ ጥቅም የሚደነግግ ረቂቅ ህግ ማዘጋጀቱን በመግለጽ የህዝብ ጠበቃ መሆኑን ለመስበክ ሞክሮ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መሪ እቅድን በተመለከተ ግን ከዥዋዥዌ አልዳነም፡፡ መሪ እቅዱ ለአጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች የሚሰጠውን ጠቀሜታ ሲሰብክ ቆይቶ በኋላ ግን እቅዱ እንደማይተገበር በመጥቀስ ፖለቲካዊ ትርፍ ሊያገኝበት ሞክሯል፡፡ በሁለቱም ሙከራዎች በኩል ግን እስካሁንም ይህ ነው የሚባል አወንታዊ እና ተጨባጭ ለውጥ አልታየም፡፡ በጸጥታ ረገድ ግን ኦህዴድ የክልሉን ልዩ ሃይል እንኳ ማንቀሳቀስ ባለመቻሉ በዋናነት የታየው የፌደራል መንገስቱ ተቃውሞን በወታደራዊ ኃይል የመቀልበስ ርምጃ ብቻ ነበር፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ የፈጠረው የድህረ-አመጽ ነባራዊ ሁኔታ ደሞ መጠነኛ መፈናፈኛ እድል ፈጥሮለታል፡፡ በጥቅሉ በድህረ አመጹ ኦህዴድ ሦስት ዋና ዋና ርምጃዎችን መውሰድ ችሏል፡፡ አንደኛው፣ በፖለቲካ እና መዋቅር በኩል እርምጃዎች መውሰዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለፓርቲው እና ለክልሉ አዳዲስ መሪዎች መሾሙ እና ለመልካም አስተዳደር መጓደል ተጠያቂ ያደረጋቸውን በሺህዎች የሚቆጠሩ ካድሬዎቹንም አሰናብቷል፡፡ ይህ ግን ኦህዴድ ውስጣዊ መዳከም ባጋጠመው ቁጥር የሚወስደው የተለመደ ስልት በመሆኑ ለህዝባዊ አመጹ የተሰጠ አስተማማኝ አወንታዊ ምላሽ አድርጎ መውሰድ ያስቸግራል፡፡

ሁለተኛው ርምጃ የፖሊሲ ለውጥ ነው፡፡ ለዚህ በዋናነት ተጠቃሽ የሚሆነው እና ህዝባዊ አመጹን ለቀሰቀሰው ብሶት ምላሽ ይሆንልኛል ብሎ በቅርቡ ያወጀው የኢኮኖሚ አብዮት ትርክት ነው፡፡ ትርክቱ የህዝባዊ አመጹ መነሻ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ብቻ እንደሆኑ አስመስሎ የተቀረጸ ሲሆን ና ብዙም ያልተብራራ ነው፡፡ ላሁኑ ግን የኢኮኖሚ አብዮት ንቅናቄው ሁለት መርሃ ግብሮችን ማቀጣጠያ አድርጓል፡፡ ባንድ በኩል የግል መኖሪያ ቤት ለሌላቸው የክልሉ ነዋሪዎች እና በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች የከተማ ቤት መስሪያ ቦታ ያለ ሊዝ ክፍያ እንዲያገኙ የሚያስችል አዲስ መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡ በሌላ በኩል ደሞ የክልሉ መንግስት ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር አርሶ አደሮችን፣ የመንግስት ሰራተኞችን እና ወጣቶችን ያቀፉ የአክሲዮን ንግድ ኩባንያዎችን ማቋቋሙን መግለጹ ነው፡፡ በተለይ 400 ሺህ ዜጎችን ያቅፋል የተባለለት ኦዳ የተቀናጀ ትራንስፖርት አክሲዮንማህበርን ማቋቋም ደሞ ዋነኛው ነው፡፡ ወደፊትም መኪና መገጣጠሚያዎች፣ ነዳጅ ማደያዎች እና የግብርና ውጤቶች መቀነባበሪያዎች እንደሚቋቋሙ ከወዲሁ ሲሰበክ ሰንብቷል፡፡

