Addis Taxi

  • አመጽ ቀስቃሽ የታክሲ ጥቅሶችን በአስቸኳይ እንዲያነሱ ተነግሯቸዋል

ዋዜማ ራዲዮ- ካለፈው ሳምንት ሚያዚያ 11 ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ስቴዲየም በሚገኘው የመንገዶች ባለሥልጣን አዳራሽ በፈረቃ ከመንግሥት ሰዎች ጋር እየተወያዩ የሚገኙት ባለ ኮድ አንድ የታክሲ ሾፌሮች በቁጥር ከ5ሺ ይልቃሉ፡፡
ውይይቱ የተዘጋጀው በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ሲሆን አዲስ የወጣውን የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደነብ ቁጥር 395/2009 ከሚመለታቸው አካላት ጋር ለማስተዋወቅ የተሰናዳ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ኾኖም መድረኩ ቅሬታና የዓመታት ብሶት ገንፍሎ በወጣባቸው የታክሲ ባለንብረቶችና ሾፌሮች ቁጥጥር ሥር ወድቋል ለማለት ያስደፍራል፡፡
በሰባቱ ቀናት ስብሰባ የመናገር እድል የተሰጣቸው ተወያዮች መንግሥትን ክፉኛ የተቹ ሲሆን የብዙዎቹ አቤቱታ “መንግሥት እኛን እንደተቃዋሚ ፓርቲ እንጂ እንደ አገልግሎት ሰጪ አድርጎ አይመለከተንም” የሚል ነው፡፡
“እኛን ከመክሰሳችሁ በፊት ራሳችሁን ብትፈትሹ ጥሩ ነበር” ያሉ አንድ የታክሲ ባለንብረት “በአገሪቱ ሙስና የተፈለፈለው ከናንተ ቢሮ አይደለምን?” ሲሉ ጉቦ የማይጠይቅ ትራፊክ በአዲስ አበባ በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ ፈልጎ ማግኘት እንደማይቻል የ15 ዓመት ልምዳቸውን በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡
በየቀኑ ከ10 እስከ 20 የሚሆኑ ታዳሚዎች ሐሳባቸውን እንዲሰጡ በተደረገበት በዚህ ዉይይት ፖለቲካዊ መንፈስ የነበራቸው ድምጾችም ተሰምተዋል፡፡
“በ97 ምርጫ ዋዜማ ለሰልፈኞች ነጻ ትራንስፖርት ሰጥታችኋል ብላችሁ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በበጎ እንደማታዩን ይገባናል፡፡” ያሉ ሌላ ባለንብረት ንግግራቸው በጭብጨባ ከተቀቋረጠ በኋላ ሐሳባቸውን የቀጠሉ ሲሆን ሁሉም ዘርፎችን መንግሥት ባለው አቅም ሁሉ እየደጎመ ታክሲን ቸል ያለበት ምክንያት ከዚሁ የጠላትን ስሜት የመነጨ እንደሆነ እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ “ለመንግሥት ሠራተኛ በሰበብ አስባቡ ደመወዝ ትጨምራላችሁ፣ የኛን ታሪፍ ለማሻሻል ግን አንድ ቀን እንኳ አስባቸሁ ታውቃለችሁ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በዚህ አስተያየት የተበረታቱ ሌላ የታክሲ ባለንብረት የመናገር እድሉን ያገኙ ሲሆን “እዚህ አገር በሕዝብም በመንግሥትም እየተጠላን፣ ዘላለም እየተረገምን የምንሠራ እኛ ታክሲዎች ነን፡፡” ካሉ በኋላ “ተመስግነን አናውቅ፣ አትርፈን አናውቅ፣ ሕይወታችን ተለውጦ አያውቅ፡፡ እስቲ ከታክሲ ሥራ ተነስቶ እዚህ ደረሰ የተባለ ሰው ንገሩኝ” ሲሉ ታዳሚውን ጠይቀዋል፡፡ “እኔ ንግግሬን በሌላ አትውሰዱብኝና እኛ ታክሲዎች ጧት ተነስተን ባንሠማራ እኮ አገሪቷም ትቆማለች፡፡ መንግሥትም የሚሽመደመድ ይመስለኛል፣ ከናንተ ውስጥ ግን ይህን የሚያስብ ያለ አይመስኝም” ሲሉ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡ ታዳሚውም በጭብጨባ ድጋፉን ገልጾላቸዋል፡፡
” ለመሆኑ የመኪና መለዋወጫ ዋጋን ታውቃላችሁ? ስፔርፓርት ስንት ነው?” በሚል ጥያቄ የሰነዘሩ ሌላ የታክሲ ባለንብረት፣ “ዛሬ አንድ ስፖኪዮ ቢሰበር ስንት ብር እንደሚያስወጣን ብታውቁ ደፍራችሁ እዚህ ባልጠራችሁን ነበር” ሲሉ ጠንከር ያለ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ “ለነገሩ መንግሥት ሕዝብን መስማት ካቆመ ስለቆየ በናንተ አልፈርድባችሁም፤ እኛ ትዝ የምንላችሁ እኮ አድማ ስንመታ ብቻ ነው፤ ጃንሆይንም ታክሲ ነው ያወረዳቸው፣ ታሪክ ብታውቁ ደፍራችሁ እዚህ አትጠሩንም ነበር” ሲሉ አስተያየት የሰጡ አባት በመድረኩ አስተናባሪዎች ተግሳጽ ደርሶባቸዋል፡፡
