FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ለ3 ወር ገደማ ተቋርጠው የነበሩ የዲጂታል የኃዋላ መተግበሪያዎች አገልግሎት መሰጠት ሊጀመሩ ነው። 

አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች አልተሟሉም በሚል በአቢሲኒያ ባንክ በኩል አገልግሎት የሚሰጡት “ካሽጎ” እና “ማማ ፔይስ” የተሰኙ መተግበሪያዎች በባንኩ ተእዛዝ መሰረት አገልግሎት አቋርጠው ነበር።  “ካሽጎ”  ሶልጌት በተባለ ድርጀት የተሰራ ሲሆን፣ “ማማ ፔይስ” ደግሞ በቤል ካሽ የተዘጋጅ ነው። 

የባንኩ የውጭ ምንዛሬ ክትትልና ሪዘርቭ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ባንኩ ወይም የቴክኖሎጂ አቅራቢዎቹ የኃዋላ ሰራ ፈቃድ እንዲያወጡ ፍላጎት እንደነበረው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል። 

ለውዝግቡ አንድም መነሻ የሆነው ሀገር ውስጥ የተሰሩ የዲጂታል የኃዋላ አገልግሎት መተግበሪያዎች ባለመኖራቸው ነው። 

በብሔራዊ ባንክ በወጡ ህጎች መሰረት ድርጅቶች ለባንኮች ቴክኖሎጂ ማቅረብ ስለሚችሉ ሌላ ተጨማሪ ፈቃድ እንደማያስፈልግ ባንኮች ደግሞ የኃዋል አገልግሎት መስጠት በባንክ ፈቃዳቸው ውስጥ የተካተተ እንደሆነ ክርክር ያቀርባሉ። 

ጉዳዩ ከብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች መፈታት ባለመቻሉ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ድረስ ደርሶ ውሳኔ እንዲሰጥበት እንደተደረገ ምንጮች ተናግረዋል።

በመጨረሻም የብሔራዊ ባንክ ቦርድ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ መተግበሪያዎቹ ስራ መጀርመር እንዲችሉ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን ሰኞ ደግሞ ለአቢሲኒያ ባንክ ደብዳቤ እንደተጻፈ ዋዜማ ሰምታለች። ውሳኔው ለአቢሲኒያ ባንክ ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሊሎችም ባንኮች ተመሳሳይ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚፈቅድ ነው።  

ሁለቱም መተግበሪያዎች ከሌሎች ባንኮችም ጋር በመተባበር አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚፈልጉ ናቸው። 

ካሽጎ የተለያዪ በመተግበሪያው ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎችን አድርጎ በሚቀጥሉት ቀናት ስራ እንደሚጀምር ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።  

ካሽጎ ለ6 ወር አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን በቀን እስከ 50,000 ዶላር ደረስ ያለምንም የአገልግሎት ክፍያ ይላክበት ነበር። በተመሳሳይ ማማ ፔይስም በወር እስከ 200,000 ዶላር ይተላለፍበት የነበረ ሲሆን ለማንኛውም የሚላክ ገንዘብ 1 ዶላር አገልግሎት ክፍያ ያስከፍላል። 

ኢትዮጵያ በኃዋላ ብቻ በአመት ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ ታገኛለች። [ዋዜማ ራዲዮ]