ዋዜማ ራዲዮ- የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የኢትዮዽያና ኤርትራ የድንበር ውዝግብን ለመፍታት ስለለገመ የሀያላኑ ሀገራት መሪዎች ጫና እንዲያደርጉ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለየሀገራቱ ልከዋል።

ለዩናይትድ ስቴትስ ለእንግሊዝ ለፈረንሳይ ለሩሲያና ለሌሎቹም ሀገራት በተላከው በዚህ ደብዳቤ የድንበር ኮምሽኑ ውሳኔ ይግባኝ የሌለው  መሆኑ እየታወቀ ኢትዮዽያ በሀይል ከያዘችው መሬት ለቃ እንድትወጣ ለማድረግ ሀያላኑ ሀገራትና የተባበሩት መንግስታት አንዳችም እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።  ይልቁንም በኤርትራ ላይ ፍርደ ገምድል ማዕቀብ እንዲጣልባት መደረጉ ኣሳዛኝ መሆኑን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አመልክተዋል።
ኤርትራ ይህን መሰሉን አቤቱታ ስታቀርብ ያሁኑ የመጀመሪያዋ አይደለም። ይሁንና በዩናትይድ ስቴትስ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከኢትዮዽያ ጋር ያለው ግንኙነት የተቀዛቀዘ መሆኑና ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኤርትራን እንደ አጋር ወስደው የሀይል ሚዛኑን ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ ለመቀልበስ ያለመ መሆኑን ለኤርትራ መንግስት በማማከር አገልግሎት የዲፕሎማሲ ድጋፍ የሚያደርጉ ምንጮች ጥርጣሬያቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።
የቀድሞ የአሜሪካ ድፕሎማት ሀርማን ኮህን ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሏቸው ለኤርትራ የዲፕሎማሲ ማግባባት (ሎቢ) ስራ እንደሚሰሩ ይታወቃል። ኤርትራ በአውሮፓም ተመሳሳይ አማካሪዎችን በመቅጠር ድምጿን ለማሰማት እየሞከረች ነው።