በሺ የሚቆጠሩ ሊስትሮዎች በቴዲ ምክንያት ሥራ ቀይረዋል

ዋዜማ ራዲዮ-ዛሬ እጅግ ማልደው የተነሱና የቴዲን አዲስ አልበም በጀርባቸው ያዘሉ በርካታ ወጣቶች በመላው አዲስ አበባ በሥራ ተጠምደዋል፡፡

ሊስትሮዎች ብቻ አይደሉም ሥራ የቀየሩት፡፡ የመንገድ ላይ ፓርኪንግ  ሠራተኞች፣ የሞባይል ካርድ ቸርቻሪዎች፣ ጋዜጣ አዙዋሪዎች፣ ማስቲካ አዝዋሪዎች፣ ዝርዝር ሳንቲም አቅራቢዎች በበርካታ ቁጥር ሲዲውን በመሸጥ ለጊዜው መደበኛ ሥራቸውን አቁመዋል፡፡

አራት ኪሎ ከማለዳው 12፡30 ጀምሮ ሞንታርቦ የተጫነ ነጭ ሚኒባስ መኪና በርካታ ሲዲ በመሸጥ ላይ ነበር ፣በመኪናው ዙርያ የገበያ ግርግር በመፈጠሩ ጧት ላይ መኪናው በፖሊሶች እንዲንቀሳቀስ ተደርጓል ብለዋል የዐይን እማኞች፡፡

በርካታ መጽሐፍ አዝዋሪዎችም በዚህ ገበያ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሆነ የዋዜማ ዘጋቢዎች በተዘዋወሩባቸው ሰፈሮች ለመታዘብ ችለዋል፡፡ ካዛንቺስ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ አካባቢ አንድ ወጣት በድምጽ ማጉያ እየታገዘ ‹‹ የቴዲሻን  ምርጥ ሥራዎች በአምሳ አምሳ ብር፣ አልሰማንም አላየንም እንዳትሉ…›› በሚል ሰፊ ገበያ እንዳገኘ ማየት ችለናል፡፡ መገናኛ አደባባይ፣ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ብሔራዊና ስታዲየም ‹‹ቴዲን በ50 ብር›› የሚሉ ወጣቶች በፌስታል በርካታ ሲዲ ይዘው ሲሸጡ ይታያሉ፡፡

በከተማዋ ዉስጥ የሚዘዋወሩ አብዛኛዎቹ ታክሲዎች የቴዲን ሙዚቃ በማጫወት ላይ እንደነበሩ መታዘብ ችለናል፡፡ ከጀሞ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ሦስት ታክሲ ይዛ እንደመጣች ለሪፖርተራችን የተናገረች ወጣት እስካሁን በገባችባቸው ሁሉም ታክሲዎች  አዲሱ የቴዲ ሙዚቃ እየተቀነቀነ እንደነበር ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡

አንድ የጥበብ ሥራ በአንድ ከተማ በዚህን ያህል ጉጉት ሲሸጥ ስመለከት በኔ እድሜ የመጀመርዬ ነው ያለ የገርጂ ኮንዶምንየም ነዋሪ በተንቀሳቀሰበት ሁሉ ሰዎች ሲዲውን ይዘው መመልከቱ እጅግ እንዳስገረመው አልሸሸገም፡፡ ‹‹ከጧት እስከአሁን ብዙ ቦታ ተዘዋውሪያለሁ፤ ሰው አዲስ ነገር እንደተራበ በግልጽ ማየት ትችላለህ›› ሲል ሐሳቡን ያክላል፡፡

ትንናት ማምሻውን ለዋና ዋና ክልል አከፋፋዮች እንደደረሰ የተነገረው የቴዲ አዲስ ሥራ ዛሬ ረቡዕ በመላ አዲስ አበባ ሲከፋፈል የዋጋ ተመኑ ከ50 ብር እስከ 120 ብር ነበር፡፡ ማልደው የተነሱ አዝዋሪዎች መታገስ ላልቻሉ የሙዚቀኛው አድናቂዎች ሲዲሰው ከ100 ብር ጀምሮ በመሸጥ ጠቀም ያለ ትርፍ ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹እኔ ተከራክሬ 70 ብር ነው የሸጡልኝ›› ያለች አንዲት በፒያሳ መብራት ኃይል አፓርትመንት የምትኖር ወጣት ‹‹ለቴዲ ምንም ነገር ብከፍል አይቆጨኝም›› ትላለች፡፡ የሲዲ የማከፋፈያ ዋጋ በተለምዶ ከ15-20 ብር ሲሆን የቴዲ አልበም ስለምን በተጋነነ ዋጋ እንደቀረበ ማወቅ አልተቻለም፡፡ ምናልባት ገበያው እየተረጋጋ ሲመጣ እስከ የሲዲው ዋጋ ወደ 30 ብር ሊወርድ  እንደሚችል ተነግሯል፡፡ በድሬዳዋ፣ በሐረር እና ሌሎች ሲዲው በደረሰባቸው ከተሞች ሙሉ ግጥሙ ያለባቸው ሲዲዎች ከመቶ ብር ጀምሮ እየተሸጠ እንደሆነ ዘጋቢዎቻችን በስልክ ማጣራት ችለዋል፡፡

እስከአሁን ባለው ሁኔታ በዋና ዋና የከተማዋ መስቀለኛ መንገዶች በርካታ ታዳጊዎች ለአሽከርካሪዎች ሲዲዉን እየሸጡ ሲሆን የዋጋ ተመናቸው 50 ብር ብቻ ነው፡፡ ኾኖም ከከተማ ራቅ ባሉ ሰፈሮች ሲዲው እስከ 120 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ለመታዘብ ችለናል፡፡

ቡቲኮች፣ ካፌዎች፣ የሕዝብ ተሸከርካሪዎች፣ የቤት መኪኖች እንዲሁም ኤፍ ኤም ጣቢያዎች የቴዲን አዲስ አልበም እያጫወቱ ሲሆን አዲስ አበባ ለዛሬ ከቴዲ ድምጽ ዉጭ መስማት የምትፈልገው ነገር የሌለ አስመስሎባታል፡፡