ዋዜማ ራዲዮ- ባልደራስ ፓርቲ አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ከአባልነት እንዲነሱ ምርጫ ቦርድ ትብብር እንዲያደርግ ያቀረበውን ጥያቄ ቦርዱ ውድቅ ማድረጉን ዋዜማ ስምታለች።

ምርጫ ቦርድ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላትን ከምክር ቤት አባልነታቸው ለማስነሳት ለማናቸውም አካል ትብብር የሚያደርግበት ሥልጣን እንደሌለው ለባልደራስ እውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል።

ቦርዱ ይህን ደብዳቤ ለፓርቲው የጻፈው፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አዲስ አበባ ከተማን ወክለው በከተማዋ ምክር ቤት ገዥው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው አባል የሆኑ ዘላለም ሙላቱ የተባሉ ተመራጭን ከምክር ቤት አባልነታቸው እንዲነሱ ፓርቲው ለሚያደርገው ጥረት ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ የካቲት 7 ለቦርዱ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ መሆኑን ገልጧል።

ቦርዱ በደብዳቤው ባሠፈረው ማብራሪያ፣ አንድን የሕዝብ ተመራጭ ከምክር ቤት ለማስነሳት ቦርዱ ለማናቸውም አካል በተለይም በምርጫ ክልሉ የምርጫ ተወዳዳሪ ለነበረ የፖለቲካ ፓርቲ ድጋፍ የሚያደርግበት አንዳችም ሕጋዊ አሠራር እንደሌለ በመግለጽ የፓርቲውን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

በምርጫ በሚቋቋሙ ምክር ቤቶች ተወካይ የሆኑ የሕዝብ ተመራጮችን ከምክር ቤት አባልነታቸው ማንሳት ወይም መጥራት የሚችለው የወከላቸው ወይም የመረጣቸው ሕዝብ ብቻ እንደሆነ እና ሕገ መንግሥቱ እና ሌሎች የሀገሪቱ ምርጫ ሕጎችም ይህንኑ እንደሚያረጋግጡ ቦርዱ አውስቷል።

የቦርዱ ሥልጣን ባንድ ምርጫ ክልል አብዛኛው መራጭ ሕዝብ በተወካዩ ላይ አመኔታ ስለማጣቱ በፊርማው ሲያረጋግጥ ሌላ ተወካይ ለማስመረጥ ማሟያ ምርጫ ማድረግ ብቻ እንደሆነ ቦርዱ በደብዳቤው አብራርቷል።

ባልደራስ ፓርቲ የከተማዋ ምክር ቤት አባል ዘላለም ሙላቱ ከምክር ቤቱ አባልነታቸው እንዲነሱ እንቅስቃሴ የጀመረው፣ ተወካዩ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እና አዲስ አበባ ከተማን አስመልክተው በሕግ ሊያስጠይቃቸው የሚችል የዘለፋ ንግግር አድርገዋል በማለት ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]