በፌደራል ከተሞች ጉዳይ 21 ምክረ ሀሳቦች

ዋዜማ- በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በ36ኛ ቀን ውሎው፤ በስምንቱም አጀንዳዎች ዙሪያ የተጠናቀሩ ምክረ ሀሳቦች በሥራ ቡድን ደረጃ ለተመካካሪዎች ቀርበዋል። ከስምንቱ አጀንዳዎች መካከል አንዱ በሆነው የፌደራል ከተሞች ጉዳይ 21 ምክረ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን፤ 20ው ምክረ ሀሳቦች በሥራ ቡድን ደረጃ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው መሆናቸው መገለጡን ምንጮች ነግረውናል።

“አዲስ አበባ ራሷን በራሷ ታስተዳድር፤ ተጠሪነቷም ለፌደራል መንግስት ይሁን” የሚለው ምክረ ሀሳብ ያለ ተጨማሪ አማራጭ ስምምነት ላይ እንደተደረሰበት ሰምተናል። “ከተማዋ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ናት” የሚል ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ ይካተት በሚል ሲቀርብ የነበረው ምክረ ሀሳብ፤ ከከተማዋ ተጠሪነትና ሕጋዊ ቁመና በተነጠለና ራሱን በቻለ ምክረ ሀሳብ እንዲቀመጥ የተደረገ ሲሆን፤ ሁለት አማራጮችን መያዙን ተረድተናል።

ሁለት አማራጮች የቀረቡበት የአዲስ አበባ፣ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫነት ጉዳይ

አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ መሆኗን የሚያመላክት ድንጋጌ በሕገ መንግስቱ ይካተት በሚሉና፣ ድንጋጌው በሕገ መንግስት ውስጥ መካተት የለበትም በሚሉ ተመካካሪዎች መካከል ሰፊ ክርክር ሲካሄድ መቆየቱን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ 120 አባላት ያሉት የጋራ ማረጋገጫ ቡድን ያደራጀው ምክረ ሀሳብ ለጉዳዩ ሁለት አማራጭ ምክረ ሀሳቦችን አቅርቧል። የመጀመሪያ ምክረ ሀሳብ ክልሎች ርዕሰ ከተማቸውን ራሳቸው መምረጥ እንደሚችሉ የሚያስቀምጥ “የመርህ ድንጋጌ” በሕገ መንግስቱ እንዲካተት የሚጠይቅ ነው። ሁለተኛው ምክረ ሀሳብ ደግሞ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ፤ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ከተማዋንና ክልሉን የሚመለከቱ ጉዳዮች በሕግ ይወሰናሉ” የሚል ድንጋጌ እንዲካተት የሚጠይቅ ነው።

እነዚህ አማራጭ ምክረ ሀሳቦች በምን አይነት ሁኔታ እልባት እንደሚያገኙ የሚያመላክት አገላለጽ በሰነዱ ላይ አለመካተቱን ምንጮች ነግረውናል። በምክረ ሀሳቦች ዙሪያ በተደረገው ምክክር ጥያቄ ሲያስነሱ የነበሩ የትርጓሜ ጉዳዮች በባለሙያዎች ትንተና እንዲሰጥባቸው በምክረ ሀሳቡ ላይ መካተቱንም የሰማን ሲሆን፤ “ተጠሪ” እና “አካል” እንዲሁም “ርዕሰ ከተማ” እና “መቀመጫ” የሚሉ አገላለጾችን በሚመለከት ግልጽ የቃላት አጠቃቀም በሕግ እንዲደነገግ መጠየቁን ተረድተናል።

የልዩ ጥቅም ድንጋጌ

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 የተቀመጠውን “ኦሮሚያ ክልልና አዲስ አበባን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ክልሉ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል” የሚለው ድንጋጌ ወጥቶ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ አዲስ ድንጋጌ እንዲተካ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ሰምተናል።

የከተማዋ የበጀት፣ ፖሊስና ፍርድ ቤት ጉዳይ

አዲስ አበባ ለፌደራል መንግስት ከምታበረክተው የገቢ አስተዋጽኦ ጋር የሚመጣጠን የበጀት ድጋፍ ማግኘት እንዳለባት የሚያመላክት ምክረ ሀሳብም ቀርቧል። አዲስ አበባ ራሳቸውን የቻሉ የፖሊስና የፍርድ ቤት  ተቋማት እንዲኖሯት፤ ከተማዋ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫና የዲፕሎማቶች መናኸሪያ ከመሆኗ ጋር በተያያዘም፣ የከተማዋ የፖሊስና የፍትህ ተቋማት ከፌደራል ተቋማት ጋር በትብብርና በቅንጅት እንዲሠሩ የሚል ምክረ ሀሳብም መቅረቡን ሰምተናል። ይህ ጉዳይ በከተማዋ ቻርተር እንዲቀመጥም ምክረ ሀሳቡ ጠይቋል።