” እዚህ መድረክ ስላገኘን ብቻ እንዳመጣልን መናገር ተገቢ አይመስለንም፡፡ ታክሲዎች ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ ይቅርብኝ ብሎ ያለቀረጥ ከአንድ ሺ በላይ ታክሲዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የተደረገውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የትርፍ ህዳጋችን መጨመር አለበት፣ ሥራው በሚፈለገው መልኩ እያተረፈን አይደለም የሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ እኛ ካመጽን አገር ትቆማለች ማለት ግን ኃላፊነት የጎደለው ንግግር ነው፤ መንግሥት እናንተ የምታገኙት ትርፍ ወቅቱን ያገናዘበ እንዳልሆነ ይረዳል፡፡ ለዚህም ጥናት እያደረገ ነው፡፡ በዚህ ዓመት የታሪፍ ማሻሻያ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡” የሚል ምላሽ ከመድረክ መሪዎች በአንዱ ተሰጥቷል፡፡
ሊፋንና ሳሎን በሚል የሚጠሩ የቢጫ ታክሲ ባለንብረቶች “የባንክ ብድር መክፈል እንደተሳናቸው፣ ቤተሰባቸውን ለመበተን ቋፍ ላይ እንደሆኑ በመናገር ከፍ ያለ ብሶት ያሰሙ ሲሆን” በኪሎ ሜትር ደንበኞችን እንዲያስከፍሉ የተተመነው ዋጋ ቅሬታ እንደፈጠረባቸውና ይህን ቅሬታ የሚሰማ ባለሥልጣን ግን እንደሌለ በተከታታይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“ከመንግሥት ይልቅ ተሳፋሪ ደንበኞች የዋጋ ተመኑን ማነስ ተረድተው ቲፕ ይሰጡናል፡፡ ለምንድነው እንደጠላት የምታዩን? የባንክ እዳ ውስጥ ነን፤ እኛም እኮ ልጆች አሉን፣ እናስተምራለን፤ እኛም እኮ መብላት መጠጣት አለብን፡፡ እኛም እኮ የቤት ኪራይ አለብን፤ እንዴት ነው በ10 እና በ13 ብር ብድር እየከፈላችሁ ኑሯችሁን ግፉ የምትሉን? ለማን ነው ይሄን ነገር አቤት ማለት ያለብን?” ሲሉ ከፍ ያለ እሮሮ ያሰሙ አንድ የታክሲ ባለንብረት የታክሲ ሥራ ዉስጥ የገቡበትን ወቅት ደጋግመው እንደሚረግሙ ተናግረዋል፡፡
“መንግሥት ሁሉንም ዘርፍ ይደጉማል፣ እኛ ታክሲዎችን ግን እግዛብሔር ምስክሬ ነው አትወዱንም፡፡ ሁሉም አውቶቡሶች መቆሚያ አላቸው፤ ከኛ በኋላ የመጡ እነ ሸገር ባስ፣ አሊያንስ፣ ፐብሊክ ባስ ሁሉ መቆምያ አላቸው፡፡ ታክሲ ይኸው ስንት ዘመን መቆሚያ የለውም፡፡ መቆምያ ሳታዘጋጁ ባልተገባ ቦታ አቁመሀል ብላችሁ ትከሱኛላችሁ፡፡ ተሳፋሪ ወራጅ እያለ ያንቀኛል፡፡ ትራፊክ እንደ ደመኛው ነው የሚያየን፡፡ አንድ እንኳ የተስተካከለ የመንገድ ምልክት ሳትተክሉ እኛን ለመቅጣት ትሮጣላችሁ፡፡ ቀኑን ሙሉ ያለ እረፍት ሮጠን 200 መቶ ብር ይዘን ልንገባ ስንል የ250 ብር ቅጣት ይጻፍብናል፡፡ ይሄ ምን ማለት እንደሆነ ግን ይገባችኋል? ያለ የታክሲ ሾፌር “አንድ ነገር በርግጠኝነት ልንገራችሁ፡፡ እዚህ የሰበሰባችሁን አንዳችንም የተሻለ አማራጭ ብናገኝ ታክሲ ሥራ ላይ አንቆይም፡፡” በማለት ከተናገረ በኋላ ወደ መቀመጫው ሲመለስ ከቤቱ ደማቅ ጭብጨባ ተችሮታል፡፡
የመድረክ መሪው በርከት ያሉ ሀሳችን ከተሳታፊዎች ከተቀበሉ በኋላ መንግሥት የተነሱትን ሐሳቦች በበጎ እንደሚመለከታቸውና ምላሽ እንደሚሰጥባቸው ቃል ገብተዋል፡፡ የታሪክ ማሻሻያ ለማድረግም ጥናት እየተደረገ እንደሆነ ካብራሩ በኋላ አንዳንድ ማሳሰቢያዎችን ለታክሲ ሾፌሮች አድርሰዋል፡፡
“መንግሥት የራሱን የቤት ሥራ ይሠራል፣ እናንተም የራሳችሁን የቤት ሥራ ሥሩ” በሚል የተንደረደሩት ሰብሳቢው ባለታክሲዎች ጾታዊ ትንኮሳን የሚያበረታቱ፣ ሕዝብን ለአመጽ የሚያነሳሱ የታክሲ ጥቅሶችን በተቻለ ፍጥነት እንዲያነሱ አሳስበዋል፡፡ “የምትለጥፏቸው ነገሮች ለናንተ ቀላል ሊመስሉ ይችላሉ፤ መልዕክታቸው ግን አፍራሽ ነው፡፡” ካሉ በኋላ “አንድም ስለናንተ ሕዝብና መንግሥት መልካም ገጽታ እንዳይኖራችሁ የሚያደርጉት እነዚህ ጥቅሶችና ለሥነ ምግባር አለመገዛታችሁ ይመስለኛል” ብለዋል፡፡
ዉይይቱ ካበቃ በኋላ ደንብ ቁጥር 208/2003 በመተካት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው ደንብ 395/2009 ለሾፌሮችና የታክሲ ባለንብረቶች በነጻ ታድሏል፡፡