ዋዜማ ራዲዮ – ከድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያና እሱን ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙት እውቅ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አቶ በቀለ ገርባና ልደቱ አያሌው ዛሬ ሰኞ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የዋዜማ ሪፖርተሮች ተከታትለዋል።

ከድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ሞት፣ ሁከትና ብጥብጥ በቁጥጥር ሥር ውለው በሚገኙት የኦሮሞ ፌደራሊሰት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራር አቶ በቀለ ገርባ ለ3ተኛ ጊዜ ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት።

በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ችሎት የአራዳ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ሰኞ ከሰአት የቀረቡት አቶ በቀለ የድምፃዊ ሃጫሉን አስከሬን ከቡራዩ እንዲመለስ በማድረግ ፣ የኦሮሚያ የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ይዘው ሲገቡ፣ በጥበቃ ላይ የነበረ አንድ የኦሮሚያ ፖሊስ አባልን ተኩሰው መግደላቸውንና ሦስት ሌሎች ፖሊሶች  እንዲቆስሉ ማድረጋቸውን አንዲሁም አቶ በቀለ በዕለቱ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ ሻሸመኔ፣ አምቦና የተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ስልክ በመደወል አመፅና ሁከቱ እንዲባባስ ባስተላለፉት ትዕዛዝ ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱንና ከ50 በላይ የሰው ሕይወት መጥፋቱን ተርጥረው ነው፡፡


የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ባለፉት የምርመራ ጊዜ የተሰሩ ስራችን ለፍርድ ቤቱ ያስረዳ ሲሆን የጦር መሣሪያዎችን የፎረንሲክ ምርመራ ውጤትና የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ምርመራ ውጤትን ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ከመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ መቀበል እንደሚቀረው፣ እንዲሁም ለተለያዩ ተቋማት በሁከት የወደመ የንብረትን መጠን ለማወቅ የተጻፈ ደብዳቤ ምላሽ ማግኘት እና የቀሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ግዜ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል፡፡


አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው “ወንጀለኛ የተባልኩት በፖለቲካዊ አመለካከቴ ነው፣ ወንጀል የሚሰራ ሰው ልጆቹን ይዞ አይሄድም ፣ እኔ ሃጫሉን በግል ስለማውቀው እና ስለማከብረው ለቅሶ ለመድረስ ነው የሄድኩት፣ ወንጀል ፈፅመሀል የተባልኩት አውቀው በምርጫ እንዳልሳተፍ ለማድረግ ነው ” ሲሉ ለችሎት ተናግረዋል፡፡ አክለውም የግል መኪናቸው እስካሁን በፖሊስ እንደተያና እንዳልተለቀቀላቸቅ ተናግረዋል፡፡


የተጠርጣሪው ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ ከመጀመሪያ ጀምሮ የምርመራ ጊዜ ለማራዘም ሲቀርብ የነበረው ምክንያት ተመሳሳይ ነገር ነው፣ ምክንያቱ 14 የምርመራ ቀናት ለመጠየቅ በቂ አይደለም ያሉ ሲሆን፣ የደንበኛችን ወንጀል የግል ተሳትፎ ተለይቶ አልቀረበም ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የጠየቀውን የምርመራ ግዜ ተቃውመዋል፡፡

የሁለቱንም ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት 8 የምርመራ ቀን የፈቀደ ሲሆን የምርመራ መዝገቡ ከቀጠሮ በፊት በፅኅፈት ቤት በኩል እንዲቀርብ አንዲሁም የግል መኪናቸው ለምን ያልተለቀቀበት ምክንያት በፅሁፍ እንዲቀርብ ትእዛዝ ሰጥቶ ለነሀሴ 28 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡


ልደቱ አያሌው
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መስራች እና የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት ፖለቲካኛው አቶ ልደቱ አያሌውቱ በቢሸፍቱ ከተማ ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ በማስተባበር እና በመደገፍ የተጠርጥረው በፌደራል ፖሊስ በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር ውለው ለኦሮሚያ ፖሊስ ተላልፈው ከተሰጡ በኋላ ዛሬ ረፋዱን በቢሸፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ልደቱ አያሌው የ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል፡፡


አቶ ልደቱ ለህክምና ወደ አሜሪካ አትላንታ ጉዞ እንደነበራቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተው የዋስትና መብት እንዲሰጣቸው ካልሆነም በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቋሚ አድራሻ እና ቤት ያላቸው መታወቂያቸውም በዚያው መሆኑን በማንሳት በጊዜያዊነት በቢሾፍቱ ቤት እንዳላቸው በመግለፅ በፌደራል ፍርድ ቤት ነው መቅረብ ያለብኝ በሚል መቃወሚያ አቅርበዋል። ተጠርጣሪው አክለውም እስር ቤቱ ውስጥ ለኮሮና ቫይረስ ምንም አይነት ጥንቃቄ እየተደረገ አይደለም ካለብኝ ህመም ጋር ለጠንነቴ ያሰጋኛል ሲሉ ለችሎት ተናግረዋል፡፡
ፖሊስ በበኩሉ በዋስ ቢወጡ መረጃ ያሸሹብኛል እንዲሁም የእስር አያያዛቸው በጥሩ ሁኔታ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል


ግራ ቀኙን የሰማው ፍርድ ቤት የዋስትና ጥያቄውንና የፍርድ ቤት ዝውውር ጥያቄን ውድቅ አድርጎ ወንጀሉ የተፈመው በቢሸፍቱ ከተማ ስለሆነ መዝገቡ እዚሁ ይታያል ሲል ትእዛዝ ሰጥቷል። ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ቀን በመፍቀድ ለነሀሴ 4 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ቀጥሯል። [ዋዜማ ራዲዮ]