አሁን ኦህዴድ ጠባብ እና ትምክህት በሚላቸው ሃይሎች ላይ ጣቱን ላይ ከመቀሰር ይልቅ የውስጥ ኢኮኖሚያዊ ጡንቻውን ለማዳበር መፈለጉን ለማሳየት እየጣረ ነው፡፡ ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆኑ ከወዲሁ ለመተንበይ ቢያስቸግርም በተለይ ርዕሰ መስተዳድሩ የኦሮሞ ብሄርተኝነት እንዲጎለብት፣ ኦሮሞዎች አንድነት ፈጥረው እና ተደራጅተው የህዝቡን የውስጥ ኢኮኖሚያዊ ማነቆ እንዲፈቱ ጥሪ ባድረግ ተጠምደዋል፡፡ ብሄርተኝነትን የማጎልበት ትርክት ከርዕሰ መስተዳድር መሰማቱ እና ስለ ሃብት ክፍፍል ሲናገሩ ከሌሎች በስም ካልጠቀሷቸው ብሄሮች ጋር እያነጻጸሩ መሆኑ ደሞ አነጋጋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡ ያሁኑ ስብከት ግን አዲስ ነው ማለት አይቻልም፡፡ እንዲያውም በድህረ-1997ቱ ምርጫ ኦህዴድ የቀሰቀሰው የብሄርተኝነት መነቃቃት ትርክት ሁለተኛ ምዕራፍ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

በዋናነት ግን የኦህዴድ የኢኮኖሚ አብዮት ንቅናቄ ከገዥው ግንባር የሃይል አሰላለፍ ሚዛን ላይ ምን አንድምታ ይኖረዋል? የህዝባዊ አመጹ እና ኦህዴድ በድህረ-አመጹ የሚወስዳቸው ርምጃዎች በህወሃት-መራሹ ገዥው ግንባር ላይ አንጻራዊ ተጽዕኖ እንዲፈጥር ያስችሉት ይሆን? በሀገሪቱ የሚመራውን ህዝብ ቁጥር እና ግዙፉን ክልል የሚመጥን የሃብት ድርሻ ያስገኝለት ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች ከወዲሁ ማንሳት ግድ ይላል፡፡

በ2000 ዓ.ም የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ (አንቀፅ 52) ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በቀጥታምሆነ በተዘዋዋሪ በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሥራዎች መስማራት እንደማይችል ቢደነግግም ህወሃት ግን የግዙፍ ንግድ ኩባንያዎች ባለቤትነቱን እንዳስጠበቀ ቀጥሏል፡፡ በሃብቱ ግዙፍነትም ተወዳዳሪ የለውም፡፡ ብአዴን “ጥረት” በተሰኘው ኢንዶውመንቱ በሁለተኛ ደረጃ ሲከተል ኦህዴድ ግን እዚህ ግባ የሚባል ኢንዶውመንት የለውም፡፡ ቀደም ሲል “ዲንሾ” እና “ቱምሳ” የሚባሉ ኢንዶውመንቶች የነበሩት ቢሆንም ወሪያቸው ከጠፋ በርካታ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የሰሞኑን የኦህዴድ የኢኮኖሚ አብዮት ትርክት የከሸፈው የንግድ ተወናይ የመሆን ህልም ሁለተኛ ምዕራፍ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ከኢህአዴግ መዋቅራዊ አደረጃጀት እና የፓርቲው ፖሊሲ አንጻር ሲታይ ኦህዴድ የኢኮኖሚ ጡንቻውን ለማዳበር ስልት መንደፉ ትክክል ነው፡፡

