በሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ጉልህ የተባለ አዲስ የፖሊሲ ማሻሻያ ከሰሞኑ ይደረጋል። ቀድሞ በባንክና ኢንሹራንስ ዘርፍ እንዳይሳተፉ ተከልክለው የነበሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሁን በዘርፉ እንዲሳተፉ የሚያስችል የህግ ማሻሻያ እየተደረገ ነው። 

ዋዜማ ራዲዮ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንዳረጋገጠችው የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆነው ዜግነታቸውን የቀየሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በኢትዮጵያ የባንክና ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ አክስዮን ገዝተው ዘርፉን በኢንቨስትመንት እንዲቀላቀሉ ሰፊ ስራ እየሰራ ነው።

እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የባንክም ሆነ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሆነው በተለያየ መልኩ ዜግነታቸውን ቀይረው ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ግለሰቦችም እንዲሳተፉ አይፈቀድላቸውም ነበር። ከሁለት አመት በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በሀገሪቱ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ውስጥ ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎች አሉ ብሎ አክሲዮናቸውን እንዲያስተላልፉ ካልሆነም እንደሚወርሰው መመሪያ አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል።

እነዚህ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አንድም በስራ በሌላ በኩል በትምህርት ወጥተው የውጭ ሀገር ዜጋ የሆኑ ናቸው።ኢትዮጵያ የሁለት ሀገር ዜግነትን ስለማትቀበልም ግለሰቦቹ በባንክና ኢንሹራንስ ዘርፍ ላይ የመሳተፍ እድላቸውን ተነጥቀዋል።በዚህ ሳቢያ በርካታ ግለሰቦችች ብሄራዊ ባንክ ላይ ክስ ከፍተው ሲከራከሩም ነበር።በግልባጩ ደግሞ ከባንክና ኢንሹራንስ ዘርፉ እንዲወጡ የተደረጉ ባለአክስዮኖችን ድርሻ መልሶ ለመግዛት ገበያው ተጧጡፎ እንደነበርም አይዘነጋም።

አሁን ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግስት ዲያስፖራዎች በፋይናንስ ዘርፍ ላይ ባለ አክስዮን ሆነው እንዲሰማሩ ለማድረግ ከጫፍ ደርሷል።ይህም ግለሰቦቹ በውጭ ምንዛሬ አክስዮን እንዲገዙ የሚመቻች በመሆኑ የባንኮችን የካፒታል አቅም ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የፈይናንስ ዘርፍ ወደፊት መከፈቱ ስለማይቀር የሀገር ውስጥ ባንኮች ለመጠናከር እድል ይሰጣቸዋል።
በሀገር ውስጥ ያሉት ባንኮች የሸጡት አክስዮን ከአንድ ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ብዙም እንደማይበልጥ መረጃዎች ያሳያሉ።ይህ ደግሞ ዘርፉ አንዴ ቢከፈት የአንድ የውጭ ኩባንያ አቅም እንደሆነና መወዳደር አይችሉም ተብሎ ይታመናል። በተለይ የንግድ ባንኮችም አቅማቸውን በካፒታል ከማጠናከር ይልቅ በርካታ ትርፍ መከፋፈል ላይ ማተኮራቸው ሲያስተቻቸው ቆይቷል

መንግስት አሁን ላይ ዲያስፖራውን በፋይናንስ ዘርፍ ላይ ለማሳተፍ ያስጀመረው ጥናትን እያገባደደ ሲሆን በቅርቡ ተመክሮበት ተግባራዊ እንደሚሆን ከምንጫችን አረጋግጠናል።ይህም ትልቅ የፖሊሲ ለውጥ መሆኑ ታምኖበታል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ሁለት የመንግስተና 16 የግል ባንኮች አሏት። ባንኮቹ ልማት ባንክን ሳይጨምር ያላቸው የቁጠባ ተቀማጭ 800 ቢሊየን ብር ደርሷል። [ዋዜማ ራዲዮ]
የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ

https://youtu.be/O8kquSy14Gs