GERD -FILE

ዋዜማ- የውሀ እና ኤነርጂ ሚኒስቴር በወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዙርያ የሚያማክር ቡድን ማቋቋሙን ዋዜማ ሰምታለች።አማካሪ ቡድኑ የኢትዮጵያን ወሰን በሚያቋርጡ ወንዞች ዙርያ ሊነሱ በሚችሉ የጥቅምም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ሚኒስቴሩን ያማክራል።

አማካሪ ቡድኑ በወሰን ተሻጋሪ ወንዞች በተለይ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከአመታት በፊት ኢትዮጵያን ወክለው በመደራደር የሚታወቁትና በተፋሰስ ላይ ሰፊ ስራ እንደሰሩ በሚነገርላቸው ፈቅአህመድ ነጋሽ ይመራል። 

ፈቅአህመድ ነጋሽ በውሀ እና ኤነርጂ ሚኒስቴር የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክተር ሆነው የሰሩ ሲሆን ; በመቀጠልም የምስራቅ ናይል የቴክኒክ ጽህፈት ቤትን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል። 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ የአማካሪ ቡድኑ ምክትል ሰብሳቢ ናቸው። 

የህዳሴው ግድብ ላይ ቅርብ ጊዜ ድረስ እየተደራደሩ ያሉት የምህንድስና ሙያተኞቹ ጌድዮን አስፋውና ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ ደግሞ የአማካሪ ቡድኑ አባላት ናቸው። 

በለጠ ብርሀኑ  ፣ ተፈራ በየነ  ፣ እምሩ ታምራት  ፣ ዘውዱ ተፈራ  ፣ ሚካኤል መሀሪ እና ዘነበ ላቀውም የአማካሪ ቡድኑ አባል እንዲሆኑ በውሀ እና ኤነርጂ ሚኒስቴር ተመርጠዋል። 

በየወሩ የሚሰበሰበው አማካሪ ቡድን ባለፈው አርብ ግንቦት 18 ቀን 2015 አ.ም የመጀመርያ ስብሰባውን አድርጓል።የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች አማካሪ ቡድኑ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙርያ በሚደረጉ ድርድሮች ውስጥ ተሳታፊ እንደሚሆንም ሰምተናል። 

የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ በግድቡ ዙርያ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር የሚደረጉ ድርድሮችን የሚያማክር ብሎም በድርድሩ የሚሳተፍ ብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ነበር። አባላቱም በብዛት አሁን አማካሪ ቡድን ውስጥ የተካተቱት ሙያተኞች ነበሩ።

ሆኖም የቴክኒክ ኮሚቴው ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የውሀ እና ኤነርጂ ሚኒስትር ሆነው በቆዩባቸው አመታት ተበትኖ ቆይቶ እንደነበር አባላቱ ያነሳሉ። ለዚህ መነሻቸውም መንግስት ኮሚቴውን በትኜዋለሁ ብሎ በይፋ ባይናገርም ከሶስት አመት በላይ ተሰብስቦ አለማወቁን ነው። 

ይህም በህዳሴው ግድብ ድርድር ዙርያ ልምድ ያላቸውን ሙያተኞች እንደማግለል ተቆጥሮ ነበር። ሆኖም አማካሪ ቡድኑ ከዚህ ቀደም ከነበረውም ሰፋ ያለ ስራ ተሰጥቶት ከውሀና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ጋር የመጀመርያ ስብሰባውን በማድረግ ስራውን ጀምሯል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳይ ከአሜሪካ እና አለም ባንክ እጅ ከወጣ በኋላ ፣ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሲካሄድ ቆይቷል።  የተባበሩት አረብ ዔምሬትም አመቻች ሆና ሌላ ውይይት ከግብጽና ሱዳን ጋር ተደርጓል። ነገር ግን ግብጽና ሱዳን በሚያነሷቸው ፍላጎቶች እንዲሁም በሱዳን ወቅታዊ ችግር ሳቢያ ድርድሩ በእንጥልጥል ይገኛል። [ዋዜማ]