ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት በውጪ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዉያን የገና እና የጥምቀት በዓላትን በሀገር ቤት በመገኘት እንዲያከብሩ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በርካታ እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ይገኛሉ። ይህን ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ በባንኮች እና በጥቁር ገበያው መካከል የነበረው ሰፊ የምንዛሬ ልዩነት እየጠበበ መምጣቱን የዋዜማ ሪፖርተር በቅኝቱ አረጋግጧል


ከሁለት ሳምንት በፊት አንድ የአሜሪካን ዶላር በጥቁር ገበያው ይመነዘርበት የነበረው መጠን ከባንኮች ከነበረው በንፅፅር ሲታይ እስከ 17 ብር የደረሰ ልዩነት ነበረው። የዋዜማ ሪፖርተር በጥቁር ገበያ ያለውን ምጣኔ ለማጣራት ሐሙስ ዕለት ባደረገው ቅኝት አንድ የአሜሪካን ዶላር ከ61 እስከ 58 ብር እየተመነዘረ መሆኑን ታዝቧል። ይህ ማለት በባንክ ካለው የምንዛሬ ምጣኔ አንፃር ሲታይ ከ10 ብር ያነሰ ልዩነት ብቻ ይታይበታል።


አንድ ዩሮ በጥቁር ገበያው ይመነዘርበት ከነበረው የ 70 ብር አካባቢ አሽቆልቁሎ ከ62 እስከ 60 ብር ድረስ እየተመነዘረ ነው። ይህም ትናንት በነበረው የባንክ ምንዛሬ አንፃር ሲታይ እስከ 20 ብር ሰፍቶ የነበረው የምንዛሬ ልዩነት አሁን በግማሽ መቀነሱን ያሳያል ።


ለዚህም እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው አስቀድሞ መንግስት የጥቁር ገበያው ምንዛሬ ይከናወንባቸዋል በተባሉ እና በተለምዶ የሚታወቁ አካባቢዎች ላይ ሰፊ አሰሳ እና የማሸግ እርምጃ መውሰዱ ሲሆን በዲያስፖራው ዘንድም የውጭ ምንዛሬ በህጋዊ አግባብ ለመመንዘር የሚያስችል ሰፊ ዘመቻ መጀመሩ ገንቢ ውጤት እያመጣ መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል።
በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ ላይ ተሰማርቶ የነበረ አንድ ግለሰብ ለዋዜማ በሰጠው አስተያየት ዳያስፖራው ወደ ሀገር ቤት መግባት ከጀመረበት ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ የውጭ ምንዛሬን በጥቁር ገበያ ለመመንዘር የሚመጡ ደንበኞች በእጅጉ መቀነሱን ይናገራል።


በአንጻሩ ደግሞ የዋዜማ ሪፖርተር ቅኝት ባደረገባቸው የሸራተን አዲስ እና የሂልተን ሆቴል የሚገኙ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎች ስራ በዝቶባቸው ተመልክቷል። በተለይም በሆቴሎች የሚገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ህብረት ባንክ የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት በመስጠቱ ረገድ እንዲህ አይነት በርካታ ደንበኞችን ያስተናገዱበት አጋጣሚ እንደማያስታውሱ የቅርንጫፉ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]