
ኮሚሽኑ ይቅርታ የጠየቀበት 35ኛ ቀን ውሎ
ዋዜማ- በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 35ኛ ቀን ውሎ በሥራ ቡድን ደረጃ እንዲካሄድ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው የምክክር ሂደት ሳይካሄድ ቀርቷል። የጋራ ማረጋገጫ ቡድን አባላት በየሥራ ቡድኑ የቀረቡ አስተያየቶችን በማካተት የስምንቱንም አጀንዳዎች ምክረ ሀሳቦች በሥራ ቡድን ደረጃ እንዲያቀርቡ ቢታቀድም፤ የጋራ ማረጋገጫ ቡድኑ ሥራውን ባለማጠናቀቁ ምክንያት ሂደቱ ነሐሴ 13 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑን ሰምተናል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ተመካካሪዎችን ሰብስበው ባደረጉት ንግግርም፤ በምክክሩ ሂደት ተፈጥረዋል ላሏቸው መስተጓጎሎች ይቅርታ ጠይቀዋል። ከኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች መካከል አንዱ የሆኑት መላኩ ወልደማርያም፤ አንዳንድ የምክክር መርሃ ግብሮች በታሰበላቸው ጊዜ መካሄድ አለመቻላቸውን የገለጡ ሲሆን፤ በመሰል ሁኔታዎች ውስጥ ተመካካሪዎች መጉላላታቸውን ጠቁመዋል። ለዚህም ኮሚሽኑ “ይቅርታ ይጠይቃል” ማለታቸውን ምንጮች ነግረውናል።
እርስ በእርስ የሚጋጩ ምክረ ሀሳቦች
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ ለተመካካሪዎች ባደረጉት ንግግር፤ ሁለትና ከዛ በላይ ምክረ ሀሳቦች የቀረቡባቸው ንዑስ አጀንዳዎች መኖራቸውን የገለጡ ሲሆን፤ እነዚህ ምክረ ሀሳቦች አንዳቸው ሌላቸውን “የሚያጣፉ” መሆናቸውን ተናግረዋል። ተመካካሪዎች “በተቻለ መጠን” ምክረ ሀሳቦችን ወደ አንድ እንዲያመጡ የጠየቁት ኮሚሽነሯ፤ “መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ለመግባባት ጥረት እንዲደረግ” መጠየቃቸውን ሰምተናል። ኮሚሽኑ ባካሄዳቸው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች የተሰበሰቡና ክልሎችን የሚመለከቱ አጀንዳዎችን ለክልል አስፈጻሚ አካላት ለማስረከብ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ መግለጣቸውን ሰምተናል።
የዋና ኮሚሽነር መስፍን ጉዳይ
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከሰሞኑ ምክክር በሚካሄድበት አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል አለመታየታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ በቤተሰብ ጉዳይ ከሀገር መውጣታቸውን ዋዜማ ከኮሚሽኑ ምንጮቿ አረጋግጣለች። የምክክር ሂደቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ከመድረሱ ጋር በተያያዘም፤ የዋና ኮሚሽነሩ አለመገኘት ክፍተት ይፈጥራል የሚል ስጋት መኖሩን የገለጡልን ምንጫችን፤ ምክክሩ ከመጠናቀቁ በፊት ወደ ሀገር ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል። የኮሚሽኑ ሰባት ኮሚሽነሮች ከተመካካሪዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ግን የዋና ኮሚሽነሩን አለመኖር በተመለከተ ያሉት ነገር የለም።
ኮሚሽነሮች በመሪነት የሚከታተሉት አጀንዳ እንዴት ተለየ?
በምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ የሚገኙ ፓርቲዎች እና ተመካካሪዎች ካቀረቧቸው ቅሬታዎች መካከል በአንዳንድ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ላይ ያነሷቸው ይገኙበታል። ስምንቱ ኮሚሽነሮች እያንዳንዳቸው አንድ አጀንዳን በዋነኛነት በመያዝ እየተከታተሉ የሚገኙ ሲሆን፤ ዋዜማ ኮሚሽነሮች በመሪነት የሚሳተፉባቸው አጀንዳዎች እንዴት ተለዩ ስትል የኮሚሽኑን ምንጮቿን ጠይቃለች። ስምንቱ ኮሚሽነሮች የትኞቹን አጀንዳዎች በመሪነት እንደሚከታተሉ ለመለየት እጣ መውጣቱን የገለጡልን ምንጫችን፤ በእጣው መሠረት የኮሚሽነሮች ምደባ መከናወኑን ነግረውናል። ይሁንና በኮሚሽነሮች ላይ እየተነሳ ያለውን ቅሬታ ተከትሎ በኮሚሽኑ ምክር ቤትም ይሁን በአማካሪ ምክር ቤቱ ውስጥ የውይይት ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ የተደረገ ውይይት እንደሌለ ሰምተናል።
የክልሎች ሕገ መንግስት ጉዳይ
የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ላይ እየተመካከረ የሚገኘው የሥራ ቡድን፤ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የክልሎች ሕገ መንግስት አንዱ ነው ሲል ባጠናቀረው ምክረ ሀሳብ ላይ ማካተቱን ተረድተናል። በክልሎች ውስጥ የሚገኙ የተለያየ ብሔር ላላቸው ዜጎች እኩል መብት የማይሰጡ የክልል ሕገ መንግስቶች መኖራቸው በምክክሩ መነሳቱን የገለጡልን ምንጮች፤ እነዚህ ሕገ መንግስቶች በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም ምክንያት መሆናቸው መመላከቱን ጠቁመዋል። በዚህም የክልሎች ሕገ መንግስታት ሁሉም ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጠበቅ በሚያደርግ መልኩ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ምክረ ሀሳብ መቅረቡን፤ ይህ ምክረ ሀሳብም ተቀባይነት ማግኘቱን ሰምተናል።
የሠራተኞች የሥራ ግብር እንዲቀንስ የቀረበው ምክረ ሀሳብ
ከስምንቱ የሥራ ቡድኖች መካከል አንዱ በሆነውና የሙስና እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ እየተመካከረ የሚገኘው የሥራ ቡድን፤ የመንግስትም ሆነ የግል ድርጅት ሠራተኞች የሚከፍሉት የሥራ ግብር እንዲቀንስ ምክረ ሀሳብ ማቅረቡን ሰምተናል። የሙስና ተግባራት እንዲቀንሱ ማድረግ ያስችላሉ በሚል ከቀረቡ ምክረ ሀሳቦች መካከል ሠራተኞች የሚያገኙት ክፍያ እንዲያድግ ማድረግ አንዱ መሆኑን የነገሩን ምንጫችን፤ የደመወዝ ማስተካከያ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ሠራተኛው የሚከፍለው የሥራ ግብር እንዲቀንስ ማድረግም ምክረ ሀሳብ ሆኖ የቀረበ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል። ይሁንና ከደመወዝ ላይ የሚቆረጠው “የሥራ ግብር ምን ያህል ይሁን?” የሚለው ጉዳይ በጥናት እንዲወሰን የተተወ ሆኗል። በሙስና ተግባራት ላይ መሳተፋቸው የተረጋገጠ ግለሰቦች እስከ ዕድሜ ልክ እስራት የሚደርስ ቅጣት እንዲጣልባቸው የሚያደርግ የሕግ ማሻሻያ እንዲደረግ መጠየቁንም ሰምተናል።
መግለጫ ለማውጣት “የፈሩ” ፓርቲዎች
በምክክር ሂደቱ ዙሪያ መግለጫ ያወጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም፤ መግለጫዎችን ተከትሎ ሊከሰት የሚችልን ጫና በመፍራት መግለጫ ያላወጡ ፓርቲዎች መኖራቸውን ዋዜማ ሰምታለች። በጉዳዩ ዙሪያ ለዋዜማ ቃላቸውን የሰጡ የሦስት ፓርቲዎች አመራሮች፤ ከምክክር ሂደቱ አሁናዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ መግለጫ ለማውጣት የሚደረጉ ጥረቶች ሊያስከትሉ ከሚችሉት ውጤት ጋር በተያያዘ በፓርቲዎች አባላት መካከል ልዩነት መፍጠራቸውን ገልጠዋል።
የፓርቲያቸው አባላት መግለጫ እንዲወጣ መጠየቃቸውን የገለጡልን የአንድ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር፤ መግለጫ “ይሰጥ፤ አይሰጥ” በሚለው ጉዳይ በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መካከል የሀሳብ ልዩነት መፈጠሩን ነግረውናል። ፓርቲው መግለጫ ቢያወጣ ከመንግስት ጋር ያለው ግንኙነት “ይበላሻል” የሚል ስጋት ያላቸው አመራሮች መግለጫ እንዳይወጣ ማድረጋቸውን አመላክተዋል። በመጪው መስከረም ወር ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የመንግስት ምስረታ ስልጣን እንደሚሰጣቸው “ቃል የተገባላቸው” የፓርቲዎች አመራሮች መኖራቸውንም የጠቀሱልን ምንጮች፤ መሰሉ ሁኔታ በፓርቲዎች የምክክር ተሳትፎ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል። [ዋዜማ]