House Speaker , Tagesse Chafo – FILE
  • ለኮሚሽነርነት በህዝብ ከተጠቆሙት መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑት በቀጣይ በሚደረገው አገራዊ ምክክር አወያይ እንደሚሆኑ ተገልጿል

ዋዜማ ራዲዮ- የህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት ዛሬ የካቲት 14 ቀን  2014 ዓ.ም ባካሄደው  2ኛ አሰቸኳይ ስብሰባ 11 አባላት ያሉትን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ሹመት በአምስት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

ዘጠኝ ወንዶችና ሶስት ሴቶች በተካተቱበት የኮሚሽነሮች ስብስብ ውስጥ

ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፣

ወይዘሮ ሂሩት ገብረስላሴ – ምክትል ሰብሳቢ

እንዲሁም  በአባልነት ዶክተር ተገኘወርቅ ጌቱ፣

አምባሳደር ዶክተር አይሮሪት መሃመድ፣

ወይዘሮ ብሌን ገብረመድህን፣

ዶክተር ዮናስ አዳዬ፣

አቶ ዘገየ አስፋው፣

አቶ መላኩ ወልደማሪያም፣

አምባሳደር መሃሙድ ድሪር፣

አቶ ሙሉጌታ አጎ እና 

ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ ይገኙበታል፡፡

በአፈ ጉባኤው የሚመራው የኮሚሽነሮች መልማይ ኮሚቴ በህዝብ የተጠቆሙትን  632 ግለሰቦች  በስምንት የተለያዩ መስፈርቶች በሶሰት ምድብ በመለየት የመጀመሪያው ምድብ ከዚህ በፊት ለህዝብ ይፋ ከተደረጉት 42 ግለሶብች ውስጥ የተሸሙትን 11  ኮሚሽነሮች ያካተተ ሲሆን፣ በሁለተኛ ምድብ 75 ግለሰቦችና በ ሶስተኛ ምድብ 515 ግለሰቦችን የያዘ ነበር፡፡

በዚህም መሰረት ምክርቤቱ በኮሚሽነርነት ከሰየማቸው 11 ግለሰቦች በተጨማሪ አንደኛ ምድብ ላይ የቀሩትንና በሁለተኛ ምድብ የተቀመጡትን ግለሰቦች በቀጣይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚደረጉ የምክክር ሂደቶች እንደአወያይ ያገለግላሉ በሚል ፓርላማው ባጸደቀው የኮሚሽነሮች ሹመት የውሰኔ ሃሳብ ላይ ተቀምጧል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አገራዊ የምክክር ኮሚሽ አዋጅን ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በማጽደቅ ምክክሩን በበላይነት ሊመሩ የሚችሉ ግለሰቦችን ጥቆማ የሚቀበል ጽህፈት ቤት በምክርቤቱ ስር በማቋቋም ለኮሚሽነርት ብቁ የሆኑ  ሰዎችን ከታህሳስ 26 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሲቀበል ቆይቶ ከተጠቆሙት 632 ግለሰቦች መካከል የተለዩትን 42 ግለሰቦች ጥር 27ቀን 2014 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በጥቆማው መሰረት ከህዝብ ከተሰበሰበው የ632 ሰዎች ዝርዝር መካከል የ42ቱ ስም ብቻ ለህዝብ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት ቅራኔ የተፈጠረ ሲሆን፣ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የካቲት 09 ቀን 2014ዓ.ም ያወጣውን የፓርቲዎች የጋራ መግለጫ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ምክር ቤቱ በመግለጫው  ስኬታማ አገራዊ ምክክር አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ነፃ የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችል አማራጭ በመሆኑና ተስፋ የተጣለበት የፖለቲካ ሂደት መሆኑን በመጥቀስ ከኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ፣ከእጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማና ምልመላ ሂደት በተያያዘ እንዲሁም በሂደቱ  ለፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎና ሚና ረገድ በአመራረጥ ሂደቱ አየናቸው ያሉትን ጉድለት በመጥቀስ  ሂደቱ ለጊዜው ቆሞ በድጋሚ ውይይት እንዲደረግበት ጥያቄ ያቀረበው ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር፡፡

በተጨማሪም ሰኞ በቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ላይ በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ በዕጩነት የቀረቡት ግለሰቦች ላይ ተቃውሞ እንደሌላቻው ነገር ግን በነበረው ሂደት ላይ የግልፅነት  ጥያቄ እንደነበረበት አስታውሰው በህዝብ የተጠቆሙትን ግለሰቦች ስም ለምን  ይፋ እንዳልተደረገ ጠይቀዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የኮሚሽነሮች አመራረጥ በጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መስፈርቱን በመመልከት ሁሉንም አገራዊ ጉዳይ በእኩል አይን ማስተናገድ የሚችሉ በሚልና ካላቸው ብቃትና አለማቀፍ ልምድ በመነሳት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]