የአዲስ አበባ የወሰን ጉዳይ

በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተሞች መካከል የተጀመረው የወሰን ማካለል ሥራ ተጠናቅቆ፤ አዲስ አበባ ሕጋዊ ዕውቅና ያለው ወሰን እንዲኖራት የሚጠይቅ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ሰምተናል። በወሰን ማካለል ሥራው ውስጥ፤ የፌደራል መንግስት፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕጋዊ አካሄዶችን የተከተለ ሚና እንዲኖራቸውም በምክረ ሀሳቡ ተጠይቋል።

በከተማዋ ለሕዝባዊ ቦታዎች፣ ተቋማት እንዲሁም ቅርሶች የሚሰጡ ስያሜዎች ሕብረ ብሔራዊነትንና ሌሎች የማንነት መገለጫዎችን ያማከሉ እንዲሆኑ በምክረ ሀሳብ መቅረቡንም ምንጮች ነግረውናል። የአዲስ አበባ ከተማ የሥራ ቋንቋዎች ደግሞ የፌደራል መንግስት የሥራ ቋንቋዎች (አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና አፋርኛ) እንዲሆኑ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ውክልና ጉዳይ

የፌደሬሽን ምክር ቤት አባልነት በብሔር ውክልና የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ እና ድሬ ዳዋ ከተሞች በምክር ቤቱ ውክልና የሌላቸው ሲሆን፤ ሁለቱ ከተሞች በምክር ቤቱ ውክልና የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች የሚጠይቅ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል። በዚህም ጥናት ላይ ተመስርቶና የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት ሁለቱ ከተማዎች በምክር ቤቱ ውክልና የሚያገኙበት አሠራር እንዲዘረጋ ምክረ ሀሳቡ አቅጣጫ አስቀምጧል።

የድሬ ዳዋ ከተማ ጉዳይ

ድሬ ዳዋ ራሷን በራሷ የምታስተዳድርና፤ ለከተማው ምክር ቤት ተጠሪ የሆነ አስተዳደር ያላት፤ ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግስት እንዲሆን የሚጠቁም ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ሰምተናል። ይህ ጉዳይ በከተማዋ ቻርተር እንዲሠፍር የሚጠይቅ ነጥብ በምክረ ሀሳቡ መቅረቡን የገለጡልን ምንጮች፤ ከተማዋን የሚያዋስኑት ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የጋራ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የሚያመላክት ድንጋጌም በቻርተሩ እንዲካተት ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ነግረውናል። ድሬዳዋ የከተማ እና የገጠር ነዋሪዎቿን መሠረት ያደረገ አስተዳደር እንደሚኖራትም ተመላክቷል።

ድሬዳዋ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራት፣ የራሷ የፖሊስና ፍርድ ቤት ተቋማት እንዲኖሯት፣ ለፌደራል መንግስት በምታበረክተው አስተዋጽኦ ልክ የበጀት ድጋፍ እንዲደረግላት፣ የፌደራል መንግስት የሥራ ቋንቋዎችን በሥራ ቋንቋነት እንድትጠቀም የሚጠይቁ ምክረ ሀሳቦች መቅረባቸውንም ሰምተናል።

የምክረ ሀሳቦቹ ቀጣይ ሂደት

120 አባላት ያሉት የጋራ ማረጋገጫ ቡድን ያደራጃቸው ምክረ ሀሳቦች ከተመካካሪዎች በተሰጡ አስተያየቶች መሠረት ማስተካካያ ተደርጎባቸው፤ ነሐሴ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ለምክክሩ ጠቅላላ ጉባኤ ይቅርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ነግረውናል። በምክረ ሀሳቦቹ ዙሪያ በጠቅላላ ጉባኤው የሚሳተፉ ተመካካሪዎች አስተያየት የሚሰጡበት ዕድል አለ ወይ ስንል የጠየቅናቸው ምንጫችን፤ ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳቦች ከተነበቡ በኋላ ምክረ ሀሳቦችን የተመለከተ አስተያየት ሳይቀበል “በጭብጨባ” እንዲጸድቁ የማድረግ ሂደትን ለመከተል መወሰኑን ነግረውናል።

ኮሚሽኑ ለተመካካሪዎች ባቀረበውና በአመዛኙ ተግባራዊ ባላደረገው የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት መሰረት በጠቅላላ ጉባኤው “ጠንካራ ተቃውሞ” ያልገጠማቸው ምክረ ሀሳቦች በጭብጨባ እንዲጸድቁ ይደረጋል። ተመካካሪዎች “ጠንካራ ተቃውሞ” ማሰማታቸው በምን አይነት ሁኔታ እንደሚረጋገጥ ግን የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓቱ አይጠቁምም። [ዋዜማ]