Birhanu Nega Leader of EZEMA- Photo Credit EZEMA

ዋዜማ- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ኢዜማ አባላቱ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ ፓርቲው ያዘጋጀው የአምስት አመት የፖለቲካ ሂደትን የሚገመግም ሰነድ ላይ ውይይት አያደረገ ነው። ይሁንና ተጨማሪ 41 የፓርቲው የምርጫ ወረዳ አመራርና መደበኛ አባላት ድርጅቱን ለቀው መውጣታቸውን ለዋዜማ በላኩት መግለጫ ገልፀዋል።


በኢዜማ ውስጥ ፓርቲው ከገዥው ብልፅግና ፓርቲ ጋር ባለው ግንኙነት ዙሪያ የሰነበተ አለመግባባት እንደነበረ ሲነገር ቆይቷል። ባለፉት ቀናትም የቀድሞ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በተለያየ ደረጃ ያሉ አባላት ከፓርቲው ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል። በዛሬው ዕለትም በምርጫ ወረዳ 2/14 ያሉ 41 ብሄራዊ የስራ አሰፈፃሚ አባላትና መደበኛ አባላት ራሳቸውን አግለዋል። የኢዜማ መሪዎች በጉዳዩ ላይ ለዋዜማ ምላሽ ሰጥተዋል።


የኢዜማ አመራር ያለፉትን ሁለት ቀናት በአምስት ዓመቱ የፖለቲካ ሂደት ላይ ሰነድ አዘጋጅቶ ውይይት ማድረግ የጀመረ ሲሆን ውይይቱ ወደታችኛው የድርጅቱ መዋቅር እንደሚቀጥልም አስታውቋል። የውይይት ሰነዱን ይዘት ፓርቲው ይፋ አላደረገም። ይሁንና አሁንም በፓርቲው ውስጥ ያሉ አባላት በኢዜማና በመንግስት መካከል ስላለው ግንኙነት አንድ ወጥ አቋም እንደሌላቸው፣ ግን ደግሞ ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ትግል ላይ መሆናቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።

“ኢዜማ የህልውና አደጋ ተጋርጦበታል” ያሉን አንድ የፓርቲው አባል ችግሩን በቀጣይ ቀናት መፍታት ካልተቻለ ፓርቲው የሚፈለገውን የህዝብ ድጋፍ አግኝቶ መቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው ብለውናል።
ከፓርቲው ራሳቸውን ያገለሉ ሌላ የቀድሞ ከፍተኛ አመራር በበኩላቸው “አሁን ሰነድ ተዘጋጅቶ እየተደረገ ያለው ውይይት ኢዜማ ከብልፅግና ጋር ያለውን ትብብር ቅቡልነት እንዲያገኝ ለማሳመን በተወሰኑ የፓርቲው አመራሮች ፍላጎት የተሰናዳ ሰነድ ነው” ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ።

ሰኞ ዕለት ከፓርቲው መልቀቃቸውን ያሳወቁት 41 አባላት በመግለጫቸው ፓርቲውን በውስጠ ትግል ለመቀየር ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካ ይገልፃሉ።


“ኢዜማ በአመራሩ ደካማ አቋምና የአላማ ክህደት መንገዱን ቢስትም ወደ ትክክለኛ ሕዝባዊ አላማው ተመልሶ ለዜግነት ፖለቲካ ምሰሶና አሰባሳቢ እንዲሆን ለማድረግ በየደረጃው ያደረግነው እልህ አስጨራሽ የውስጥ ትግል ውጤት ማምጣት እንደማይችል በመረዳታችን ከዚህ በታች ስማችን የተጠቀሰው የኢዜማ ምርጫ ወረዳ 2/14 አመራሮችና እና አባላት ከዛሬ ዕለት ጀምሮ ከፓርቲው ለቀን በመውጣት የተለየን መሆናችንን እናሳውቃለን” ብለዋል ባሰራጩት የፅሁፍ መግለጫ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ሙለእለም ተገኝወርቅ በቅርቡ ከፓርቲው የለቀቁት የቀድሞ አመራሮች በፓርቲው ቀጣይ ዕጣፈንታ ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ እንደማይኖረው ከዋዜማ የራዲዮ መጽሔት መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ አጽኖት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡

