[ዋዜማ ራዲዮ]- የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት የመጀመሪያ ምዕራፍ በድል መጠናቀቁን ካወጀ በኋላ በድሕረ ጦርነቱ በሚኖሩ የፀጥታ ስጋቶች ላይ ምክክር ማድረግ መጀመሩን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ማረጋገጥ ችላለች።

በፌደራልና በክልል ባሉ አደረጃጀቶች እየተካሄደ ያለው ስልጠና ከጦርነቱ በኋላ ያሉ የአጭርና ረጅም ጊዜ ስጋቶችንና ፈተናዎችን በማብራራት ጀምሮ በተለይ የቅርብ ስጋቶች ላይ የጋራ አስተሳሰብ መፍጠር ዋና ግቡ መሆኑን የስልጠናው መሪዎች ለተሳታፊዎች አስረድተዋል።

ምክክሩ እየተደረገ ያለው መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ ባዘጋጀው የስልጠና ሰነድ ላይ ተመስርቶ መሆኑንም ከተሳታፊዎች ስምተናል።


መንግስት ከሕወሓት አማፅያን ጋር ሲያደርግ የነበረውን ጦርነት የመጀመሪያ ምዕራፍ በድል ማጠናቀቁን ይፋ ካደረገ በኋላ በጦርነቱ ጀብዱ ለፈፀሙ ዕውቅና፣ የማዕረግ ዕድገትና ማበረታቻ ሰጥቷል።


ዋዜማ ከስልጠናው ታዳሚዎች ባገኘችው መረጃ መንግስት ከጦርነቱ በኋላ በኢትዮጵያ ሊያጋጥሙ ይችላሉ ብሎ በስጋትነት የተመለከታቸውን  ፈተናዎች በቅድም ተከተል በማስቀመጥ በመፍትሄው ላይ ሀሳብ የማሰባሰብ ጥረት እያደረገና ወጥነት ያለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ለመፍጠር እየሞከረ መሆኑንም ከተሳታፊዎቹ ገለፃ ተረድተናል።


ለስብሰባው ሚስጥራዊነት እና ለውይይት የቀረበው ሰነድ ለአደባባይ እንዳይበቃ በሚል ስጋትም ሰልጣኞች ወደ መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲገቡ ተንቀሳቃሽ ሰልካቸውን ትተው እንዲገቡ ሲገደዱ እንደነበር ምንጮ ቻችን አረጋግጠዋል።  


ከድህረ ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ በሚልም በሰነዱ ከሰፈሩ ሃሳቦች መካከል መንግስት በሕወሓት ላይ የተቀዳጀውን ድል ለመውረስ ወይም የኔ ነው ወደሚል የድል ሽሚያ መግባት እና ከዚህ ጋርም ተያይዞ የፖለቲካ ትኩሳቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይጠቁማል። 


በጦርነቱ ምክንያት በገፍ ወደ ሀገር በህገወጥ መንገድ የገባውም ሆነ ጦርነቱ በራሱ በሰፊው በግለሰቦች እጅ ውስጥ እንዲገባ  ያደረገው የጦር መሳሪያ ሌላው ለሀገር ደህነነት እና ሰላም ስጋት ሊሆን የሚችል ተግዳሮት መሆኑን ይኸው ሰነድ ይገልፃል።


የኢትዮጵያን የድህረ ጦርነት ፈተናዎች እና አድሎችን የሚዳሰሰው ሰነድ ጦርነቱ ምክንያት ሆኖ በየአካበቢው የተደራጀው የጎበዝ አለቃ እና ኢመደበኛ አደረጃጀት ሌላው ለሀገሪቱ ፈተና ሊሆን እንደሚችልም ስጋቱን ያስቀምጣል። [ዋዜማ ራዲዮ]