ዋዜማ- በስምንት አጀንዳዎች ዙሪያ እየመከረ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስምንቱ የሥራ ቡድኖች የቀረቡ 476 ምክረ ሀሳቦችን ለማጽደቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል። በ96 ንዑስ አጀንዳዎችና በ225 መሪ ጥያቄዎች መሠረት ምክክር ሲያደርጉ የቆዩ ተመካካሪዎች ያቀረቧቸው ምክረ ሀሳቦች በልዩነት የተያዙና አማራጭ የቀረበላቸው ነጥቦችን ያቀፉ መሆናቸውን ምንጮች ነግረውናል።

በሀገር ግንባታ አጀንዳ ዙሪያ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች

በሀገር ግንባታ አጀንዳ ዙሪያ በተመካከረው የሥራ ቡድን ከቀረቡ ምክረ ሀሳቦች መካከል፤

  • ሀገር የብሔረሰቦችና የዜጎች ናት፣ በሕገ መንግስቱ መግቢያ ላይ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች” የሚለው አገላለጽ “እኛ የሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ሕዝብ” በሚል እንዲተካ፣
  • የኢትዮጵያ ታሪክ  ምሁራንን ያሳተፈ ገልለተኛ ኮሚሽን ተቋቁሞ እንዲጻፍ፣ ታሪክ ከፖለቲካ መጠቀሚያነት እንዲወጣ፣ የጭቆና ታሪክን የሚያንጸባርቁ ነጠላና ከፋፋይ ትርክቶችን በማረም የወል ትርክት ይዘርጋ፣
  • ቋንቋን መሠረት ያደረገ ጉዳትና ጥቅም እንዳይኖር ማድረግ፣ ብሔራዊ ቋንቋን ተግባራዊ ለማድረግ ተጨማሪ ጥናትና ምርምር እንዲካሄድ፣ ግዕዝ ቋንቋን የጥናትና ምርምር ቋንቋ ማድረግ፣
  • የፌደራል መንግስት አምስት የሥራ ቋንቋዎች (አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ፣ አፋርኛ) እንዲኖሩት ማድረግና ሌሎች ቋንቋዎች በጥናት ላይ ተመስርተው የሥራ ቋንቋ መሆን የሚችሉበትን አሠራር መዘርጋት፣ ሁሉም ክልሎች ከሚጠቀሙበት የሥራ ቋንቋ በተጨማሪ ከፌደራል የሥራ ቋንቋዎች መካከል አንዱን በሥራ ቋንቋነት እንዲጠቀሙ ማድረግ፣
  • ብሔራዊ በዓላትን ሊውስን የሚችል ዝርዝር ሕግ እንዲዘጋጅ፣ በዩኔስኮ የተመዘገቡና ወደፊትም የሚመዘገቡ በዓላት ሕዝባዊ በዓላት ሆነው እንዲከበሩ ማድረግ፣ 
  • በክልሎች መዝሙሮች ላይ ያሉ አሉታዊ ይዘቶች እንዲስተካከሉ ማድረግ የሚሉት እንደሚገኙበት ሰምተናል። 

የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይን በሚመለከት ሁለት አማራጭ ምክር ሀሳቦች መቅረባቸውን የነገሩን ምንጮች፤ ሁለቱም ምክረ ሀሳቦች በሥራ ላይ ያለው ሰንደቅ ዓላማ የመደብ ቀለማት ባሉበት እንዲቀጥሉ የሚያደርጉን መሆናቸውን ገልጠዋል። የመጀመሪያ አማራጭ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው አርማ ባለበት እንዲቀጥል የሚጠይቅ ሲሆን፤ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ አርማው ሕብረ ብሔራዊነትን በሚያሳይ መልኩ እንደ አዲስ እንዲዘጋጅ የሚጠይቅ መሆኑን ተረድተናል።

