ዋዜማ ራዲዮ- የሀገር ሚስጥርን ለሽብርተኞች በመስጠትና ተያያዥ ክሶች የተጠረጠሩ የአዲስ አበባ የሕወሐት ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ተወልደ ገ/ፃዲቅ ߹ የህግ ጥናትና ምርምር ማዕከል ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋለም ይሕደጉ እንዲሁም 2 የፅህፈት ቤቱ ሹፌሮች በድጋሚ ዛሬ (ሰኞ) አራዳ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቤት ቀረቡ።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኛና የአቃቂ ክፍለ ከተማ የደህንነት ሀላፊ አቶ አፅብሀ አለማየሁም እዛው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

የሀገር ሚስጥርን ለሽብርተኞች በመስጠት ߹ አገሪቷ ላይ ብጥብጥ እና ግርግር እንዲነሳ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ አመራሮቹ ላይ ፖሊስ ምርመራዬን አልጨረስኩ የሚቀሩኝ ምርመራዎች አሉ ይህን ለማድረግ ተጨማሪ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን የጠየቀ ሲሆን ባለፈው የምርመራ ግዜ የተጠርጣሪዎችን ቃል ተቀብያለሁ ߹ ሰነዶችን ለኢትዮጵያ መረብ ደህንነት (ኢንሳ) ልክያለሁ በቀጣይ ተጨማሪ ተባባሪዎቻቸውን ለመያዝ ߹ የምስክሮችን ቃል መቀበል ተጨማሪ መረጃዎችን መሰብሰብ
ይቀረኛል ብሏል፡፡

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ የጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ሊሰጠው አይገባም ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን ፖሊስ የሚቀሩትን ስራዎች ለመስራት ደንበኞቻችንን አስሮ ለማቆየት በቂ ምክንያት አይደለም ደንበኞቻችን ታስረው በሚገኙበት አዲስ አበባ ፖሊስ እስር ቤት 3 እስረኞች በኮሮና ተይዘዋል ስለዚህ የጤንነታቸው ጉዳይ ያሳስባል እንዲሁም ፖሊስ የምርመራ መዝገብ የተደራጀ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ እኛ ታጋዩች ነን አገራችን ስናገለግል ነው የቆየነው ምንም ሽብር በአገራችን ላይ አልሰራንም ሽብርተኛ የተባለውም ቡድን አልተጠቀሰም ሲሉ ለችሎት ተናግረዋል፡፡

ግራ ቀኙን ያዳመጠው ችሎት ለጤንነታቸው ዋስትና እንዲጠበቅ እንዲሁም የፖሊስ የምርመራ መዝገብ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርብ እንዲሁም ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰብ እንዲሁም ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ ትእዛዝ ሰቷል በአቶ ተወልደ ገ/ፃዲቅ ߹ አቶ ተስፋለም ይደጉ እና 2 ፅህፈት ቤቱ ሹፌሮች ላይ ተጨማሪ የ8 ቀን የምርመራ ጊዜ ለሀምሌ 21 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን አቶ አፅብሀ አለማየሁ ላይ 10 ተጨማሪ ምርመራ ግዜ በተለዋጭ ቀጠሮ ለሀምሌ 23 2012 ሰጥቷል፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]