ኦህዴድ-መራሹ ክልላዊ መንግስት ሊሰማራባቸው ያሰባቸው የንግድ መስኮች ግን አዲስ አይመስሉም፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ በቁጥር እያደጉ፣ በአቅም እየጎለበቱ የመጡት የህወሃት ኢንዶውመንቶች ቀደም ብለው ተሰማርተውባቸዋል፡፡ የህወሃት ኢንዶውመንቶች የንግድ ቀጠና ደሞ ሰፊ ሃብት እና ገበያ ባለቤት የሆነውን ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ መላ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ኢንዶውመንቶቹ ደሞ በኦህዴድ ወይም በክልሉ መንግስት ይዞታ ስር ያሉ የንግድ ኩባንያዎችን ይቅርና በሀገሪቱ ነጻ ገበያ ህግ የሚወዳደሩትን የግል ኩባንያዎች እንኳ ከገበያ በማስወጣት ይታወቃሉ፡፡ ከህወሃት ኢንዶውመንቶች ባሻገር ደሞ በጦር ግዙፉ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በበርካታ የንግድ መስኮች ተሰማርቷል፡፡

በዚህ ሁኔታ በክልሉ የኦህዴድ ኩባንያዎች ከህወሃት ኢንዶውመንቶች ጋር በቀልፍ ንግድ መስኮች መፎካከር ቀርቶ የተወሰነ የገበያ ድርሻ እንኳ እንዲያገኙ ይፈቀድላቸዋልን?  ታዲያ በዚህ ሁኔታ የኦሮሚያዎቹ ኩባንያዎች ክፍተት አግኝተው ቢያንስ የወጣቶችን መሰረታዊ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች የሚመልስ የኢኮኖሚ አብዮት ሊያቀጣጥሉ ይችላሉን? አስቸጋሪ ይመስላል፡፡

ኦህዴድ ክልሉን በሞግዚትነት ማስተዳደር አልፎ ክልላዊ መሰረት ያለው የኢኮኖሚ ጡንቻ እንዲያዳብር መፍቀድ አደጋ እንዳለው ማስላቱ አይቀርም፡፡ በፓርቲው ወይም ክልላዊ መንግስቱ ዙሪያ የሚፈጠር የሃብት ክምችት ውሎ አድሮ የገዥው ግንባር ውስጥ የሰፈነውን ያልተመጣጠነ የፖለቲካ ስልጣን ወደማስተካከል መቀየሩ አይቀርም፡፡ ለምን ቢባል በገዥው ግንባር አራት አባል ድርጅቶች መካከል ያለው የሃብት መራራቅ ያልተመጣጠነ የፖለቲካ ሥልጣን ክፍፍሉ ቀጥተኛ ነጸብራቅ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እስካሁንም በህወሃት እና ኦህዴድ መካከል የአግድሞሽ ቅራኔ ሊፈጠር ያልቻለበት አንዱ ምክንያት በዚሁ ግዙፍ ክፍተት ሳቢያ እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡ ቀደም ሲል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ከስልጣን የተነሱት የተማሩ ጎልማሶችን በማስተባበር ጡንጫው የፈረጠመ መካከለኛ መደብ ለመፍጠር በመንቀሳቀሳቸው እንደሆነ በሰፊው ይታመን እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ያ ማለት ግን ህወሃት ከሰሞኑ የኦህዴድ የኢኮኖሚ አብዮት ትርክት ጀርባ እጁ አይኖርበትም ማለት አይሆንም፡፡ ከዚህ አንጻር ህወሃት ሁለት ታሳቢ እቅዶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ አንደኛው፣ የኦህዴድ ኩባንያዎች አክሲዮንኖች የክልሉ ነዋሪ ለሆኑ ዜጎች ሁሉ ክፍት እንዲሆን በማድረግ ኩባንያዎቹን በተዘዋዋሪ መቆጣጠር ነው፡፡ ሁለተኛው ደሞ ኦህዴድ መለስተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት ፈጥሮ ቅቡልነቱን እንዲያሻሻል በማገዝ የህዝባዊ አመጽ ስጋትን ለጊዜው ማረግብ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የኦህዴድ ትርክት በገዥው ግንባር ውስጥ ሊመነዘር የሚችል የፖለቲካ ስልጣን ጡንጫ ይሆነዋል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች መፈናፈኛ አግኝተው ቢነግዱ እንኳ ባጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ ሆነው በተለይ የወጣቱን ቀልብ እንዲስቡ መፈለጉ አይቀርም፡፡ ይህም ኩባንያዎቹ በተለይ የግል ባለሃብቶችን ሊደፈጥጡ ይችላሉ የሚለው ግምት እንዲያይል አድርጎታል፡፡ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ማስፈን ተስኖት እያለ በኢኮኖሚ አብዮት ሽፋን ከባለሃቶች የልማት ዘርፎችን ነጥቆ ለወጣቶች ለመስጠት ማቆብቆቡን በይፋ ማመኑም ሌላ መዘዝ እንደሚስከትል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ፡፡ በርግጥም የሀገር በቀል ባለሃብት እጥረት መኖሩን ቀን ተሌት የሚሰብከው መንግስት በዚህ ዓይነት ተግባር መሰማራቱ እንቆቅልሽ ነው፡፡

