Kassahun Follo- CETU President/ Photo credit- Fortune

ዋዜማ ራዲዮ- ለዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን ዛሬ ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ በመንግስት ክልከላ ምክንያት እንደማያካሂድ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን አስታወቀ።

ኮንፌደሬሽኑ ለጋዜጠኞች በላከው መግለጫ እየተባባሰ ከመጣው የኑሮ ውድነት አንፃር በዝቅተኛ እርከን ላይ የሚገኙ ሰራተኞች ደሞዝ እንዲሻሻል ለመጠየቅ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።


ይሁንና የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር በመስቀል አደባባይ ሰልፉ እንዲደረግ አልፈቀደም።
ኮንፌደሬሽኑ ላለፉት 48 ዓመታት በየዓመቱ የሰራተኞች ቀንን ምክንያት አድርጎ በመስቀል አደባባይና በአዲስ አበባ ስታዲየም ስልፍና ትርዒቶች ሲያደርግ ነበር።


ከ1966ቱ አብዮት ጋር የተወለደው የኢትዮጵያ ስራተኞች ማህበር ኮንፌደሬሽን ባለፉት ዓመታት ስር የሰደዱ የሰራተኛው ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ድምፁን ሲሰማ ቆይቷል።የተወሰኑ ዓመታትን ኮንፌደሬሽኑ ስልጣን ላይ ባሉ ኀይሎች የፖለቲካ ተፅዕኖ ስር ወድቆና የፖለቲካ አጀንዳ አስፋፃሚ እንዲሆን ተደርጎ ተዳክሞም ነበር።


ባለፉት ሶስት ዓመታት የሰራተኛውን የመብት ጥያቄዎች ለማስመለስ ቢንቀሳቀስም ከመንግስት በኩል ቀና ምላሽ እንዳላገኘ ሲናገር ቆይቷል።


የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ ባለፈው ወር ለዋዜማ በሰጡት አስተያየት የሰራተኛው የደሞዝ ማሻሻያ ጉዳይ እንዲስተካከል ከሶስት ዓመታት በላይ ከመንግስት ጋር በትዕግስት ሲደራደሩ መቆየታቸውንና በድርድሩ ውጤት ባለመገኘቱ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ለማቅረብ እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረው ነበር።


የዋጋ ንረቱ በተለይም ሰራተኛው የህብረተሰብ ክፍል ክፉኛ እየፈተነው በመምጣቱ ሳቢያ በመኖርና አለመኖር ጥያቄ ውስጥ እንደሚገኙና፣ መንግስት የተጠየቀውን ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል ተመን እንዲወጣ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ባለመስጠቱ ስሞታቸውን ለዋዜማ አሰምተዋል።

የሰራተኞች ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል ተመን እንዲደነገግ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲጠይቁ መቆየታቸውን ጠቅሰው ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ደግሞ የግብር ታክስ እንዲቀነስ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ቢጠይቁም ምላሽ ባለመሰጠቱ የተነሳ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንገደዳለን ሲሉ ካሳሁን ፎሎ ለዋዜማ ተናግረው ነበር ። [ዋዜማ ራዲዮ]