kembataዋዜማ ራዲዮ- ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥር እስከ ሦስት ሺህ የሚቆጠሩ የሀዲያ፣ የወላይታ እንዲሁም የሲዳማና የከምባታ  ተወላጆችን እያፈነ በማዕከላዊና ሌሎች እስር ቤቶች በማጎር ላይ እንደሚገኝ የዋዜማ ምንጮች ገለጹ፡፡

በርካታ የደቡብ ወጣቶች ይኖሩበታል ተብሎ የሚገመተው ገርጂ ሮባሰላም ሰፈርእንዲሁም ወረገኑ ባለፉት ሦስት ቀናት ከአንድ ሺህ የሚልቁ ወጣቶች በሽፍን መኪና ታፍነው እንደተወሰዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በተለያየ የአዲስ አበባ ሰፈሮች በጉልበት ሥራ፣ በታክሲ ረዳትነትና በሊስትሮነት የሚተዳደሩ ወጣቶች በቡድን አንድ ክፍል ቤት በመከራየት ኑሮን የሚገፉት በዚህ ገርጂ ሮባ ሰላም ሰፈርና ወረገኑ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በነዚህ ሰፈሮች በአንድ ክፍል ዉስጥ እስከ 15 ወጣቶች ተዳብለው የሚተኙባቸው በርካታ ግቢዎች መኖራቸው ይነገራል፡፡

ፖሊስ ትኩረቱን በይበልጥ በተለይም በሰላም ሰፈር ያደረገው በከባድ ወንጀል የሚጠረጠሩ የደቡብ ወጣቶች በአካባቢው እየመሸጉ እንደሆነ መረጃ ስለደረሰው ነው ተብሏል፡፡ ገርጂ ሮባ አካባቢ ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ሰባት ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ አምሽተው ሲገቡ በወጣት ወንጀለኞች አንገታቸው ተቀጭቶ ለሞት እንደተዳረጉ ፖሊስ ይናገራል፡፡ ድርጊቱን የሚፈጽሙት ወጣቶችም በአካባቢው በሚገኘው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የመቃብር ስፍራ በመሸሽ እንደሚሰወሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ከአንድ ወር በፊት ወደ ክፍለ አገር ለመሳፈር በማለዳ የተነሱ ሌላ አባት አንገታቸው ተቀጭቶ፣ ሻንጣቸው ተዘርፎ በአካባቢው ሞተው መገኘታቸው እያነጋገረ ቆይቷል፡፡

ይህ ሰውን በምሽትና በማለዳ አንገት ቀጭቶ የመግደል ክስተት በሌሎችም የአዲስ አበባ ሰፈሮች እየተዘወተረ መሆኑ የከተማዋን ፖሊስ በእጅጉ ሳያሳስበው አልቀረም፡፡ ነዋሪዎች እነዚህን ወንጀሎች በብዛት የሚፈጽሙት ቀን ቀን ጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የደቡብ ወጣቶች እንደሆኑ ለፖሊስ ተደጋጋሚ ጥቆማ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ የሰፈሩ ነዋሪዎችም እነዚህን ‹‹መጤ›› ወጣቶች በከፍተኛ ጥርጣሬ እንደሚመለከቷቸው፣ ከድርጊታቸው በመነሳትም ‹‹ቀን ቀን ሊስትሮ፣ ማታ ላቦሮ›› በሚል እንደሚጠሯቸው ይነገራል፡፡ ለዚህም ይመስላል ወንጀሎች በተፈጸሙ ማግስት በርካታ በሥራ ላይ የሚገኙ የሀድያና የወላይታ ተወላጆች በቁጥጥር ስር ማዋል እየተወዘተረ የመጣው፡፡

ትናንት ማምሻውንና ዛሬ ጠዋት የነዚህ ብሔር ተወላጆች በብዛት ያርፉባቸዋል ተብለው የሚገመቱባቸው ሰፈሮች በፖሊስ ከበባ ተደርጎባቸው ነበር ተብሏል፡፡ መርካቶ አሜሪካን ግቢ በርካታ የሀድያ ብሔር ተወላጆች እንደታፈሱ ሲታወቅ፣ በአራት ኪሎና አምስት ኪሎ ሰፈሮች ማለዳ ካፌ ደጅ፣ ጆሊ ባር መደዳና 4ኪሎ ዩኒቨርስቲ መግቢያ በር በሊስትሮነት የተሰማሩ በርከት ያሉ ወጣቶች ዛሬ ጠዋት በሥራ ላይ ሳሉ በበርካታ ፓትሮል መኪኖች ተጭነው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል፡፡

ዋዜማ ያነጋገረችው አንድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ባልደረባ ስለጉዳዩ ሙሉ መረጃ እንደሌለው ገልጾ ሆኖም ግን የወላይታና ሀድያ ብሔር ተወላጆች ወደዋና ከተማ በስፋት መፍለስን ተከትሎ በከተማዋ ወንጀሎች መበራከታቸው በፖሊስ በስፋት እንደሚታመን፣ በየሰፈሩ 24 ሰዓት ዉስጥ ከሚመዘገቡ በርካታ የወንጀል ተግባራት ዉስጥ ከግማሽ በላዩን የሚፈጽሙት ከእነዚህ አካባቢዎች የመጡ ተወላጆች እንደሆኑ በየስብሰባው እንደሚነገር አብራርቷል፡፡

ከቆሙ መኪናዎች መስታወት ሰብሮ ገንዘብና ላፕቶፕ መስረቅ፣ የመኪና ስፖኪዮዎችን መንቀል፣ አምሽተው በሚገቡ ነዋሪዎች ላይ አንገት ቀጭቶ መዝረፍ፣ በኮብልስቶን ድንጋይ ጭንቅላትን በመምታት ከተጎጂ ላይ የኪስ ቦርሳ መውሰድ፣ የሞባይል ቅሚያና ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች አሁን አሁን በከተማዋ በስፋት እየተዘወተሩ የሚገኙ ዕለታዊ ተግባራት እንደሆኑ የፖሊሱ ባልደረባ ይናገራል፡፡ 

ወንጀሉን ከፈጸሙ በኋላ ወደ አገራቸው ተሳፍረው ይሄዳሉ፡፡ በቀን በየጣቢያው ብዙ ወንጀል ነው የሚመዘገበው፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ኅዳር ወር ላይ አንድ ልዩ ግብረኃይል ማዋቀሩን አውቃለሁ፡፡ ልጆቹን ከትውልድ ቦታቸው ድረስ ተከታትሎ የመያዝ ሥራ እንዲሰራ ነበር ግርማይ ያቋቋመውይላል ይኸው የፖሊስ ባልደረባ፡፡

በተያያዘ ዜና ዛሬ (ሀሙስ) ሌሊቱን በገርጂ ብርሃን ባንክ የዘረፋ ሙከራ መደረጉንና ጉዳዩን ፖሊስ እየተከታተለው እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡ ዘረፋውን የመሩት በአካባቢው የሚገኙ የደቡብ ወጣቶች ናቸው በሚል በሰላም ሰፈር አዲስ አፈሳ መጀመሩንም ሰምተናል፡፡