Takele Uma

ዋዜማ ራዲዮ- ከአራት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የተበሰረው በኢትዮጵያ የነዳጅ መገኘት ዜና ዕውን ሆኖ ምርት ሊገኝ  ባለመቻሉ መንግስት የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን የማዕድን ሚንስትሩ ታከለ ኡማ  ለፓርላማ አባላት ባቀረቡት ሪፖርት አስታወቁ። 

የነዳጅ መገኘቱ ዜና እውነት መሆኑን ያረጋገጡት ታከለ ሀገሪቱ ያላትን የነዳጅ ክምችት በድጋሚ የማረጋገጥና አዋጭነቱን የመመዘን ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል። ለዚህም የውጪ ሀገር አጥኚዎች የአሰሳ ጥናት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የቻይናው ፖሊ ጂሲኤል ፔትሮሊየም ሆልዲንግ ኩባንያ አስር ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በሶማሌ ክልል ነዳጅ ፍለጋ የጀመረ ነው። 

ከአራት ዓመታት በፊት በቁፋሮ ላይ ከነበሩ  ጉድጓዶች መካከል ሦስቱ ተጠናቀው ድፍድፍ ነዳጅ የሙከራ ምርት መጀመሩ የተበሰረውም በዚሁ ኩባንያ እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ የአገሪቱ የዘመናት የነዳጅ ፍለጋ ስኬት ታየበት የተባለው ሙከራ እንደታለመው አለመጓዙን መንግስት አምኗል።

ይህን ዜና ተከትሎ በሁለት ዓመታት ይጠናቀቃል የተባለ 767 ኪ.ሜ ወደ ጂቡቲ የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ዝርጋታ ለመገንባት ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ አገሪቱ ወደ ውጭ ለመላክና ገቢ ለማግኘት ተስፋ የጣለችበት ጋዝና ነዳጅ እንደ ውጥኗ መጓዝ አለመቻሉን የማዕድን ሚንስትሩ ታከለ ኡማ አልሸሸጉም። 

ፖሊ ጂሲኤል የተባለው ኩባንያ አራት የፍለጋ ስምምነትና አንድ የልማትና ምርት ፈቃድ ያለው ሲሆን፤ ኩባንያው በዘጠኝ ዓመታት ስራውም የሚጠበቅበትን ስራ አላከናወነም። ይህም በመሆኑ አገሪቱ ላይ ጉዳት ማድረሱ ተጠቁሟል። በአገር ደረጃ የተያዘውና ዘርፈ  ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት የተፈጥሮ ጋዝ ልማት በተያዘለት ጊዜ እውን እንዳይሆን አድርጓል።

የፋይናንስ ውስንነነትና የቴክኒክ አቅም ችግር አለበት የተባለው ፖሊ ጂሲኤል ኩባንያ  እስከ ሰኔ መጨረሻ 2014 ዓ/ም. ማስተካከያ ካላደረገ ስምምነቱ እንደሚቋረጥ ተነግሮታል።  ሪፖርተር ጋዜጣ  መጋቢት 18 ይዞት በወጣው ፅሁፉ ኩባንያው ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ለማምረት ከሚያስፈልገው አጠቃላይ መዋዕለ-ነዋይ ውስጥ 30 በመቶውን ከሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በፊት በብሔራዊ ባንክ እንዲያስመዘግብ ማስጠንቀቂያ ደርሶታል። 

ጋዜጣው አገኘሁት ባለው ሰነድና መረጃ መሰረት ፕሮጀክቱ ከሚጠይቀው አራት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 30 በመቶውን (አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊየን ዶላር) ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት አለበት።

የማዕድን ሚንስትሩ ታከለ ኡማ የአገሪቱ የማዕድን ልማት ደላሎች ባሏቸውና ከመንግስት ሹማምንት ጋር ቁርኝነት በመሰረቱ ሠዎች መታጠሩ ለአፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን እንደ አንድ ምክንያት አንስተዋል።

በአጠቃላይም የማዕድን ዘርፉ ከሚገኝበት ስፍራ አንፃር ለፀጥታ ስጋትና ችግሮች ቀጥተኛ ተጋላጭ ነው ያለው የማዕድን ሚንስቴር ሪፖርት፤ በአብዛኛው የማዕድን ምርት ባለባቸው አካባቢዎችና ኩባንያዎች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ምርት እንዲያቆሙ ተገደዋል ብሏል። 

በመሆኑም የነዳጅ ፍለጋና ልማት ባለበት እንደ ሶማሌ ክልል ባሉ አካባቢዎች ስራ መስተጓጎሉን አስረድተዋል።

ለትራንስፖርት ዘርፉና ለኢንዱስትሪዎች የኃይል ምንጭ የሆነው ነዳጅ በተለይም በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ዋጋው ጣራ እየነካ ነው። በዚህ ወር እስከ አምስት ብር ድረስ የዋጋ ማስተካከያ ያደረገው መንግስት፤ በሐምሌ ወር ሙሉ ለሙሉ ድጎማውን ያነሳል ተብሎም ይጠበቃል። [ዋዜማ ራዲዮ]