በመንግስት አደረጃጀት አጀንዳ ዙሪያ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች

በመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ ዙሪያ የተመካከረው የሥራ ቡድን ካቀረባቸው  ምክረ ሀሳቦች መካከል፤

  • ፌደራላዊ የመንግስት ሥርዓት እንዲቀጥል፣ በሥራ ላይ ያለው የፌደራሊዝም ሥርዓት ክፍተቶቹ ተጠንተውና ግብዓት ተጨምሮበት ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ተግባራዊ እንዲደረግ፣
  • ራሳቸውን በብሔር ማንነት መግለጽ የማይፈልጉ ዜጎች እንደ ኢትዮጵያዊ ብቻ እንዲታዩ ማድረግ፣ የተለያየ የብሔር ማንነት ካላቸው ወላጆች የተወለዱ ዜጎችን የማንነት ጉዳይ የሚመለከት ሕግ ማዘጋጀት፣
  • ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮችን የሚመለከት “ሕብረ ብሔራዊ የአንድነት ኮሚሽን” ማቋቋም፣
  • በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” የሚለው ድንጋጌ ውስጥ “እስከመገንጠል” የሚለውን ቃል ማስወጣት፣
  • “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች” የሚለውን አገላለጽ “ብሔረሰብ“ በሚል መተካት፣
  • ክልሎች መደበኛ ፖሊስ ብቻ እንዲኖራቸው ማድረግ (የልዩ ኃይል አደረጃጀትን ሙሉ በሙሉ ማፍረስ)፣
  • በክልሎች ግጭቶች በሚከሰቱበትና አስገዳጅ በሆነበት ጊዜ ክልሉ ጥሪ ባያቀርብም የፌደራል መንግስት ጣልቃ መግባት የሚችልበትን አሠራር መዘርጋት፣
  • የሕዝብ ቆጠራ በማካሄድ አዲስ የድጎማ በጀት ቀመር ተግባራዊ ማድረግ፣
  • የአካባቢ አስተዳደሮች በአካባቢው ያሉ ማንነቶች የሚወከሉበት እንዲሆኑ ማድረግ፣ የአካባቢ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ፣
  • ንቁ የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች መፍትሄ እስኪያገኙ ድረስ የፌደራል መንግስት ጸጥታ የማስከበር ኃላፊነትን እንዲወስድና በሌሎች ጉዳዮች የፌደራል መንግስትና ክልሎች በትብብር እንዲሠሩ ማድረግ፣
  • የኢትዮጵያ ሕጋዊና ታሪካዊ ደንበር ቀይ ባሕር መሆኑን ማረጋገጥ፣
  • ሕግ የመተርጎም ስልጣን ያለው የሕገ መንግስት ፍርድ ቤት ማቋቋም፣ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 105 ከሕገ መንግስት ማሻሻያ ጋር ተያይዞ “ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት” የሚለው ድንጋጌ “ሶስት አራተኛ ክልሎች በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁት” በሚል እንዲተካ፣
  • የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአዋጅ ዕውቅና እንዲሰጠው፣ አዲስ የሕዝብ ቆጠራን መሠረት ያደረገ የምርጫ ክልል አደረጃጀት ተግባራዊ እንዲደረግ የሚሉት እንደሚገኙበት ዋዜማ ሰምታለች።

ከመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ጋር በተያያዘ ሁለት አማራጭ ምክረ ሀሳቦች መቅረባቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ በሥራ ቡድኑ ውስጥ ከሚገኙ ተመካካሪዎች መካከል “አብዛኛው” ፓርላመንታዊ ሥርዓት ቀጥሎ፣ መሪው ከፓርላማ የሚመረጥ ፕሬዝዳንት እንዲሆን የሚለውን አማራጭ መደገፋቸውን፤ “የተወሰኑ” ተመካካሪዎች ደግሞ ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲደረግና መሪው በሕዝብ የሚመረጥ ፕሬዝዳንት እንዲሆን ምክረ ሀሳብ ማቅረባቸውን ነግረውናል። ይሁንና “አብዛኛው” እና “የተወሰኑ” በሚል የተቀመጡ አገላለጾች፤ የድጋፍ መጠናቸው በቆጠራ ሳይረጋገጥ የተሰጡ ናቸው የሚል ቅሬታ መቅረቡን ሰምተናል።

