ዋዜማ- በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 15ኛ ቀን ውሎ “ስልታዊ” ቡድኖች በተጠናቀሩ ምክረ ሀሳቦች ዙሪያ ተመካክረዋል። በንዑስ ቡድን ደረጃ የተዘጋጁ የምክረ ሀሳብ ቃለ ጉባኤዎች ተጠናቅረው ወደ ስልታዊ ቡድን እንዲያድጉ የተደረገ ሲሆን፤ የስልታዊ ቡድኖች አባላት አልተካተቱም ያሏቸውን ሀሳቦች በማንሳት፣ ሊካተቱ አይገባም የሚሏቸውንም በመጠቆም የሞቀ ምክክር ማድረጋቸውን የነገሩን ከዋዜማ ምንጮች ፤ ይህ ሂደት ለቀናት እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። 

ሕዝበ ውሳኔ የተጠየቀባቸው ጉዳዮች

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለተመካካሪዎች ባቀረበው “የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት” ሰነድ መሰረት በሁለት ሁኔታዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ሊወሰን ይችላል። የመጀመሪያው ሁኔታ፤ በምክክር ሂደቱ የውሳኔ አሰጣጥ ሳይፈቱ ቀሪ የተደረጉ “መሰረታዊ” ጉዳዮች በሕዝበ ውሳኔ እንዲፈቱ ተሳታፊዎች ሲጠይቁ መሆኑን ሰነዱ ይጠቁማል።

ሁለተኛው ሁኔታ ደግሞ፤ በሀገራዊ ምክክር ጠቅላላ ጉባኤ ጠንካራ ተቃውሞ የሚገጥመው ምክረ ሀሳብ ሲያጋጥም መሆኑን ሰነዱ ያመላክታል። ምክክሩ አሁን ያለበት ሂደት ምክረ ሀሳቦችን በድምጽ አሰጣጥ ማሳለፍ ወይም መጣል ላይ ያልደረሰ ቢሆንም፤ ተመካካሪዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድባቸው የጠየቁባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ከዋዜማ ምንጮች ሰምተናል።

በተመካካሪዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲሰጡባቸው የተጠየቀባቸው ጉዳዮችም በ”ሀገር ግንባታ” አጀንዳ ውስጥ የሚገኙ ንዑስ አጀንዳዎች መሆናቸውን ምንጮች ነግረውናል። ለአጀንዳው ከተዘጋጁ መሪ ጥያቄዎች መካከል የክልል ሰንደቅ ዓላማዎች እና የክልል መዝሙሮች አስፈላጊነትን የሚመለከቱ ጥያቄዎች የሚገኙ ሲሆን፤ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ምክረ ሀሳቦችን ካቀረቡ ተመካካሪዎች መካከል “ሕዝበ ውሳኔ” እንዲካሄድ የጠየቁ እንደሚገኙበት ምንጮች ነግረውናል።

ክልሎች “አርማ” እንዲኖራቸው የጠየቁ፣ ሰንደቅ ዓላማም ይሁን አርማ መኖር የለበትም ያሉ፣ የክልል መዝሙር ያስፈልጋል ያሉ፣ በተቃራኒው የክልል መዝሙር አያስፈልግም ያሉ እንዲሁም ብሔራዊ መዝሙር በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ አገልግሎት ላይ እንዲውል የጠየቁ መኖራቸውን ሰምተናል። አዲስ ብሔራዊ መዝሙር እንዲዘጋጅ የጠየቁ ስለመኖራቸው የነገሩን ምንጮች፤ የብሔራዊ መዝሙር ጉዳይ ወደ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያመራ መጠየቁንም ጠቁመዋል።

የምርጫ ሥርዓት ለውጥ 

በመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ አጀንዳ ውስጥ የተካተተው “የኢትዮጵያ የምርጫ ሥርዓት” ንዑስ አጀንዳ፤ “የአብላጫ ድምጽ ሥርዓትን ማስቀጠል”፣ “ተመጣጣኝ የውክልና ሥርዓትን መከተል” እና “ቅይጥ የውክልና ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ” የሚሉ አማራጮች የቀረቡለት ሲሆን፤ ተመካካሪዎች በሁለቱ አማራጮች ዙሪያ ምክረ ሀሳቦችን አቅርበዋል። ተመጣጣኝ የውክልና ሥርዓት እና ቅይጥ የውክልና ሥርዓት፤ ተመካካሪዎችን ለሁለት ጎራ ከፍለው ያነጋገሩ መሆናቸውን የገለጡልን ምንጫችን፤ ተመጣጣኝ የውክልና ሥርዓት በበርካቶች ድጋፍ ያገኘ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

በምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁለቱ አማራጮች ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችን የሰነዘሩ ሲሆን፤ በሥራ ላይ ያለው የአብላጫ ድምጽ ሥርዓት በቂ ድጋፍ ሳያገኝ ቀርቷል። የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ተወካዮች ተመጣጣኝ የውክልና ሥርዓትን የሚደግፍ አስተያየት መሰንዘራቸውንም ሰምተናል። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅይጥ የውክልና ሥርዓት ዙሪያ ጠንካራ አቋማቸውን ቢገልጹም፤ ቀጣዩ የምርጫ ሥርዓት ተመጣጣኝ የውክልና ሥርዓት የመሆን ዕድሉ ሰፊ ስለመሆኑ ምንጮች አረጋግጠውልናል። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት “የተለየ” ውክልና

በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግስት አንቀጽ 54 መሠረት የተለየ ውክልና ያስፈልጋቸዋል ተብሎ የታመነባቸው “አናሳ” ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ20 የማያንስ መቀመጫ እንደሚኖራቸው ተደንግጓል። ይህ የመቀመጫ ብዛት አነስተኛ መሆኑን ያነሱ ተመካካሪዎች፤ በዚህ ድንጋጌ ምክንያት የብሔር እውቅና አግኝተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግን ተገቢውን ውክልና ያላገኙ ብሔረሰቦች መኖራቸውን ጠቁመዋል።  በዚህም በሕገ መንግስቱ የተቀመጠው ቁጥር፤ ውክልና ማግኘት ያለባቸው ብሔረሰቦችን ማስተናገድ የሚያስችል እንዲሆን ተጠይቋል። 

የክልልነት ጥያቄ ያስነሳው የብሔር ፌደራሊዝም

በሥራ ላይ ያለው የብሔር ፌደራሊዝም ድክመቶቹ እንዲሻሻሉ ተደርጎ “ይቀጥል” በሚል የቀረበው ምክረ ሀሳብ ሚዛን መድፋቱን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎ የክልልነት ጥያቄዎች “በቃለ ጉባኤ ይያዙልን” የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ተመካካሪዎች መበራከታቸውን ምንጮች ነግረውናል። መልክዓ ምድራዊ የፌደራሊዝም ሥርዓትን በምክረ ሀሳብነት ያቀረቡና፣ አጥብቀው ሲከራከሩ የነበሩ ተመካካሪዎች፤ በጉባኤው ውሳኔ አሰጣጥ መሠረት የብሔር ፌደራሊዝም እንዲቀጥል የሚወሰን ከሆነ፤ የክልልነት ጥያቄዎች መልስ ሊያገኙ ይገባል የሚል አቋም ማንጸባረቃቸውን ሰምተናል። በተለይም የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይገባል የሚሉ ተመካካሪዎች በስልታዊ ቡድን ደረጃ በተካሄደው “ምክክር” ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ምንጮች ገልጠዋል። 

የቋንቋ ጉዳዮች

አማርኛ፤ ብሔራዊ እና የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንዲቀጥል ከመጠየቅ አንስቶ፤ ብሔራዊ ቋንቋ አያስፈልግም እስከሚሉ ድረስ የተለያዩ ምክረ ሀሳቦች የቀረቡበት የቋንቋ ጉዳይ ደግሞ በርካታ አስተያየቶችን ያስተናገደ ሆኗል። ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆኑ በተለያዩ ተመካካሪዎች የቀረቡት አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ ሲሆኑ፤ እንደ ትግርኛ፣ ሶማልኛ፣ አፋርኛ፣ ሲዳምኛ፣ ወላይትኛ፣ የምልክት ቋንቋ፣ እንግሊዝኛ እና አረብኛ ያሉ ቋንቋዎች ደግሞ የፌደራል የሥራ ቋንቋዎች እንዲሆኑ በምክረ ሀሳብ ደረጃ ቀርበዋል።በርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን ደረጃ እነዚህ አማራጮች ውሳኔ እንደሚያገኙ የሚጠበቅ ሲሆን፤ አማርኛ ብሔራዊና የሥራ ቋንቋ፤ ሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎች ደግሞ የፌደራል የሥራ ቋንቋ ሆነው ውሳኔ የመተላለፉ ዕድል ከፍተኛ መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። 

የጷጉሜን ወር ጉዳይ  

በሀገር ግንባታ አጀንዳ ውስጥ መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ የጷጉሜን ወር ጉዳይ ነው። በወሩ ውስጥ ያሉ ቀናት ሠራተኞች ያለ ደመወዝ ክፍያ የሚሠሩባቸው መሆናቸውን ያነሱ ተመካካሪዎች፤ እነዚህ ቀናት የእረፍት ቀናት አልያም የደመወዝ ክፍያ የሚከፈልባቸው ቀናት እንዲሆኑ ጠይቀዋል። [ዋዜማ]