ኢዜማ በፓርቲ ቁመናውም ሆነ በፍልስፍናው በተዋቂ ግለሰቦች ላይ ያልተንጠላጠለ ከታች ከወረዳ ተወክለው በሚመጡ አባላት የተዋቀረ መሆኑ ከኢትዮጵያ የፓርቲዎች አደረጃጀት  የተለየ እንደሚያደርገው ጠቁምው፤ አሁንም ከፓርቲው የተለዩት አባለት እንደማንኛውም  አባል ራሳቸውን ይዘው ከመረጣቸው የምርጫ ወረዳ ከመለየት በዘለለ በአዜማ መሠረት ላይ ሊፈጥሩት የሚችሉት አደጋ ፍጽሞ አይኖርም ይላሉ፡፡

የቀድሞ አመራሮቹ ለምርጫ ወረዳቸው ተገቢውን የመልቀቂያ ደብዳቤ ሳይሰገቡ ለሚዲያ ፍጆታ በሚውል ርእሰ ወሬ ላይ መጠመዳቸው ከምንም በላይ ለመርህ ያላቸው ታማኝነት ምንያህል ደካም እንደሆነ የሚያሳይ  ነው ያሉት ኃላፊው ፤ ከለቀቁት አባላት ገሚሶቹ የፓርቲውን ሕግ እና ደንብ ባለማክበራቸው የተነሳ የዲሲፕሊን ክሰ ቀርቦባቸው  እና ክሳቸው እየታየ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ፤የተቀሩት ደግሞ በቀድሞው ሊቀመንበር አማካኝነት ከሥራ አስፈጻሚነት ከ2013 ምርጫ በፊት  የተነሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ አመራር ለቀቁ ተብሎ በተለያዩ የመገናኛ አውታር የተዘገበው ዘገባ ፍጽሞ የተሳሳተ ነው፤ ሲሉ አክለዋል ፡፡

“ኢዜማን የገዢው ፓርቲ ተለጣፊ አድርገው የሚከሱት ኃይሎች እውነታውን ከግምት ጥፈው እይደለም ከድምዳሜ ላይ የደረሱት፤  እኛ እየሠራን ያለነው ከመንግሥት ጋር እንጂ ከፓርቲ ጋር አይደለም ፡፡ በዚህም ተቀራርበን በሠራንበት መስክ ትልቅ እምርታ ማስመዝገብ ችለናል” ብለዋል፡፡

“ጥያቄውን እያነሱት ያሉት የተለዩት አባላት፣ ኢዜማ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ መሥራትን በተመለከተ ብያኔ ለመስጠት በጠራው ጉባኤ ላይ የድጋፍ ድምጻቸውን በመለገስም ሆነ በማስወሰን ሒደት  ውስጥ  መሪ ተዋናዮች ነበሩ፡፡ አሁን ይሄን አጀንዳ  እንደ አዲስ ለማንሳት የፈለጉት ትኩረት ለመሳብ እና ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ነው” በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡

የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመጋቢት 02/2015 ዓ.ም ባደረገው 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ያቀቀመው ግብር ኃይል ያዘጋጀው የጥናት ሰነድ  ከሁሉም በላይ በአባላቱ ዘንድ ያለውን የፖለቲካ መስመርን በመገንዘብ  ረገድ ያለውን ክፍተት በመሙላትም ሆነ  ከገዢው ፓርቲ ጋር ያለውን  ግንኙነት በማጥራት ሒደት ውስጥ ሚናው የላቀ እንደሚሆን  የሕዝብ ግኙንነት ኃላፊው ዶ/ር ሙሉአለም ተገኝወርቅ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የኢዜማ ሊቀመንበር የሺዋስ አሠፋን ጨምሮ ሰባት የፓርቲው የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚ አባላት በገዛ ፍቃዳቸው ከፓርቲው አባልነታቸው መልቀቃቸውን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ማስታወቃቸው ይታወሳል። ከኢዜማ አባልነታችን ለቀናል ያሉት፣ ከየሺዋስ በተጨማሪ ሀብታሙ ኪታባ፣ ዳንዔል ሺበሺ፣ ናንሲ ውድነህ፣ ጂአልጋው ጀመረ፣ ተክሌ በቀለ እና ኑሪ ሙደሲር ናቸው። ግለሰቦቹ፣ የፓርቲውን አካሄድ ለማስተካከል ለረጅም ጊዜ ያደረጉት ጥረት “በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ” ምክንያቶች እንዳልተሳካ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። ተሰናባቾቹ ፖለቲከኞች፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ሕዝብንና ፓርቲዎችን አስተባብሮ በማታገል ፋንታ፣ “አገዛዙ እየፈጸመው ላለው አገር ዓቀፍ ግፍ ድጋፍ እየሰጠ” እና “የገዢውን ቡድን እሴቶችና ዓላማዎች እያራመደ” ይገኛል በማለት ከሰዋል። [ዋዜማ]