የፌደራልና የክልል መንግስታት የሥልጣን ጊዜ ስድስት ዓመት እንዲሆን በጠየቀው ምክረ ሀሳብ፤ አንድ መሪ ከሁለት የስልጣን ጊዜያት የበለጠ እንዳያገለግል ገደብ መቀመጡን አውቀናል። የምርጫ ሥርዓትን በሚመለከት ደግሞ “ቅይጥ ትይዩ” የምርጫ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ምንጮች ገልጠዋል። ሥርዓቱ በዝርዝር በሚወጣ ሕግ መሰረት ተግባራዊ እንዲደረግ የጠየቀው ምክረ ሀሳቡ፣ መንግስት መመስረት የሚያስችለው የወንበር መጠን በሚዘጋጀው ሕግ እንዲደነገግ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በሃይማኖት ጉዳይ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች

በሃይማኖት ጉዳዮች ዙሪያ የተመካከረው የሥራ ቡድን ካቀረባቸው ምክረ ሀሳቦች መካከል፤

ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚመለከት “የሃይማኖት ኮሚሽን” እንዲቋቋም፣ የጎዳና ላይ ሃይማኖታዊ ተግባራት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወኑ ማድረግ የሚያስችል መመሪያ እንዲዘጋጅ፣

ተቋማት አርብ ቀን ለጁምዓ ጸሎት ከ5 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት ያለውን ጊዜ የዕረፍት ጊዜ እንዲያደርጉ፣ በዓለ ሀምሳ የዘመን መቁጠሪያ (ካላንደር) ላይ ዕውቅና ያለው የበዓል ቀን እንዲሆን፣ የአዳዲስ ሃይማኖቶች ምዝገባ ጥብቅ እንዲሆን፣

የአደንዛዥ ዕጽ እርሻን በሌሎች ምርቶች መተካት የሚያስችል ሀገራዊ ንቅናቄ እንዲካሄድ፣

ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ ገደብ እንዲጣል፣

ፍትሃዊና ቦታ ቆጣቢ የሃይማኖት ተቋማት ቦታ አሰጣጥን ተግባራዊ ማድረግ፣ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሕገ ወጥ የሠውና የመሳሪያ ዝውውር እንዳይካሄድ ማድረግ፣

የሃይማኖት አባቶች በቂ ክብርና ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ማድረግ፣

የሃይማኖት ተቋማት ኦዲት ተደርገው የፋይናንስ ግልጸኝነት እንዲፈጠር ማድረግ የሚሉት እንደሚገኙበት ምንጮች ነግረውናል።

የምክረ ሀሳቦቹ ቀጣይ ሂደት

120ዎቹ የጋራ ማረጋገጫ ቡድን አባላት ያዘጋጁትና ከተመካካሪዎች በቀረቡ አስተያየቶች መሠረት ለመጨረሻ ጊዜ የተስተካከለ ምክረ ሀሳብ ነሐሴ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ለምክክሩ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚቀርብ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።

በጠቅላላ ጉባኤው የሚጸድቁ ምክረ ሀሳቦችን የሚረከበው ኮሚሽኑ፤ ምክረ ሀሳቦቹ በተግባር ላይ ሊወሉ የሚችሉበትን ስልት የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካሉ እና ለሚመለከታችው የመንግስት አካላት እንደሚያቀርብ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ 1265/2014 ደንግጓል። ኮሚሽኑ ከሚረከባቸው ምክረ ሀሳቦች መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ወደ ቀጣዩ ሂደት የማያሳልፋቸው ምክረ ሀሳቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል [ዋዜማ]