በሀገሪቱ ግዙፍ ከሚባሉት የግንባታ ተቋራጭ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ተክለብርሀን አምባዬ ኮንስትራክሽን በግንባታ ዘርፍ መቀዛቀዝና ከፍ ባለ የታክስ ዕዳ ክፍያ ሳቢያ ወደ ቀውስ ገብቷል። ሰራተኞች ለስድስት ወራት ያህል ደሞዝ አልተከፈላቸውም።

ዋዜማ ራዲዮ- በሀገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ የግንባታ ተቋራጮች መካከል አውራየሆነው ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን በስሩ ከ1 ሺህ በላይ ጊዜያዊ እና ቋሚ ሰራተኞችን ይዞ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመውሰድ ሲሰራ ቆየታል፡፡ ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ የሚተመኑ ስራዎችን በመሠራት የዘለቀው የግንባታ ድርጀቱ ከኢትዮጵያ ውጪም በሶማሊላንድ አውሮፕላን ማረያፊ እስከ መገንባት የደረሰ ሲሆን በዩጋንዳም በሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ሃሳብ ነበረው፡፡


ነገር ግን የዚህ በጀት አመት ከጀመረበት ከሰኔ 2010 ጀምሮ ለኩባንያው ጥሩ ግዜ እንዳልሆነ ምንጮቻችን ይናገራሉ፡፡ ቀዳሚው ነገር የአቢይ አህመድ አስተዳደር በዚህ አመት አዳዲስ ፕሮጀክትን ለመገንባት ስራዎች ከመጀመር ይልቅ ሳይጠናቀቁ የተጓተቱትን መጨረስ ላይ ማተኮሩ መሆኑን ያስቀምጣሉ፡፡ ቀድሞም ቢሆን የመንግስትን አጠቃላይ በጀት ቀመር እና የአመቱን ትኩረት በመለየት የግንበታው ዘርፍ ላይ በየአመቱ ዝግጅት ለሚያደርጉት የግንባታ ተቋራጭ ድርጅቶች ይህ የመንግስት ውሳኔ ስራቸው በእጅጉ እንዲቀዛቀዝ ያደረገ ሆኗል።


በአንድ የግንባታ ድርጅት ውስጥ በፕሮጀክት አዋጭነት ላይ የሚሰራ ባለሙያ ሀሳቡን ለዋዜማ ሲናገር የእሱን ድርጅት ጨምሮ አብዛኞቹ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ተቋራጮች የአመቱን የስራ ትኩረት የሚለዩት መንግስት ከፍተኛውን ወጪ የመደበበትን ዘርፍ ቀድሞ በመለየት መሆኑን ያስታውሳል፡፡ ዘንድሮ ግን አዲስ የግንባታ ፕሮጅክቶች ላይ መንግስት የተከተለው አቅጣጫ ለዘርፉ ተዋናዮች መልካም ዜና አይደለም።


በግንባታው ዘርፍ ቀዳሚ ስም ካላቸው ተቃራጮች መካከል ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን አውራ ነው፡፡ የድርጅቱ ሰራተኞች እንደነገሩን ደሞዝ ከተከፈላቸው 6 ወራት ተቆጥሯል። ምንጮቻችን እንደሚሉት ለቋሚ ሰራተኞቹ ያቀረበው “ለጥቂት ግዜ ታገሱኝ” ተማጽኖን በመቀበል አብዛኞቹ ሰራተኞች ቢቆዩም ጠዋት ገብተው ማታ ከመውጣት የዘለለ ስራ እየሰሩ አይደለም፡፡


በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ተክለ ብርሃን አምባይ ለረጅም ግዜ ሳይከፍል የቆየውን ግብር ከ68 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ በቅርቡ እንዲከፍል መደረጉም ድርጅቱን ለተጨማሪ የፋይናንስ ጫና እንደዳረገው ምንጮቻችን ይናገራሉ፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ በኢንቨስትመንት በስፋት ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች መካከል የባንክ እዳ ጫና ካለባቸው ድርጅቶች ውስጥ ተክለብርሃን አምባዬ ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደሚሰለፍ ዋዜማ መረጃውን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምንጮቿ አረጋግጣለች፡፡ ምንጮቻችን እንደሚሉት ድርጅቱ በእጁ የሚገኘው ሀብትና በባንክ ያለበት የእዳ ጫናም ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]

https://youtu.be/O8kquSy14Gs