በኦህዴድ ትርክት ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች ግን ድርጅቱ ብዙ ያላስጠበቃቸው ወይም እንደ አጀንዳ ያላነሳቸው የኦሮሞ ህዝብ የመብት ጥቄዎች እያሉ ኢኮኖሚያዊ አብዮትን ማቀንቀኑ ለጊዜው አቅጣጫ ከማስቀየር ያለፈ ፋይዳ እንደሌላቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ አዝማሚያው አሁንም ወጣቱን እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በመንግስት እና ፓርቲ መዋቅር ስር ጠርንፎ ጥገኛ በማድረግ ጽኑ ፍላጎት እንዳለ ይጠቁማል፡፡ በጥቅሉ የኦህዴድ ስልት ህዝባዊ አመጽን ለማስታገስ እና በተለይ ወጣቶችን ለማባበል በገዥው ግንባር የተነደፈ ስልት ይመስላል፡፡

በሌላ በኩል መሬት ለኢሕአዴግ የፖለቲካ ሥልጣን ማስጠበቂያው ከመሆኑም በላይ ለፌደራሉ እና ክልል መንግስታት ዋነኛው የገቢ ምንጫቸው በመሆኑ መሬት በነጻ የማደሉ ፖሊሲ አስተማማኝ ስልት ሆኖ መቀጠሉ ያጠራጥራል፡፡ በተለይ ለ2008ቱ ህዝባዊ አመጽ መነሻ የሆነውን የአርሶ አደሮች ከቀያቸው መፈናቀል ሊያባብሰው እንደሚችል ጠንከር ያሉ ስጋቶች አሉ፡፡

በተለይ የህግ የበላይነትን፣ እኩልነትን እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍኑ መዋቅራዊ እና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ሳይወሰዱ እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካዊ እና ሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ሳይፈቱ የተቀረጸው የኦኮኖሚ አብዮት በጥድፊያ የተገባበት ነው የሚመስለው፡፡ ኦህዴድ ከገዥው ግንባር ጫና ባይደርስበት እንኳ በሙስና እና ብልሹ አስተዳደር ተዘፍቆ የኖረው ኦህዴድ ግዙፍ የኢኮኖሚ መርሃ ግብሮችን ነድፎ እውን ለማድረግ ያለውን ብቃት እና ቁርጠኝነት የሚጠራጠሩት በርካቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱም አዳዲሶቹ መርሃ ግብሮች የተዘረጉት ለሙስና ተጋላጭ ሆነው ላለመኮላሸታቸው ዋስትና የሚሰጥ አሰራር ሳይኖር ነው፡፡

በዚህም አለ በዚያ ኦህዴድ ከውስጥም ሆነ ከውጭ በሚጋረጡበት እንቅፋቶች ሳቢያ ለህዝባዊ ጥያቄው ምላሽ ለመስጠት እና የራሱንም ፖለቲካዊ ቁመና ለማሻሻል አወንታዊ አስተዋጽዖ ደርጉለት ይሆን የሚለው ጥያቄ በጥርጣሬ እንደታጀበ ቀጥሏል፡፡

[ቻላቸው ታደሰ]